Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የታክስ ይግባኝ መዝገቦች በተያዘላቸው ጊዜ ውሳኔ እያገኙ ባለመሆናቸው በኮሚሽኑ ላይ ትችት ቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ለውሳኔ ቀጠሮ የተያዘላቸው መዝገቦች ውሳኔ አሰጣጥ መዘግየት ጋር በተያያዘ በተገልጋዮቹ ትችት ቀረበበት፡፡

በ2015 ዓ.ም. በግማሽ ዓመት ውስጥ የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው ስብሰበ፣ የችሎት ሰዓት አለመከበርና ቀጠሮ በተያዘላቸው መዝገቦች ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ አለመሰጠቱ ተገልጋዮችን እያማረረ መሆኑ በሰፊው ተነስቷል፡፡

የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው የውሳኔ ቀጠሮ የተያዘላቸው መዝገቦችም ከስድስት ወራት በላይ የዘገዩበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቅሰው፣ በተገልጋዮች የሚነሳው ትችት ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ 1,127 ተገልጋዮች በኮሚሽኑ አሠራር አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ 1086 የሚሆኑት ግን ኮሚሽኑ የሚሰጠው አገልግሎት ጥሩ መሆኑን፣ 41 ተገልጋዮች ደግሞ በኮሚሽኑ የችሎት ሰዓት ላይ ችግር እንዳለ፣ የመዛግብት የውሳኔ ቀጠሮ እየተከበረ አለመሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመስከረም ወር ውሳኔ ማግኘት ያለባቸው መዝገቦች ወደ ኅዳር፣ በኅዳር ውሳኔ ሊሰጣቸው የሚገባ መዝገቦች ወደ ታኅሳስ ወር እየተላለፉ እንደነበር የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ በግማሽ ዓመቱ የታየው የሥራ አፈጻጸም ጥሩ ቢሆንም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳ ኮሚሽኑ በውሳኔ አሰጣጥ ጥራት ላይ ችግር ባይኖርበትም፣ በወቅቱ ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ግን ክፍተት እየተስተዋለበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ውሳኔ የሰጠባቸው አብዛኞቹ መዝገቦች በፍርድ ቤት ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ በአሠራር ጥራት ላይ ግን እንከን እንደሌለም አክለዋል፡፡

‹‹በ2015 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ወደ 316 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥተን 171 መዝገቦች ላይ ይግባኝ ተጠይቆብናል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት አይቶ ወደ እኛ የመለሳቸው 19 መዝገቦች ብቻ ናቸው፡፡ ከተመለሱ 19 መዝገቦች ውስጥ አራቱን ብቻ ነው ያየነው፡፡ አንዱ ፀንቶ የመጣ ሲሆን፣ ሦስቱ ግን እኛ የወሰነውን ውሳኔ የማያስቀይር አይደሉም ብለን ደግመን ነው የወሰነው፡፡ 15 በሒደት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ውሳኔያችን ጥራት አለው ማለት ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ተገልጋዮች በታክስ ቅሬታ ለኮሚሽኑ ካቀረቧቸው 654 መዝገቦች፣ በግማሽ ዓመቱ 316 መዝገቦች ላይ ውሳኔ እንደተሰጠና 354 መዝገቦች በሒደት ላይ መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተነግሯል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ውሳኔ የተሰጠባቸው 316 መዝገቦች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳላቸው፣ የኮሚሽኑ ፕላንና ለውጥ ማስተባበር ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡ 

በተቀጠሰው ጊዜ 654 መዝገቦች ለኮሚሽኑ ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ የታሰበው ለ320 ብቻ እንደነበር፣ ከእነዚህም መካከል አራት መዝገቦች በታቀደው መሠረት ውሳኔ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ አራት መዝገቦች በተያዘላቸው ቀጠሮ ውሳኔ ማግኘት የነበረባቸው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየታቸውን አስረተዋል፡፡ 

ወደ ኮሚሽኑ በአካል ሄደው ቅሬታቸውን ከሚያቀርቡ ተገልጋዮች በተጨማሪ፣ ሌሎችም በ30 ቀናት ውስጥ ማመልከት አለመቻላቸው የተገልጋዮች ተደራሽነት ውስንነት እየተስተዋለበት በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ በሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ዳታ ቤዝ በመገንባት 250 ተገልጋዮች ቅሬታቸውን በኦንላይን ማሳወቃቸውን አቶ ኢዮብ ገልጸዋል፡፡

በታክስ ቅሬታ መዛግብቶች አሠራር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሰፊው የተወያዩት የኮሚሽኑ ሠራተኞችም፣ የተስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ መሥራት እንዳለባቸው አቅጣጫ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች