የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክልሎች ከሕግ አግባብ ውጪ ወደ ጎረቤት አገሮች ገበያ በሚላክ የጫት ምርት ላይ ቀረጥ እያስከፈሉ በመቸገሩ፣ ፓርላማው ለመፍትሔው ትብብር ያድርግልኝ ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡
ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በተለይም ጫትን የኦሮሚያ፣ የሐረሪና የሶማሌ ክልሎች ቀረጥ እያስከፈሉ ምርቱ ከአገር ሳይወጣ ወደ ውጭ ተልኮ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ገንዘብ፣ እዚሁ ተበልቶ እያለቀ መሆኑን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጐፌ ለፓርላማ አስረድተዋል፡፡
ነጋዴዎች ማትረፍ ቀርቶ ዋናውን የመሸጫ ዋጋ እንኳ መመለስ ባለመቻላቸው፣ በሕገወጥ መንገድ ጢሻ ለጢሻ በኮንትሮባንድ የሚያስወጡበት ዋናው ሚስጥር ይኼ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የዚህ ዓይነቱ አሠራር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚጎዳ በመሆኑ ምክር ቤቱ ‹‹ሊያግዘን ይገባል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹በእኛ በኩል ያለው አቋም ማንኛውም ወደ ውጭ የሚላክ ምርት ቀረጥ ሊከፈልበት እንደማይገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአገሪቱ የፖሊሲ ማዕቀፍ ወደ ውጭ የሚላኩ ማናቸውም ምርቶች ቀረጥ ሊጣልባቸው እንደማይገባ የሚገልጽ በመሆኑ፣ ይህ ተግባራዊ እንዲደረግ ለክልሎች በተደጋጋሚ ደብዳቤ መጻፋቸውንና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይህንኑን ጉዳይ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ችግሩ እንዲፈታ አቅጣጫ አስቀምጦ እየተንቀሰቀሰ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ችግሩ ከፓርላማው አቅም በላይ ስለማይሆን የእናንተ ክትትል ያስፈልገናል፤፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ለእኛም ራስ ምታት የሆነ ጉዳይ ነው፣ አካባቢያዊ ልማትን ብቻ በማየት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና የአገር ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል መሆን የለበትም የሚለው የእኔም የመሥሪያ ቤቴም አቋም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
አቶ እስክንድር አሊየ የተባሉ የፓርላማ አባል ጫትን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ ቀረጥ ከከፈሉ በኋላ ለፌደራል መንግሥቱ በድጋሚ ቀረጥ እንደሚከፍሉ በመግለጽ፣ በተመሳሳይ ምርት በአንድ አገር ውስጥና በአንድ የታክስ አዋጅ ሁለት ጊዜ ቀረጥ እንዲከፍሉ መደረጉ ምን ዓይነት አሠራር ነው በማለት ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከጫት ጋር በተያያዘ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር መንግሥት ከሁለት ወራት በፊት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካካል፣ ከአምራቾችና ከአከፋፋዮች ጋር ምንም ዓይነት ምክክር ሳይደረግ የአገር ውስጥ የጫት ንግድ እንዲቆም በመወሰኑ በምሥራቅ ሐረርጌ 447 የጫት አቅራቢ ማኅበራትና 150 ሺሕ ወጣቶች ሥራ አቁመዋል ብለዋል፡፡
አቶ ካሳሁን የጫት ነጋዴዎችን መታገድ አስመልክተው ሲያብራሩ፣ ነጋዴዎቹ የተሰጣቸውን የንግድና የመላኪያ ፈቃድ ራሳቸው መጠቀም ሲገባቸው ሲሸጡና ሲያከራዩ 42 ነጋዴዎች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የተፈቀደውን በዱቤ የመሸጥ ፈቃድ ተጠቅመው ወደ ውጭ ከላኩ በኋላ፣ ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወደ አገር ቤት ያላስገቡ መኖራቸውንና ገንዘቡን ያስቀሩ 32 ነጋዴዎች ንግድ ፈቃዳቸው መታገዱን ገልጸው፣ ገንዘቡን እንዲያስገቡ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የጫት ንግድ ፈቃድ የተሰጣቸው 4,000 ያህል ቢደርሱም፣ በአሁኑ ጊዜ ጫት ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩት ከ500 እንደማይበልጡና አንዳንዶች ስለጫት ንግድ ምንም ዕውቀቱ እንደሌላቸው፣ የንግድ ፈቃዱን አዲስ አበባ ተቀምጠው በማከራየት በሕገወጥ መንገድ የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው አክለው አስረድተዋል፡፡
ለአገር ውስጥ ይቀርብ የነበረ ጫት መቋረጡን በተመለከተ ለቀረባላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ለሶማሌ ክልል ይላካል በሚል ዞሮ ወደ ውጭ ይላክ የነበረ የጫት ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ተጠንቶ የብሔራዊ ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ከአንድ ሳምንት በፊት በወሰነው ውሳኔ መሠረት፣ በሶማሌ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ጫት ተጠቃሚ ነው በሚል በቀን 17 ሺሕ ኪሎ ግራም እንዲገባ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡