Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት ተበዳሪዎች ቁጥር መቀነሱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፋይናንስ ተቋማት በጤናማ አቋም ላይ የሚገኙ ናቸው ቢባልም፣ የባንኮችና የአነስተኛ የብድር ተቋማት ተበዳሪዎች ቁጥር በ7.8 በመቶ መቀነሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ አመለከተ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2015 ዓ.ም. ግማሽ የሒሳብ ዓመት የፋይናንስ ተቋማትን አጠቃላይ አፈጻጸም በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት፣ የፋይናንስ ተቋማት ተበዳሪዎች በተለይ ደግሞ የአነስተኛ ብድር ተቋማት ቁጥር መቀነሱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ የተበዳሪዎችን ቁጥር መቀነስን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የፋይናንስ ተቋማት በሁሉም በሚባል ደረጃ አፈጻጸማቸው ዕድገት የታየበት ቢሆንም፣ በ2015 ግማሽ የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ግን የተበዳሪዎች ቁጥር ቀንሷል ብለዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸሞች ውስጥ ዕድገት ያላሳየ ተብሎ የሚጠቀሰው የተበዳሪዎች ቁጥር ነው፤›› ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በ2015 ዓ.ም. ግማሽ የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኮችና የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ተበዳሪዎች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት በ7.8 በመቶ ቀንሶ 4.87 ሚሊዮን ሆኗል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ለተበዳሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከነበረው አለመረጋጋት በተያያዘ ባጋጠመ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹አበዳሪዎች ራሳቸው በተለይ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት የማበደር ፍላጎታቸው ቀንሷል፤›› ያሉት ምክትል ገዥው፣ ምክንያቱ ደግሞ ከአለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ የሚሰጡት ብድር አይመለስም ከሚል ሥጋት ጋር የተያያዘ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው አክለዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ግማሽ የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ከተመዘገቡት አጠቃላይ ተበዳሪዎች ውስጥ፣ በቅርቡ ከአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋምነት ወደ ባንክ ያደጉ አምስት ባንኮችን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ የባንክ ተበዳሪዎች ቁጥር 3.73 ሚሊዮን ነው፡፡ ከአነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ ያደጉት አምስቱ ባንኮች በተናጠል ያስመዘገቡት የተበዳሪዎች ቁጥር 3.36 ሚሊዮን በመሆኑ፣ ከእነዚህ ባንኮች በተጨማሪ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆዩት ባንኮች ተበዳሪዎች ቁጥር 400 ሺሕ በመሆኑ ዕድገት ያልታየበትና አነስተኛ የሚባል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከባንኮች ሌላ ብድር በማቅረብ የሚታወቁት 44 አነስተኛ ብድርና የቁጠባ ተቋማት፣ የተበዳሪዎቻቸው ቁጥር 1.14 ሚሊዮን እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡ የብድርና ቁጠባ ተቋማቱ ተበዳሪዎች ቁጥር ዘንድሮ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ምክንያቱ አንዱ ካለመረጋጋቱ ጋር ተያይዞ የማበደር ፍላጎት በመቀነሱ የተከሰተ ነው ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ሌላው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ አምስት የብድርና የቁጠባ ተቋማት ተበዳሪዎቻቸውን ይዘው ወደ ባንክ ከማደጋቸው ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡

በአንፃሩ ብድር በማቅረብ የሚታወቁት ባንክና አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት በ2015 ዓ.ም. ግማሽ የሒሳብ ዓመት የሰጡት የብድር መጠን በ31 በመቶ ሲያድግ፣ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት የተበዳሪዎቻቸው ቁጥር ከመቀነሱ ባለፈ የተበላሸ የብድር ምጣኔያቸውም ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ከአምስት በመቶ ጣሪያ በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፣ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ 44 አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የተበላሸ የብድር መጠን 7.8 በመቶ ደርሷል፡፡ በተለይ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት የተበላሸ የብድር መጠንና በተወሰነ ደረጃም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያላስመለሷቸው ብድሮች ስላሉ፣ በዚያ ላይ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ የሚያመለክት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብዙ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑ በአድናቆት ጭምር የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ቀሪ ያልተመለሱ ብድሮችን ማስመለሱ ላይ ግን ሊሠራ እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት አካባቢ ያለው የተበላሸ የብድር መጠን ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ የወጣ በመሆኑ ችግሩ ከዚህም በላይ እንዳይወጣ በጥብቅ ሊሠራበት እንደሚገባ ያስረዱት ምክትል ገዥው፣ ያልተመለሱ ብድሮችን የማስመለሱ ሥራ ሌሎች ባንኮችም አጠንክረው ሊሠሩበት የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች