Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ውህደት የሚተገበርበትን ሕግ ሊያወጣ ነው

ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ውህደት የሚተገበርበትን ሕግ ሊያወጣ ነው

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ውህደት አተገባበርን የተመለከተና ሌሎች አዳዲስ መመርያዎችን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ሁለት ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ያለባቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ሰለሞን ከባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ ባንኩ ከሪፎርም ሥራዎች ጋር በተያያዘ እያዘጋጃቸው ካሉ የተለያዩ መመርያዎች ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ተቋማት ውህደት አተገባበርን የሚመለከት መመርያ ይገኝበታል፡፡ ወደፊት የፋይናንስ ተቋማት ውህደት ያደረጋሉ በሚል አተገባበሩን የሚገዛ መመርያ ከወዲሁ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ባንኮች ወደ ውህደት ለመግባት ውስጥ ውስጡን እየተነጋገሩ ሲሆን፣ በይፋ መዋሀድ የሚፈልጉ ባንኮች እንዳሉ እየተጠቀሰ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ መመርያ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ታምኗል፡፡   

ከዚህ መመርያ ዝግጅት ሌላ የፊንቴክ ዘርፉን ለመክፈት የሚያስችል መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው መመርያ ደግሞ የነፃ የንግድ ቀጠናን የተመለከተ መመርያ ነው፡፡ ይህም የድሬዳዋ የነፃ የንግድ ዞን ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እንዴት መሥራት እንደሚችሉ ለመወሰን እየተዘጋጀ ያለ መመርያ መሆኑን ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍና በተለያዩ መመዘኛዎች ውጤታማ ቢሆኑም በዘርፉ የገንዘብ እጥረት (የሊኪውዲቲ) ችግር ያለበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ሁለት ባንኮች በገንዘብ እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑም በፋይናንስ ተቋማት ተግዳሮት ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል፡፡

የዘርፉን የ2015 የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው፣ በዘርፉ አሉ ተብለው ከማጠቀሱት ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ የገንዘብ እጥረት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ባቀረቡት ሪፖርት፣ በዘርፉ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው ተብሎ ሲታይ አንደኛው ሊኪውዲቲ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ችግር ሁሉም ባንኮች ላይ አለ ሊባል ቢችልም አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት ባንኮች ላይ የሊኪውዲቲው ችግር አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ ስለመደረሱ ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምክትል ገዥው የእነዚህን ሁለት ባንኮች ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ የገንዘብ እጥረት ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው ታክስ መክፈያ ጊዜና ከፍተኛ የውጭ ንግድ በሚካሄድበት ወቅት (በኤክስፖርት ሲዝን) እንደሚሆን አስታውሰው እንዲህ ያለው ጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ ግን ከብሔራዊ ባንክ በቅናሽ የመበደር ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የዘንድሮ ለየት ባለ ሁኔታ የገንዘብ እጥረት በመታየቱ ባንኮች ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር በአግባቡ ማስተዳደር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ባንኮች የውጭ ክፍያዎችን በአግባቡ የመክፈል ችግርን ከገንዘብ እጥረት ጋር የሚያያዙ መሆናቸው ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ መክፈል የነበረባቸውን ክፍያ ይዘው መቆየታቸው ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ሰዎች (ከኩባንያዎች) ገንዘባቸውን ለማግኘት ብዙ እየተቸገሩና አቤቱታቸውን ይዘው ለብሔራዊ ባንክ እስከማመልከት እየደረሱ በመሆኑ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር መውጣት እንደሚገባ አቶ ሰለሞን አሳስበዋል፡፡

ክፍያን ማዘግየት ከገንዘብ እጥረት ጋር የተያያዘ ብቻ ያለመሆኑንም በማስታወስ ባንኮች ክፍያዎችን በአግባቡ መክፈልና ሊኪውዲቲ ማኔጅመንት ላይ ጥብቅ ሆነው እንዲሠሩ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክም ከዚህ በኋላ በዚሁ ጉዳይ ላይ አጥብቆ የሚሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ወስዶ አለመሠራት ባልታሰበ ሰዓት ኪሳራ (ባንክራብሲ) ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡

ከብድር አሰጣጥ ረገድም ባንኮች እየታየባቸው ያሉ ችግሮችንም የጠቃቀሱ ሲሆን፣ ብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ችግሮች እየታዩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ብድር ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ጉዳይ መሆን አለበት ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ከብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከታዩ ችግሮች መካከል አንዱ ብድሩ ለታሰበለት ዓላማ መዋል አለመዋሉን ክትትል አለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ረገድ ያጋጠሙ ነገሮች እንዳሉም ያመለከቱት ምክትል ገዥው፣ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት አንዳንድ ተበዳሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ለተፈለገው ዓላማ ሳይውል አክሲዮን የገዙበትን ሁኔታ መመልከታቸውን ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...