Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልኳንዳ ነጋዴዎች የሚጣልባቸው የግምት ታክስ ሥሌት ከሥራ እያገለላቸው መሆኑን ተናገሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የገቢዎች ቢሮ ልኳንዳን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ የሕግ ማስከበር ንቅናቄ አደርጋለሁ ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት የሚሰጡ የልኳንዳ ነጋዴዎች የሚጣልባቸው የግምት ታክስ ሥሌት አቤቱታ ባለመጤኑ ከሥራ እየተገለሉ መሆናቸውን፣ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የልኳንዳ ነጋዴዎች እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው የታክስ ሥሌት ገቢና ወጪያቸውን ከግምት ውስጥ ያላስገባና አግባብነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲሻሻል ሰፊ ጥያቄና ጉትጎታ ቢደረግም፣ ተገቢ ምላሽ ባለማግኘቱ በርካታ ነጋዴዎች ከዘርፉ እየወጡ ናቸው፡፡

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ልኳንዳ ቤቶች አሁን እየተዘጉ ስለመሆናቸው የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ነጋዴዎቹ ከእነ ዕዳቸው ራሳቸውን እንዲያሸሹ ያደረጋቸው ምክንያት መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ባለመስጠቱ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበሩ የልኳንዳ ንግድ ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚታዩበት ዕይታ መታየት የለበትም የሚል አቤቱታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጨምሮ፣ ለገቢዎች ቢሮ በተደጋጋሚ ሲያቀርብ መቆየቱን አቶ አየለ ተናግረዋል፡፡

ልኳንዳ ቤቶቹ ከሁለት ሚሊዮን እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው፣ ዕዳውን እንደያዙ ከዘርፉ በተለያየ መንገድ እየወጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር በጠቅላላው ሁለት ሺሕ የሚሆኑ አባላት ቢኖሩትም፣ በየጊዜው ይህ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን፣ መንግሥት ማየት የሚገባውን ጉዳይ ለማየት ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት፣ በሥጋ ላይ ቁርጥ ተብሎ የሚጣለውን ታክስ ማንሳት ወይም በውይይት ላይ የተመሠረተና ጥናት የተደረገበት ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚገባው ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከሰሞኑ በዓመቱ የመጀመርያ ስድስት ወራት ዕቅድ ክንውን የሚገመግም መድረክ አሰናድቶ የነበረ ሲሆን፣ በመድረኩም በተጠቀሰው ጊዜ 42.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በመድረኩ ላይ ቢሮው በቀጣይ ስድስት ወራት የሰበሰበውን ገቢ ለማጠናከር ዕርምጃውን ማጠናከር ይገባዋል ተብሎ ከለያቸው ጉዳዮች ውስጥ ከልኳንዳ ቤቶች ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሶ፣ በቄራዎች ድርጅት ዕርድ ፈጽመዋል ብሎ ለገቢዎች ቢሮ ዝርዝራቸውን ከላካቸው 152 ድርጅቶች ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ግብራቸውን ለቢሮው ማሳወቃቸው በመድረኩ ተናግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ለሪፖርተር  እንዳስረዱት፣ ማንኛውም በከተማው ውስጥ የሚደረገው ዕርድ በቄራ ድርጅት ሒደት ውስጥ ማለፍ ያለበት ሲሆን፣ ይህ መሆኑ ደግሞ በቀላሉ በአገልግሎቱ የተጠቀመን ሰው ለማወቅ የሚያግዝ ነው፡፡

በቄራ ድርጅት የተገለገለ ባለ ልኳንዳ በኪሎ ግራም ተመን የወጣለትን የቁም እንስሳ በመሸጥ ያገኘው ገቢና ወጪ ተነፃፅሮ በትርፉ ላይ ታክስ እንደሚጣል በመመርያ መደንገጉን አቶ ሙሉጌታ አስታውሰው፣ በዚህ አሠራር በርካቶች እየተገለገሉ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎች ከቄራዎች ድርጅት ውጪ እንደሚያሳርዱ ተናግረዋል፡፡

ከዕርድ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በቄራ ድርጅት አገልግሎት ያለመጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ ታርዶ የመጣን ከብት (ሥጋ) በደረሰኝ ያለመሸጥ ችግር እንደሆነ ያስረዱት አቶ ሙሉጌታ፣ ይህ ጉዳይ በተለይም በደረሰኝ እንዲሸጡ የሚገደዱ ልኳንዳ ቤቶችን የሚመለከት መሆኑን አክለዋል፡፡

የልኳንዳ ማኅበር አባላት ከሚያነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ በሕጋዊ መንገድ በቄራዎች ድርጅት ዕርድ አከናውነው ቢሸጡም፣ ሌሎች በቄራዎች ድርጅት ሳያሳርዱ ሥጋ መሸጣቸው አንዱ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ ስለሆነም የግምት ታክስ ሥሌት አፈጻጸም መመርያው በሕጋዊዎቹ ብቻ ላይ እየተተገበረ በመሆኑ ወጥ አፈጻጸም ሊኖር እንደሚገባ ለቢሮው ጥያቄ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ በቅርቡ በተመሠረተው በሸገር ከተማ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የዕርድ አገልግሎት የሚጠቀሙ ነጋዴዎች እንዳሉ ተገልጾ፣ ሆኖም እነዚህ ግለሰቦች የሚጠበቅባቸውን የታክስ ግዴታ ለሁለቱም ከተሞች ገቢ የማያደርጉበት ሁኔታ እንደሚስተዋል የገቢዎች ቢሮው አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከሸገር ከተማ ጋር በጉዳዩ ላይ የመሥራት ፍላጎት (ሐሳብ) እንዳለው ያስረዱት አቶ ሙሉጌታ፣ በሸገርም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ የዕርድ አገልግሎት ያገኘ ነጋዴ ባሳረደበት ከተማ አሳውቆ ለተገቢው አካል ገቢ ማስገባት እንደሚጠበቅበትና ለዚህም መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የታክስ መሠረቱ ይሰፋል ሲባል ከሚደረጉ ነገሮች ውስጥ ወደ ታክስ ያልገቡ አካላትን እንዲገቡ ማድረግ መሆኑ ተገልጾ፣ ይህም በንግዱ ኅብረተሰብ መካከል ፍትሐዊ ውድድር እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡

ከየካቲት ወር ጀምሮ የገቢዎች ቢሮ የልኳንዳን ንግድ ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ (በተለይም ኢመደበኛ ንግዶች) የሕግ ማስከበር የንቅናቄ መድረክ እንደሚኖር ያስረዱት የቢሮ ኃላፊው፣ ይህም ከንግድ ቢሮ ጋር በቅንጅት የሚሠራና ሌሎች ተቋማትንም የሚያሳትፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ በበኩላቸው፣ መንግሥት ለልኳንዳ ነጋዴዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ባለመበጀቱ በዘርፉ ተዋንያን ላይ አሉታዊ አመለካከቶች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቁም እንስሳት ገበያው በተገቢው መንገድ ቁጥጥር የሚደረግበት ባለመሆኑ፣ “የመኪና ገበያ ዓይነት” መልክ ይዟል ብለዋል፡፡

ማኅበሩ ከሌሎች የዘርፍ ማኅበራት ጋር በመሆን ለከተማው ከንቲባ እያጋጠሙ በሚገኙ ማነቆዎች ላይ ጥያቄ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፣ ውጤቱም ወደፊት እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር በተደጋጋሚ የግምት ታክስ ሥሌት አፈጻጸም መመርያ መውጣቱ፣ በሥሩ ያሉት ነጋዴዎች ሥራቸውን ለማቆም የገፋፋቸው ነው ሲል መቆየቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች