የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው መሬት በመቆጣጠር ጥቃት የሚያደርሱ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንቅስቃሴን አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ጥረት አድርጎ እንዲያስቆም ተጠየቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተወክለው የመጡ አንድ የምክር ቤት አባል፣ በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ያለው ድንበር ክፍት በመሆኑ ምክንያት ቀጣናው ለጦር መሣሪያ ዝውውር መዳረጉን ገልጸው፣ በአካባቢው ባለው የሰላም ችግር ምክንያትም በክልሎቹ ድንበር አካባቢ ያለው የተፈጥሮ ሀብቶችንና ማዕድናትን ለልማት ማዋል አልተቻለም ብለዋል፡፡
ጥያቄውን ያነሱት የምክር ቤት አባል፣ ‹‹እኔ ከዚያ አካባቢ ስለመጣሁ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም መልስ ልናገኝ አልቻልንም፣ ጥያቄው ግን ለብዙ ዓመታት የቆየ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገኦ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከቀናት በፊት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ወደ ተባለው ቦታ ለመስክ ምልከታ መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም አካባቢው ከዚህ በፊት የአገር መከላከያ ሠራዊት የነበረበት ቢሆንም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከደቡብ ሱዳን የተደራጁ ኃይሎች እስከ 80 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ጥቃት እያደረሱ መሆናቸውን፣ ለመስክ የሄዱ አባላትን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ጉዳዩን ከድንበር አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ ለመስጠት ለምን አልተቻለም በማለት የጠየቁት ዲማ (ዶ/ር)፣ በቀጣይ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የደረሱበትን የዳሰሳ ጥናት ውጤት ለሚኒስቴሩ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
የተነሳውን ጥያቄ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ‹‹ከአንድና ከሁለት ወራት በፊት በቦታው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍንና የድንበር ሁኔታውን በተመለተ በተደረገ ጥናት መሠረት የደረሰኝ ሪፖርት የሚያሳየው፣ የነበረው ሁኔታው መሻሻሉን ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከደቡብ ምዕራብ ክልል ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የተላከልኝ ሪፖርት ሁኔታዎች መሻሻላቸውን የሚገልጽ ሲሆን፣ ነገር ግን ምናልባት አሁን አዲስ ክስተት ከተፈጠረ ነገሮች ሊለወጡ ስለሚችሉ መረጃውን ወስደን መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት ያደርጋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በዚህ አካባቢ ያለውን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት ከሁሉም አዋሳኝ አገሮች ድንበር ጋር ያለውን መረጃና ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ የፕሮጀክት ቢሮ እየተደራጀ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደመቀ፣ በቀጣይ በግምገማው መረጃ መሠረት የድንበር ጉዳይ በዘላቂነት እንዲፈታ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡