Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን በዋጁ አሠራሮችና ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች በመምራት ወደ ሥራ ለማስገባት የምታደርገው ሽርጉድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፋጥኖ በአጭር ጊዜ እንዲጀመር የመንግሥት አቅጣጫ ተሰጥቶበታል፡፡

የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ይፋ ይደረግበታል ከተባለለት ጊዜ እንደዘገየ ሐሳብ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቢኖሩም አዋጁን ማፅደቅ፣ ራሱን የቻለ ቦርድ ማቋቋም፣ ዋና ዳይሬክተርና ሠራተኞችን ማደራጀት በማስፈለጉ ሒደቱ ዘገየ የሚባል እንዳልሆነ የሚሞግቱም በርካቶች ናቸው፡፡

በአዋጅ የተቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዲስ የሆነ ተቋም እንደመሆኑ፣ በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ማሰባሰብን ይጠይቅ እንደነበር፣ በዚህ ሰዓት የካፒታል ገበያውን ቶሎ አደራጅቶ ለመሥራት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን  አስታውቋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር  ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለሚመሠረተው የካፒታል ገበያ የፈቃድና የክትትል ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉትን በርካታ መመርያዎችና ደንቦች አዘጋጅቶ ለቦርድ እንዳቀረበ ተናግረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የመጀመርያው ተግባር የሆነው የተለያዩ መመርያዎችንና ደንቦችን ማርቀቅ ነው፡፡ በዚህም አንዳንዶቹ ተጠናቀው ወደ ቦርድና ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር የተላኩ ሲሆን፣ መመርያዎቹ ከፀደቁ በኋላ ባለሥልጣኑን ይበልጥ በማደራጀት ተልዕኮውን እንደሚያጠናክሩ ብሩክ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ብቻም ሳይሆን የሚመሠረተው የካፒታል ገበያ፣ በገበያው የሚሳተፉ ኢንቨስተሮችና ወደ ፊት ዝርዝራቸው የሚገለጹት ድርጅቶች ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቁሟል። ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ በአሁን ሰዓት ያሉት ድርጅቶች በአክሲዮን ገበያ ገብተው ለመገበያየት ብቁ መሆናቸውን ፈትሾ፣ የሚጎድላቸውን ለመሙላትና ለማብቃት ታሳቢ ያደረጉ ዝግጅቶች እየተካሄዱና መመርያዎችም በባለሥልጣኑ እንየተቀረፁ ነው፡፡

በባለሥልጣኑ ዕቅድ መሠረት በአጭር ጊዜ ማለትም ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ውስጥ በሚፈጅ ጊዜ አስፈላጊውን ፈቃድ ለሚፈልጉ በንግድ ባንኮች፣ በኢንቨስትመንት ባንኮች ላይ ለሚሰማሩ ተዋንያን፣ አገናኝ አካላት/ደላሎች/፣ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ብሩክ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ የኢንቨስትመንት ባንክ ባለመኖሩ አዲስ ባንኮች ነው የሚቋቋሙት? ወይስ ያሉት ባንኮች ማሻሻያ ተደርጎ ወደ ኢንቨስትመንት ባንክ ነው የሚቀየሩት? የሚለው ጥያቄ ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ብሩክ (ዶ/ር)፣ አዲስ የኢንቨስትመንት ባንኮችን ማቋቋም እንደሚቻል በሕጉ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁን ላይ በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች በገበያው መሳተፍ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመወሰን ምክክሮች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ መንግሥት የመጨረሻ ውሳኔ እንዳሳለፈና ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንና ከኢትዮጵያ ሴክዩሪቲ ኤክስቼንጅ ጋር በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ የምክክር መድረክ›› በሚል ርዕስ ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ባሰናዳው የምክክር መድረክ ላይ በአጭር ጊዜ ዕውን ይሆናል ስለተባለው የካፒታል ገበያና ግብይቱ (ኤክስቼንጁ) ላይ ያሉ አገልግሎቶች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ የፈቃድ አሰጣጥ ሒደት፣ ካፒታል ገበያውን ለማስተዳደር በተወጠኑ የሕግ፣ የፋይናንስና የኦዲተሮች ሚናን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የከፍተኛ አማካሪዎች ገለጻና የባለድርሻ አካላት ጥያቄና ሐሳብ ተንሸራሽሯል፡፡ 

የካፒታል ገበያ ምንነትና ያለበት ደረጃ፣ ወደ ካፒታል ገበያ የሚገቡ ድርጅቶች በምን ዓይነት መንገድ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል? ከሕግ ማዕቀፍ አኳያ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በምን ዓይነት መንገድ መሳተፍ ይችላሉ? የባለሙያ ትብብርና ድጋፍ በኢትዮጵያ በሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ሴክዩሪቲስ ኤክስቼንጅ) በኩል እስካሁን ድረስ የተሠሩ ሥራዎች በመድረኩ ተዳሰዋል፡፡

ካፒታል ገበያ ይፋ ተደርጎ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ የፋይናንስ ተቋማት የሚኖራቸው ሚና በተለይ ደንበኞቻቸው በውስጣቸው የሚገኙ ሥራተኞች ብቁ የሆነ ችሎታና ክህሎት እንዲኖራቸው የማድረግ በርካታ ሥራ ይኖራል፡፡ ባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አድርጎ የሚይዘው ከፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር፣ የፋይናንስ ትምህርት ተቋማት ጋር) አብሮ በመሥራት ክህሎትን የማሳደግና የማስፋት ሥራ የሚሠራ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

‹‹ይህንን ሒደት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ፈቃድ መስጠት እንጀምራለን፡፡ የመንግሥት ትልቅ ድጋፍ አለን፡፡ ከመንግሥት የተሰጠን መመርያ በአጭር ጊዜ የካፒታል ገበያውን ወደ ሥራ እንድናስገባ ነው፤›› ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከፋይናንስ አቅርቦት (አክሰስ ቱ ፋይናስ) ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ በአጭር ጊዜ ባንፈታውም ቢያንስ አንድ አማራጭ ሆነን እንድንገኝ ነው ኃላፊነት የተሰጠን፤›› ብለዋል፡፡

በቀጣይ ይፋ የሚደረጉ በርካታ መመርያዎች እንደሚኖሩ ተገልጾ፣ እነዚህ መመርያዎች በገበያው ላይ የሚሳተፉ አገልግሎት ሰጪዎችን በተመለከተ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎትና የመነሻ ካፒታል በምን ዓይነት መንገድ ነው መመዝገብ ያለባቸው የሚሉትን የሚመለከቱ እንደሚሆኑ፣ በቅርቡ ቦርዱ ሲያፀድቀው ወይም በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ሳምንታት ለሕዝብ ውይይት የሚቀርብ ይሆናል ተብሏል፡፡

እንደ ብሩክ (ዶ/ር) ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንቨስትመንት ባንክ የለም፡፡ ባለሥልጣኑ አንደኛው ኃላፊነቱ የኢንቨስትመንት ባንኮችን (የአገር ውስጥ፣ የውጭ የሚቋቋሙትን) ፈቃድ መስጠት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ ከፍተኛ ዝግጅትን የሚጠይቅና በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋለ አዲስ ገበያ በመሆኑ፣ ሐሳብ ላይ ያለውን የካፒታል ገበያ ከማቋቋም ባለፈ በቀጣይ ዝርዝራቸው የሚገለጹ ድርጅቶችን የመደገፍና የማብቃት ተግባር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተለምዶ ባንኮች የሚያቀርቡት ብድር ማስያዣ (ኮላተራል) የሚጠይቅ፣ የአጭር ጊዜ ነገር ግን ረዥም የመመለሻ ጊዜና ወለድ የሚሰላበት ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ አንዱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ ድርጅቶች እንዴት አድርገው የኮርፖሬት ቦንድ (የመንግሥት ቦንድን ጨምሮ) አቅርበው ትርፋቸውን በጠበቀ ሁኔታ ሥራቸውን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይችላሉ የሚለው የመጀመርያው ነው ተብሏል፡፡

አንድ ድርጅት የኮርፖሬት ቦንድ ለማኅበረሰቡ ለመሸጥ ሲነሳ ቅድሚያ የሚያስፈልጉ የማዘጋጃ ሥራዎች ሲኖሩ፣ ከዚያም ውስጥ ለምሳሌ የአይኤፍአርኤስ ቅድመ ሁኔታ ተጠቃሽ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለምን ማቋቋም አስፈለገ፣ እንዴትስ የገበያው ተዋናይ መሆን ይቻላል?

በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ (ሲኒየር ሌጋል አድቫይዘር) በመሆን እየሠሩ የሚገኙት ወ/ት ሐና ተድላ፣ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በማድረግ በተቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ግብይትን የሚያቅፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ አክሲዮንን ብቻ ሳይሆን ቦንድንና ሌሎች ‹‹ኢንስትሩመንቶችን›› እንደሚያካትት ያስረዳሉ፡፡

የካፒታል ገበያ ግብይት ብቻ ሳይሆን ካፒታል ማሰባሰብን (ካፒታል ፈንድ ሬይዚንግንም) እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመጀመርያ ገበያ (አዲስ ካፒታል የሚሰበስብ) እና ሁለተኛ ደረጃ  ወይም ግብይት የሚሉ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ በተጨማሪም ሰነድ መዋዕለ ንዋይ ሲባል ከ12 ዓመት በላይ የሆነ ሰነድን የሚመለከት መሆኑን ከፍተኛ የሕግ አማካሪዋ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡

የካፒታል ገበያ ካስፈለገባቸው ጉዳዮች አንዱ ገንዘብ የሚውልበትን ሌላ አማራጭ እንዲሰጥ ሲሆን፣ ይህም ለኢንቨስተሮች ሥጋቶችን የሚቀንስ፣ ለኩባንያዎችና ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ተጨማሪ የፋይናንስ ጥቅም እንዲያገኙ ወይም የባንክ ብድር ዓይነት ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል። በሌላ በኩል መንግሥትን በፋይናንስ ምንጭነት የሚጠቅም (በመንግሥት ቦንድ)፣  የገንዘብ ፖሊሲን ለማጠንከርም የሚረዳ ይሆናል ተብሏል፡፡

የካፒታል ማርኬት ተሳታፊ የሚባሉ ደላሎች፣ ነጋዴዎች፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ አካውንቶች የፈንዱን ፍሰት የሚያግዙ ተዋንያን ናቸው፡፡ የተቀላጠፈ የካፒታል ገበያ ዕውን የሚሆነው በቴክኖሎጂ በታገዘ የመሠረተ ልማት አማካይነት ሲሆን፣ ለዚህም ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ  ነገሮች የመጀመርያው የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓትን የሚጠቀም የግብይት መድረክ ነው፡፡ 

ካፒታል ገበያ ሲታሰብ በአንድ አፍታ የሚጀመር ሳይሆን በሒደት እየተገነባ የሚሄድ ነው፡፡ ዕድገቱም ሲታሰብ የሚጤኑ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የፖሊሲ ጉዳዮች፣ የአከፋፈቱ ሒደት፣ የአሳታፊነቱ፣ የገበያ መሠረተ ልማት፣ የአቅም ግንባታና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ካሉ ከፍተኛ የሕግ አማካሪዎች አንዱ አቶ ሰለሞን ዘውዴ ሲሆኑ፣ በአዋጁ መሠረት እንዴት ወደ እዚህ የገበያ አማራጭ መቀላቀል ይቻላል? በሚለው ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ 

አዋጁ ወደዚህ ገበያ ለመቀላቀል ሁለት ዓይነት መንገዶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ አንደኛው ድርጅቶች የያዙትን ሰነድ መዋለ ነዋይ ለሕዝብ ሽያጭ ማቅረብ (ፐብሊክ ኦፈር) የሚችሉበት ነው። በዚህም መሠረት ኩባንያዎች ተሰባስበው ድርሻዎችን አቅርበው ገበያውን የሚቋቋሙበት አማራጭ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የተመሠረተ የአክሲዮን ማኅበር ወይም ሕጋዊ ዕውቅና ኖሮት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ኩባንያን የሚመለከት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚቋቋመው የካፒታል ገበያ ሁለቱንም ያካተተ ነው፡፡ 

ለሕዝብ ሽያጭ ማቅረብ (ፐብሊክ ኦፈር) ሒደት ሲኖር በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚደረገው የምዝገባ ሒደት አብሮ የሚተገበር ሌላው ሒደት ነው፡፡ እዚህ ሒደት ላይ አንድ ኩባንያ ለገበያ ከመቅረቡ በፊት ለኢንቨስተሩ የጠራ መረጃ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ 

አቶ ሲራክ ሰለሞን ሌላው በባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሕግ አማካሪ እንዳስረዱት፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ በካፒታል ገበያ ውስጥ ዕውን የሚሆኑን አልግሎቶች የሚሰጡ አካላት በአገር ውስጥ የሉም፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ጨርሶ አይኖሩም ማለት ስላልሆነ ባለሥልጣኑ ባዘጋጀው መመርያ ላይ ታሳቢ ያደረገው ኢትዮጵያውያን በዋነኛነት ይህንን ሥራ እንዲሠሩት ነው፡፡ 

ቁጥራቸው 12 የሚደርሱ መመርያዎች በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ የሚደረጉ ሲሆን፣ ከአንድ ተቋም የተዘጋጁ እንደመሆናቸው መመርያዎቹ እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው ተብሏል፡፡ 

በአዋጁ ስምንት የአገልግሎት ሰጪዎች የተለዩ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ በየጊዜው አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውንና ይህንን ሊሠሩ ይችላሉ የሚባሉ አገልግሎት ሰጪዎችን በመለየት 15 ተዋንያን እንዲዘረዝሩ ተደርጓል፡፡ ለአብነትም ንግድ ተብሎ በተለየው ላይ አገናኝ አካል (ደላላ)፣ ‹‹ዲለር›› ያካትታል፡፡ 

በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የማክሮ ፋይናንሺያል አማካሪ የሆኑት አቶ አምባዬ መርጋ እንደሚያስረዱት፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች ከሚባሉት ውስጥ ቺፍ አካውንታት፣ የውስጥና የውጭ ኦዲተሮች፣ የኢንቨስትመንት አማካሪዎችና ሌሎችም ሪፖርት በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የሚኖራቸው ሚና የሚጠቀሙባቸውን ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሕጎችን ይጠቅሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከ100 በላይ አባላት ያሉት፣ የዓለም አቀፍ ሴክዩሪቲ ሬጉሌተርስ ኮሚሽን (አይኦስኮ – IOSCO) አባል የሚሆን ሲሆን፣ ይህም ቁጥራቸው በተገለጸው አገሮች የሚተገበረውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውንና ተዓማኒ ነው የሚባለውን የአካውንቲንግና ኦዲቲን ስታንዳርድ እንዲከተል የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የካፒታል ገበያ ማቋቋም ሲነሳ ከሚታሰቡ ጉዳዮች ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ተዋንያን የሚቀርብላቸው የግብይት አማራጭ ትክክለኛ የፋይናንስና የሪፖርት አቀራረብ አንዱ በሥጋትነት የሚነሳ መሆኑ ይገለጻል፡፡

በተለይም እስካሁን እንደ አይኤፍአርኤስ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓቶቹ ሙሉ በሙሉ ባልተተገበረበት አገር ውስጥ ለግብይት የሚቀርቡ ድርጅቶችን የኦዲት ጥናት አከናውኖ ወደ ግብይት ማቅረብ ፈታኝ መሆኑ የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ዕውን በማድረግ ጉዞ ውስጥ እንደ ችግር ከሚነገሩ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሹ መሆኑን የማክሮ ፋይናንሺያል አማካሪው ተናግረዋል፡፡ 

በአንድ አገር የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሲቋቋም አብሮት ሕጋዊነቱን የሚቆጣጠር የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ (የሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን) ይመሠረታል፡፡ በኢትዮጵያም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ በካፒታል ገበያ ውስጥ የሚሳተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዋጋ ባለው መንገድ ሳይጭበረበሩ ግብይቱ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበትን መንገድ ያመቻቻል (ይቆጣጠራል) ሥልጠናና ትምህርቶችንም መስጠት ሌላው ተልዕኮ ነው፡፡

የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ አክሲዮኖች ለመሸጥና ለመግዛት ብሎም ለማቅረብ ተፈላጊውን መሠረተ ልማት (ቴክኖሎጂ) የሚያቀርብ ነው፡፡ አገናኝ ወይም ገበያ ቦታ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል መሆኑን የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት አቶ ሚካኤል ሀብቴ ይገልጻሉ፡፡  

የሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ በአዋጁ እንደተቀመጠው የሚጀመረው እንደ አክሲዮን ገበያው ሆኖ፣ በመንግሥት በሚወክለው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ 25 በመቶ ድርሻ፣ እንዲሁም 75 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥና በውጭ ኢንቨስተሮች ድርሻ ይዘው እንደሚጀመር ተገልጿል። 

የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመክፈት ብቁ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት  ማቋቋምን ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ በሚፈልገው መንገድ ከመመርያ ዝግጅት ጀምሮ ተቋሙን ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች የማደራጀት ሥራ እየሠሩ እንደሆነ  የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ብሩክ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

‹‹የካፒታል ገበያ ብቻውን ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ የካፒታል ገበያው ዋናው ተዋንያን የንግድ ማኅበረሰቡና ኢንቨስተሩ ነው የሚሆነው፡፡ ኢንቨስተሩ የንግድ ማኅበረሰቡ ላይ እምነት ካለው፣ ባለሥልጣኑ ከሚዘረዘሩት ድርጅቶች ጋር አብሮ ተባብሮ መሥራት ከቻለና ብቁ የሆነ ገበያ መፍጠር ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬያማ የሆነ የካፒታል ገበያ መመሥረት ይቻላል፤›› ብሩክ (ዶ/ር) የሚያቀርቡት ሐሳብ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፣  የካፒታል ገበያ መመሥረት ለንግዱ ማኅበረሰብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ካፒታል በማመንጨት፣ የገንዘብ ፍሰት በመፍጠርና የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች