የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ነባር ኢንቨስትመንታቸውን የሚያስፋፉ ባለሀብቶች ከንግድ ትርፍ ግብር ነፃ መብት እንዲያገኙ የሚፈቅድ አዲስ መመርያ አወጣ፡፡
በወጣው መመርያ መሠረት ነባር ድርጅትን የማስፋፋት ወይም የማሻሻል ሥራ ያከናወነ ድርጅት፣ ከንግድ ትርፍ ነፃ የመሆን መብት ተጠቃሚ የሚሆነው፣ የነባር ድርጅቱን የማምረት ወይም አገልግሎት የመስጠት ዓቅም ከ50 እስከ 90 በመቶ በላይ የሚያሳድግና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ቁጥር 517/2014 በሰፈረው ሰንጠረዥ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ በዕድገቱ ምክንያት ባገኙት ገቢ መሠረት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በመመርያው የማምረት ወይም አገልግሎት የማሳደግ አቅማቸው ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ነባር ድርጅቶች፣ በደንቡ ላይ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ በዕድገቱ ምክንያት ባገኙት ገቢ ላይ ሊከፈል ከሚገባው የንግድ ትርፍ ግብር 60 በመቶ፣ ከ71 እስከ 90 በመቶ ድረስ የሚያሳድጉ ድርጅቶች 80 በመቶ፣ እንዲሁም ከ90 በመቶ በላይ የሚያሳድጉት ደግሞ መቶ በመቶ ከገቢ ግብር ነፃ የመሆን መብት እንደሚሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡
በነባር ድርጅት አዲስ የማምረቻ ወይም የአገልግሎት መስጫ መስመር በመጨመር ምርትን ወይም አገልግሎትን በዓይነት ወይም በመጠን ቢያንስ መቶ በመቶ የሚያሳድግ ኢንቨስተር፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ሰንጠረዥ ላይ ለተጠቀሰው ጊዜ በማሻሻያው ምክንያት በተገኘው ገቢ ላይ ከንግድ ትርፍ ግብር ነፃ የመሆን መብት እንደሚያገኝ መመርያው ላይ ሰፍሯል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 517/2014 መመርያ እንዲወጣ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የኢንቨስትምንት ማስፋፊያ/ማሻሻያና ማበረታቻ አፈጻጸም መመርያም በዚያ መሠረት ተዘጋጅቷል፡፡
የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ቁጥር 517/2014 ክፍል ሁለት ከገቢ ግብር ነፃ የመሆን ማበረታቻ በሚለው ድንጋጌ ላይ ማበረታቻ በሚያስገኝ መስክ ነባር ኢንቨስትመንቱን ያስፋፋ ወይም ያሻሻለ ባለሀብት፣ ከማስፋፊያው ወይም ከማሻሻያው የሚያገኘው ተጨማሪ ገቢ በደንቡ ላይ የቀረበውን ሠንጠረዥ መሠረት በማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት ከገቢ ግብር ነፃ የመሆን መብት ያገኛል፡፡
ማንኛውም ኢንቨስተር ከንግድ ትርፍ ግብር ነፃ የመሆን መብት ተጠቃሚ ለመሆን ድርጅቱ ቢያንስ ለ36 ወራት በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የቆየ መሆኑን በማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ነባሩን የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ሥራ ለማስፋፋት፣ የአመራረት ዘይቤውን ለማዘመን፣ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ወይም የምርትና አገልግሎቱን ዓይነት ለማብዛት ያዋለውን መዋዕለ ንዋይ የሚያሳይ በውጭ ኦዲተር የተረጋገገጠ የሒሳብ ሪፖርት ማሟላት ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
በመመርያው ላይ እንደሰፈረው የግብር ዕፎይታ ተጠቃሚ የሆነ ባለሀብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ፣ የተሰማራበትን ኢንቨስትመንት ዘግቶ ተመልሶ የዕፎይታ ጊዜ በሚያሰጥ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማራ፣ በዘጋው ኢንቨስትመንት የተጠቀመበትን የዕፎይታ ለሚያህል ጊዜ ከንግድ ትርፍ ግብር ነፃ የመሆን ማበረታቻ ተጠቃሚ አይሆንም፡፡
ለማስፋፊያ ወይም ለማሻሻያ የሚሰጠው ማበረታቻ ተፈጻሚነት መቆጠር የሚጀምረው፣ ባለሀብቱ በማስፋፊያው ምክንያት ካፒታሉን በማሳደግ የተሻሻለውን የንግድ ሥራ ፈቃድ ከወሰደበት ቀን ጀምሮ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የማስፋፊያ ሥራ የሚያከናውን ባለሀብት ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ የመሆን መብት ተጠቃሚ ለመሆን የሚችለው፣ ሊደረስበት የሚችል የነባር ድርጅቱን የማምረት ወይም አገልግሎት የመስጠት አቅም ቢያንስ 50 በመቶ ወይም መቶ በመቶ በዓይነት ለማሳደግ የተዘጋጀ መሆኑን የሚያሳይ ዕቅድ ሲያቀርብ መሆኑን መመርያው ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ባለሀብቱ ባቀረበው ዕቅድ መሠረት የማስፋፋት ሥራውን ካላከናወነ፣ ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ተደርገው ወደ አገር ባስገባቸው ዕቃዎች ቀረጥና ታክስ እንደሚከፍል ተገልጿል፡፡