Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየፖለቲካ ሰላማችን እንደምነው? ሰዓቱስ ምን ይላል?

የፖለቲካ ሰላማችን እንደምነው? ሰዓቱስ ምን ይላል?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሰላማችን፣ ደኅንታችንና ሁለመናችን በዓለም ደረጃም የሚያሳስብ ደረጃ ላይ የደረሰው ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአቅሟ ብቻ ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚና ከአቅሟና ከድርሻዋ በላይ ለዓለም ሰላም፣ ለዓለም ኮሌክቲቭ ሴኪዩሪቲ፣ ለዓለም ማኅበር ታሪክ የመዘገበው ሚና ተጫውታለች፣ አስተዋጽኦም አበርክታለች፡፡ የዓለም ሰላም ግን የሚታገሉለትንና የሚያውቁትን ያህል እንኳን አበረታች ነገር እያስመዘገበ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰዓቱ የሚነግረን የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ሰዓት ሰባ ዘጠኝ ዓመት የሞላው የዱምስደይ ወይም የምፅዓት ቀን፣ የዕለተ ደይን ወይም የቂያማ ቀን ሰዓት ይባላል፡፡ የዚህ ሰዓት ባለ አደራ፣ ጠባቂና ተጠባባቂ የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡለቲን የተባለ የኅትመት ተቋም ነው፡፡ ይህን የመሰለ ከቡለቲን፣ ከሚዲያ ተቋም፣ ከሚዲያ ውጤት በላይ የሆነና ይህን ያህል የመታመን ብቃት የተጎናፀፈ እ.ኤ.አ. በ1945 የመሠረቱት ከአልበርት አንስታይን ጋር የማንሃታን ፕሮጀክት ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ ማንሃታን ፕሮጀክት ማለት የመጀመርያውን የኑክሌር የጦር መሣሪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሠርቶ ያወጣ የ‹‹ሪሰርችና ዴቨሎፕመንት›› ሥራ የቤት ወይም የሚስጥር ስም ነው፡፡

ከ1939 ዓ.ም. ጀምሮ ቀስ ብሎ እያደገና እየተመነደገ በሄደ የሰው ኃይልና በጀት እየታቀፈና እየተደገፈ መጥቶ 130 ሺሕ ሰው ያሰማራው፣ በዚያው ጊዜ ወጪ ሁለት ቢሊዮን ያህል ዶላር (በዛሬው ሒሳብ 23 ቢሊዮን ዶላር) የተከሰከሰበት ፕሮጀክት የሥራ ፍሬ ወይም ምርት መጀመርያ  ላይ ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 3 ቀን ሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ‹‹ሲመረቅ›› 226 ሺሕ ሕዝብ አርዶ ነው፡፡ እዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የተሳተፉ ሳይንቲስቶች ግን፣

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የሳይንስ ጥበብ ተመነደገ

ደስታ ምቾት ብዙ አደገ

የጥበብ ሥራ ነው ድግሡ

ኩራዝ ቀረ ከእነ ጭሱ››፣ ወዘተ ብለው ‹‹አልጨፈሩም›› ወይም ዝም ብለው ቁጭ አላሉም፡፡ በተቃራኒው የሰው ልጅ ደኅንነት፣ የሰው ልጅ ደኅንነት ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ያለውና የሚገኘው ሕይወት (ኦርጋናይዝድ ላይፍ) ራሱ አደጋ፣ ጥፋትና እልቂት ላይ ወድቋል፡፡ ይህንን መቀበልስ ካልተቻለ ጥያቄው መቼ እንጂ፣ እውነት ነው ውሸት አይደለም ብለው መለፈፍ፣ ማሳየትና መጻፍ ጀመሩ፡፡ የሳይንቲስቶች ቡለቲን የሚባለው ይህ የሚዲያ ተቋም በዚሁ ምክንያት ይበልጥ የሚታወቀው ቡለቲኑ (ይፋዊ ኅትመት) ላይ ከ1947 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ በሚወጣው ሰዓቱ ነው፡፡ 13 የኖቤል ሎሬቶች ጭምር የሚያካትተው በኑክሌር ቴክኖሎጂና በአየር ንብረት ሳይንስ አንቱ የተባሉ ሳይንቲስቶችና ሎሎች ኤክስፖርቶች የሚገኙበት የሳይንቲስቶች ቦርድ በየዓመቱ ሰዓቱን ይወስናሉ፡፡ የዘንድሮው የ2023 ሰዓት ስንት ይላል? ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለፈው ማክሰኞ ይፋ በተደረገው በእነዚህ ሳይንቲስቶች ውሳኔ መሠረት፣ የዚህ ዓመት ሰዓት 23፡58፡30 ላይ ያሳያል፣ ለመንፈቅ ሌሊት ዘጠና ሰከንድ ጉዳይ፡፡ ዓለም መንፈቀ ሌሊት የደፍ ኬላ አካባቢ ወይም እዚያ አጠገብ በ90 ሰኮንዶች ልዩነት/ርቀት ላይ ብቻ ትገኛለች ማለት ነው፡፡ ‹‹A time of unprecedented danger, it is 90 seconds to midnight›› ይላል፡፡ ታይቶም፣ ተሰምቶም፣ ታልሞም፣ ተፈርቶም የማይታወቅ አደገኛ ወቅት/ጊዜ ላይ ነን፡፡ ለምፅዓት ቀን፣ ለዕለተ ደይን፣ ለቂያማ ቀን፣ ቂያማ ለሚቆምበት ዕለት ዘጠና ሰከንድ ጉዳይ ነው፡፡ ዘንድሮ በ2023 ይህ አዲስ ዓመት በባተ/በገባ በ24ኛው ቀን ባለፈው ሳምንት እንደተነገረን፣ ከዓምና (ከ2022) ሰዓቱ በአሥር ሰከንድ ወደ ዕልቂቱ እየተንፏቀቀ አይደለም እያጣደፈን ነው፡፡ ሰዓቱ ይህን ይላል፡፡

ችጋጎ ዩኒቨርሲቲ (University of Chicago) የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡለቲን ቢሮ ውስጥ የሚገኘው/የሚኖረው ሰዓት በኢትዮጵያ በፓርላማና በማዘጋጃ ቤት/ሲቲ ሆል ሕንፃ ላይ ‹‹ተገትሮ››› እንደምናየው የሚሠራም፣ የማይሠራም፣ የቆመም፣ የተበላሸም ዓይነት የሕንፃ ላይ ሰዓት አይደለም፡፡ ተምሳሌታዊ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ነው፡፡ የፕሬስ ውጤት ነው፡፡ ነጋሪ ነው፡፡ ሜታፎር ነው፡፡ ሎጎ ነው፡፡ ብራንድ ነው፡፡

ሰዓቱ ስንት ነው? ሰዓቱ ምን ይላል? ማለት ተዛማጅ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ይህ የተከበረ፣ ብዙ የመታመን ክብር ያገኘ የሚዲያ ተቋም የሚያስተዳድረው ሰዓት የሚያመላክተው፣ የሚያሳው፣ የሚናገረው የሰው ልጅ፣ ሥልጠኑ ዓለም፣ ይህ የጡንቸኞችና የጉልበተኞች ዓለም ‹‹የጫረውን እሳት›› መቆጣጠር አለመቻሉን ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም ሥልጣኔን ራሱን ሊበላ በሰኮንዶች ብቻ የሚቆጠር ጊዜ ብቻ እንደቀረው ነው፡፡ ሰዓቱ ጥፋት አፋፍና ግቢ ውስጥ፣ ሞት አፍንጫ ሥር አይደለም፡፡ ኦምኒሳይድ፣ ጠቅላላ ራስንና ሥልጣኔን፣ ሕይወትንና ህልውናን ማጥፋት ውስጥ ገብተናል፡፡ በሰዓቱ 47 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከዚህ የኋሊት ከሚቆጠር የመንፈቀ ሌሊት መጥፊያ ርቀን የቆየነው ሲበዛ ለ17 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ይህ የተመዘገበው በ1991 ዓ.ም. የሰዓቱ አቆጣጠር ነው፡፡ ያኔ ሰዓቱ ከምሽቱ 23፡43 ነበር፡፡

ይህን ያህል ዘመን የሞላው ይህ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በታች ሲቆጥር 2020 የመጀመርያው ነው፡፡ 2021 በዚያው ቀጠለ፡፡ በ2021 እና በ2022 ሰዓቱ ለመንፈቀ ሌሊት ለኦምኒሳይድ 100 ሰከንዶች ጉዳይ ሆነ፡፡ 2023 ላይ ወደ ዘጠና ሰከንድ ጉዳይ ለዕልቂት ተቃረብን፡፡ ሰዓቱ የሚቆጥረው፣ ከቁጥር የሚያስገባው የኑክሌርን አደጋ ብቻ አይደለም፡፡ ያንኑ ያህል እኩል የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጅ በራሱ ላይ ‹‹የጫረው እሳት›› ነው፡፡ ተላላፊ በሽታ፣ ‹‹ሥልጣኔ››ያትን ራሱ የፈጠረው የጥፋት መሣሪያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰላም መከራውን የሚያየው እዚህ አጠቃላይ ሕመም ውስጥ በመንከላወስና በመንገላታት ብቻ አይደለም፡፡ የዘንድሮውን የ2023 ሰዓት ይበልጥ ወደ ጥፋት፣ ዕልቂትና ወደ ኦምኒሳይድ ይበልጥ ያስጠጋው በብቸኝነት ባይሆንም፣ በዋነኛነትና በአመዛኙ ዩክሬን ውስጥ የሚካሄደው የሩሲያና የኔቶ ጦርነት ነው፡፡ ይህ አባባል ወይም አገላለጽ ‹‹በሩሲያና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት›› አማራጭ ወይም ተለዋጭ አባባል አይደለም፡፡ ፍልሚያው ዩክሬንና ሩሲያ በሚባሉ ሁለት አገሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት አይደለም፡፡ ከዚያ በተለየ ሩሲያን አስገድዶ፣ አማራጭ አሳጥቶ፣ በዩክሬን ላይ ወረራ እንድትከፍት ያስደረገና ዩክሬን ውስጥ በኔቶ ኃይሎችና በሩሲያ መካከል የሚደረግ ባህርይውም የታወቀ ጦርነት ነው፡፡ ኢትዮጵም በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ስምና የመንግሥታቱን ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረትን ባንዲራና ዓላማ እያውለበለቡ ‹‹The Responsibility to Protect›› ብሎ አመካኝቶ፣ ‹‹ዓለም አቀፋዊ ኅብረተሰብ›› የሚፋለምባት አገር ትሆን ዘንድ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሠራውን ሁሉ እናውቃለን፡፡ ምክንያቱና አጋጣሚዎቹ የትኛውም ጉዳይ ቢሆን ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውና ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሪቶሪያ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት በድል ቆሟል፡፡ እስካሁን (አሁን ያለነው ጥር መጨረሻ ሳምንት ላይ ነው) ባለው የሦስተኛው ወር መሰናበቻና የአራተኛው ወር መባቻ ላይ ቢያንስ ቢያንስ ክፉ ዜና አልሰማንም፡፡ እንዲያውም የ2023 የፌብሯሪ (የካቲት) ወር የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የሴኪዩሪቲ ካውንስል ጊዜያዊ መርሐ ግብር እንደሚያሳየው፣ ካውንስሉ ራሱ መቀሌ ላይ የመጀመርያውን የመስክ ሚሽን ጥር 26 ቀን (February 3) ያደርጋል፡፡

(የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የሴኪዩሪቲ ካውንስል ማለት ምንና ማን እንደሆነ ማወቅና መረዳት በገዛ ራሱ ምክንነት ከ‹‹ጠቅላላ ዕውቀት›› በላይ እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በምንነጋገርበት የፕሪቶሪያ ስምምነት አፋጻጸም ዓውድ ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያለው በመሆኑ ጭምር፣ የዚህን ተቋም ምንነት በአጭሩ ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መጀመርያ ነገር የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የሴኪዩሪቲ ካውንስል ማለት የአኅጉራዊው ድርጅት ቋሚ የሰላምና የሴኪዩሪቲ ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡ ግጭቶችን የመከላከልና የመፍታት አደራ የዚህ ቋሚ አካል አደራ ነው፡፡ ቋሚ አባላት የሚባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓይነት ነገር የለበትም እንጂ፣ አሥራ አምስት አባላት ያሉት የተመድ የሴኪዩሪቲ ካውንስል አቻ ሚና የሚጫወት ተቋም ነው፡፡ 15ቱ አባላት የሚመረጡት በኅብረቱ አስፈጻሚ አካል (የሚኒስትሮች ጉባዔ) ሲሆን፣ የአገርና የመንግሥታት መሪዎች ጉባዔም ይህንኑ ማፀደቅ አለበት፡፡ ከማዕከላዊው፣ ከምሥራቃዊውና ከደቡባዊው አፍሪካ ከእያንዳንዱ ሦስት ሦስት አባላት ከሰሜናዊ አፍሪካ ሁለት አባላት፣ ከምዕራባዊው አፍሪካ ደግሞ አራት አባላት የሚመረጡበት ይህ ተቋም ከ15 አባላቱ መካከል የተቋሙን ዘላቂነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሲባል አምስቱ ለሦስት ዓመት የሥራ ዘመን ሲመረጡ፣ አሥሩ ደግሞ ለሁለት ዓመት ይመረጣሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የሴኪዩሪቲ ካውንስል ሰብሳቢ እንደ ተመድ ሴኪዩሪቲ ካውንስል በአባላቱ መካከል የወር ተራ ይዞ የሚደላደል ሲሆን፣ የአኅጉራዊ ምክር ቤቱ የመቀሌ የመስክ ጉብኝት በሚካሄድበት ወቅት የሰብሳቢነቱ የወር ተራ የደቡብ አፍሪካ ተራ ነው)፡፡

ከፍ ሲል እንደተገለጸው ጦርነቱ ቆሟል፣ በድል ቆሟልም ስል ዝም ብሎ ለአንደበት ወግ ያህል፣ ወይም ‹‹ወሬ ለማሳመር›› ወይ የአንድን ወገን ብቻ የ‹‹ግል›› ስሜት ለማስተጋባት አይደለም፡፡ መጀመርያ ነገር የፕሪቶሪያው ስምምነት በስሙም፣ በተግባሩም፣ በዓላማውም ይኼው ነው፡፡ የስምምነቱ ረዥም አርዕስት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ መካከል ግጭትን በቋሚነት በመግታት አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹ስምን መልዓክ ያወጣዋል›› ዝም ብሎ ምኞትም ሆነ አጉል ፈንጠዝያ ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ፣ ስያሜው (የተጠቀሰው ረዥም ርዕስ ራሱ) የስምምነቱን የ‹‹እግር መንገድ››፣ እንዲሁም የ‹‹ዓይን ብርሃን›› ጭምር የሚያመለክት ነው፡፡ ስምምነቱ ዝም ብሎ ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት አልተባለም፡፡ እዚህ ሰላም፣ ለዚያውም ዘላቂ ሰላም ላይ ዝም ብዬ እደርሳለሁ አይልም፡፡ ግጭትን ማቆምን፣ በቋሚነት ማቆምን መንገዱ ያደርጋል፡፡ የዚህን ትርጉም፣ የግጭት ማቆምን የመርህ መሠረቶች ይደነግጋል፡፡ አንቀጽ ሁለትና ሦስት ይህንን ራሱን ብቻውን የሚያፍታቱና የሚደነግጉ ናቸው፡፡ እዚህም ሁሉ ውስጥ እንዲያው ዝም ብሎ ስተት ተብሎ አልተገባም፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት መግቢያ፣ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ አንድ ላይ የተደነገገው የስምምነቱ ግብ የዘላቂ ሰላምን ልክና መልክ፣ ትርጉምና ይዘት እያስተዋወቁ የሚመሩ፣ የሚያስተዋውቁና የሚያስበኙ ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ፣ በተለይ ሁልጊዜም የሚደንቀውና የሚገርመው (እኔ በበኩሌ ብዙ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እነሆ ላለፉት ሦስት ወራት ሁልጊዜ ይገርመኛል) የስምምነቱ ጓጉንቸር ወይም ሊንችፒን (Linchpin) የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት/ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱ፣ በራሱ በኢትዮጵያ በሰላምና በለውጥ ኃይሎች ውስጥ እንኳን ሙሉ ‹‹ስምምነት›› በሌለበት ሁኔታ የሰላሙን ስምምነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ ‹‹ማንጠልጠል›› የአልድልኦ ወይም የማዳላት፣ ወይም ከልጅ ልጅ የመለየት አለዚያም የ‹‹በለስ ቀንቶን›› ጉዳይ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት መሪነትና የበላይ ጠባቂነት ማዕቀፍና እዚያ ግቢ ውስጥ ለዘላቂ ሰላም የሚደረግ ጥረት ሁሉ፣ የአኅጉራዊውን ድርጅት/ተቋም ዋናውን ዋልታና ምሰሶ ከቁጥር ያስወጣ ከውጭ ያደረገ ስምምነት ሊያዋልድ አይችልም፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥን ወይም ‹‹Unconstitutional Change of Government›› ወይም ‹‹UCG››  የሚል ምኅፃረ ቃል ብቻውን ሊገልጸው የበቃ የሕግ ወግና ማዕረግ ያለው ጽንሰ ሐሳብ ማስተዋወቅና ማቋቋም የቻለው የአፍሪካ ኅብረት በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በእጅጉ ያስከነዳ፣ የዓለም/የአኅጉሪቱም ሰላምና ሴኪዩሪቲ ሥጋት ሁኔታዎችን መቀመር (ቢያንስ ቢያንስ መቀመር) የተሳካለት ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለዚያውም የትም በተወረወረና በተሰነቀረ አንቀጽ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ ቦታውና ሥፍራው እንዲመሽግ በተደረገ ድንጋጌው (በአንቀጽ 9 የሕገ መንግሥት የበላይነት ድንጋጌ) በንዑስ አንቀጽ (3)፣ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኃን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቷ የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ ያደረጋችውን ይህንን ወግና ባህል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ኅብረት እያበለፀገው፣ እያጎለበተው መጥቶ ዛሬ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥ ማለት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶችን፣ የመርሰነሪ ጣልቃ ገብነቶችን፣ የታጠቁ አማፅያን የሚፈጽሙትን የመንግሥት ማስወገድ ተግባር፣ እንዲሁም ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ከሥልጣን አልወርድም የማለትን ጭምር የሚያካትት ሆኗል፡፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ የተደረገው የሰላም ስምምነት በዚህ ማዕቀፍና ግቢ ውስጥ ተፀንሶና በልፅጎ ለዚህ የበቃው (ጥሩ ተደራዳሪዎች መልካም አጋጣሚዎች ጭምር፣ ወዘተ አግዘውት) በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እናም ከጊዜያዊ የግጭት ማቆም የጀመረ ዘላቂ፣ ዘላቂ ብቻ ሳይሆን ትርጉምና አንድምታው የተፍታታ የግጭት ማቆም ይደረጋል፣ በዚህም አማካይነት ወደ ዘላቂ ሰላም የሚደረገው ጉዞ ይቀጥላል ማለትን የመሰለ፣ ዝም ብለው ሲያዩት ብዙም ‹‹የማይደንቅ›› ውለታ ውስጥ የተገባው በሚገርምና ማንም ሊያስበውና ሊያልመው፣ ቢያስበውም፣ ቢያልመውም ከፍተኛ ተቃውሞና እንቢታ አጅቦት በኖረው ሌላ ውለታ ጭምር ታጅቦ፣ ተጎዳኝቶ ነው፡፡ ከሕወሓት ትጥቅ መፍታት ጋር፡፡ የዚህ መነሻ መሠረታዊ ምንጭ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥ (UCG) ማለት ነውር፣ ወንጀልና ክልክል በመሆኑ ነው፡፡

ሕወሓት ትጥቅ ይፈታል? አይፈታም? እንኳንስ በአጉራህ ጠናኝ ሊያስረታ የሚችል፣ ደግሞም ተቀባይነትና ተፈጻሚነት የሚኖረው ብይን ሊሰጠው ይቅርና ተራ ውይይታችን ውስጥ እንኳን የሚስተናገድ ‹‹ሐሳብ›› አልነበረም፡፡ ‹‹ምርጫ የማራዘም ጉዳይ›› የሰከነና የሠለጠነ የፖለቲካ የውይይት መድረክ አላገኝ ብሎ፣ ‹‹የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን› እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ‹‹ኮሚሽነር›› ሙሉ ወርቅ ኪዳነ ማርያምና ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ‹‹እኩል›› ኢትዮጵያ ‹ፕሪሚየር ሊግ› ውስጥ ባለሥልጣናት ሆነው/ተብለው ‹‹ሲታገሉ›› ዓይተናል፡፡ በስምምነቱ ሰነድ ውስጥ ዋናው ጉዳይ ሆኖ፣ ዋናው ጉዳይ በመሆን ብቻ ሳይወሰን የዘላቂ ሰላም ዋና መሠረት ሆኖ በየቦታው በየስምምንቱ ዋና ዋና ይዘቶች ውስጥ የሚዘናጠፈው ሕገ መንግሥታዊነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አንድ ብቻ ነው፣ ስለዚህም (ፓርቲ ብሎ ታጣቂ የለም) ሕወሓት ትጥቅ ይፈታል ብቻ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መልሶ ማቋቋም ማለት በስምምነቱ ውስጥ ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው (ለምሳሌ የስምምነቱን መግቢያ አራተኛ ፓራግራፍ አንቀጽ 1 (ግብ 1.2) እነዚህ ሁሉ ድንጋጌዎች የሚያሳዩት ስምምነቱ የዘላቂ ሰላም መንገድን የሚደለድል መንገድ መጥረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ማን የፍርድ/የድርድሩ ባለመብት፣ ማን ደግሞ የፍርድ ባለዕዳ እንደሆነ ጭምር ነው፡፡ እስካሁን የምንሰማውና የምናየው የስምምነቱ የአፈጻጸም ሒደት (የአገራችን ሁኔታና ተጨባጭ ፍጥርጥራችን የፈቀደልንን ያህል) እንደሚናገረው ‹‹ጉዞው ደህና ነው››፡፡ በደህና እየተጓዘ ነው፡፡ እስካሁን ወሬ የሆነ ችግር አላጋመጠንም፡፡

ስምምነቱ ውስጥ ቁልጭ ብለው የሠፈሩ አንዳንድ ‹‹ወሳኝ›› እና ስሜትን የሚያጎሹ ዓይነት ድንጋጌዎች አፈጻጸም ገና መልክ ገዝቶ፣ ግዝፍ ይዞ ባለመታየቱ፣ የኢትዮጵያን የፌስቡክ አርበኞች፣ ‹‹መጽሐፍ ገላጮች››፣ ‹‹የሚዲያ አዋጊዎች›› እና ታጋዮች ለብዙ ‹‹ክሊክ›› ብቻ ሳይሆን፣ ለጥቅስ የበቁ እያደረጋቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለምሳሌ በስምምነቱ አንቀጽ 10 በተለይም እዚያ ውስጥ በተለይ በአንቀጽ 10 የመጀመርያው ንዑስ አንቀጽ/ፓራግራፍ የተጠቀሰው የሽግግር/ኢንትሪም ሪጅናል አስተዳደር ጉዳይና ነገር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የተካተተብን ድንጋጌ ማንበብ አቅቶ፣ መረዳት አዳግቶ፣ ለዚያውም የዕውር ድንብር ‹‹ጥንቆላ›› ሥራ ውስጥ ገብቶ ትግራይ ውስጥ መንግሥት የሚቋቋመው በሕወሓት ብቻ ነው፣ ከመንግሥት ጋር በሕወሓት ጭምር ነው የሚል እጅና እግር የሌለው ‹‹ወሬ›› አጀንዳ ሆኖ ይሰማል፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ የስምምነቱ የአንቀጽ 10 ቦታና ሥፍራ ‹‹የመሸጋገሪያ ዕርምጃዎች›› የሚመለከት ነው፡፡ ይህ የተጠቀሰው ድንጋጌ በተለይ የሚናገረው ደግሞ ትግራይ ክልል ውስጥ የተወሰነ ጊዜ (ጊዜያዊ) የክልል አስተዳደር ስለሚቋቋምበት ሁኔታ ነው፡፡ የሚቋቋመው የተወሰነ ጊዜ (ኢንትሪም) አስተዳደር ዕድሜም ተወስኗል፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫዎች እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ ስለሚያገለግል የተወሰነ ጊዜ አስተዳደር ነው የሚደነግገው፡፡ ስለሚካሄደው ምርጫ፣ በምርጫ ስለሚቋቋመው መደበኛ እንደራሴያዊ ውክልና ብቻ ሳይሆን፣ ስለምርጫውም አስተዳደር ድንጋጌው ይወስናል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበላይ ተቆጣጣሪነት/አስተዳዳሪነት የሚካሄድ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ማለትም በስምምነቱ ተደጋግሞ በተለያየ ልክና መልክ የተገለጸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት/አስተዳደር ትግራይ ውስጥ መልሶ እስኪቋቋም ድረስ የሚያገለግል የተወሰነ ጊዜ (ኢንትሪም) አስተዳደርር ይቋቋማል፡፡ እንዴት ይቋቋማል? ማን ያቋቁመዋል? አንቀጽ 10 የሚያቋቁምበትን ሁኔታ የሚደነግገው ‹‹The establishment of an inclusive interim regional administration will be settled through political dialogue between the parties. በማለት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ግልጽ መልዕክት እያለ ሌላው ቀርቶ ‹‹Parties›› ማለት በስምምነቱ መግቢያ የመጨረሻው አንቀጽ/ፓራግራፍ ላይ የኢፌዴሪ መንግሥትና ሕወሓት ማለት መሆኑ በ‹‹ትርጉም›› ተወስኖ ሳለ፣ ምድረ ተንታኝ ሁሉ ጠንቋይ መቀለብ ውስጥ ገብቶ ያወራል፡፡

እስካሁን እንዳየነውና ተደጋግሞም እንደተገለጸው የስምምነቱ አፈጻጸም (ጭራሽ እንከን የለውም አይባል እንጂ) ደግና በጎ ሆኖ እየዘለቀ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የመላውን ኢትዮጵያን የፖለቲካ ሰላም ጭምር መወሰንና መቃኘት የሚችለውን ይህንን ፕሪቶሪያ የጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምምነት ህልውና እየተፈታተነና ደጋግሞም እያሠጋ ያለው፣ በዚህ የስምምነቱ አፈጻጸም ሒደት ውስጥ ከስምምነቱ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ፣ ጣልቃ እያስገቡ ስምምነቱ ውስጥ የተሸነፈውን ቀልባሽነትና ለውጥ ተፃራሪነት ትንፋሽ ልስጥ የሚል የትግል ሥልት፣ የአመራርም ችግርና አላዋቂ ሳሚነት ጭምር ነው፡፡

ትናንት ከትናንት ወዲያ አዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥና አካባቢው ዝም ብሎ በመብት ማስከበር፣ ለነፃነት በመዋጋት ስም አቧራ ካላነስናሳሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ የአገር የፖለቲካ ሰላም ውስጥ የተደገሰው የክልል ባንዲራና መዝሙር ጉዳይ ሰጥቶን ያለፈው ምንም ሳያስተምረን፣ ያየነው መከራ ሳይመክረን ነው፡፡ ከመከራው፣ አደጋ ደግሶ ከነበረው መከራ ምን ተመከርን? ምን ተማርን? ይህንን ጥያቄ ሳንመልስና መተማመኛ መልስ ስለማግኘት አለማግኘታችንን ሳናውቅ ነው ሌላ አደጋ፣ ሌላ ሥጋት ውስጥ ድንገት ገብተን አሁን የምንገኝበት የአገር ሰላምና ደኅንነት አደጋ ውስጥ ራሳችንን ያገኘነው፡፡

‹‹አልሃምዱልላሂ ታቦታችን በሰላም ገባ›› እየተባለ ዓመት ከዓመት በወግ በማዕረግ በሚነገርበት አገር፣ ይህም የአገር ጌጥና የአብሮ መኖር ምክንያት ሆኖ በሚታወቅበት የጋራ አገር፣ መላውን የጥር አጋማሽ በሰላም አጠናቅቀን ተገላገልን ስንል በወሩ 14ኛው ቀን ላይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው አደጋ ጤነኛ ምልክት አልሆነንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ምናልባትም ወደ ፊትም ምንም ዓይነት ክፉ ነገር፣ ስህተት፣ ጥፋትም ሆነ ነውርና ወንጀል መፍትሔ፣ መድኃኒት ወይም ሕግ አጥቶ አያውቅም፡፡ ዛሬም፣ ወደ ፊትም ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች ደም መቃባት በሌለበት መንገድ የሚፈቱበት አማራጭ ፈጽሞ ዝግ አይደለም፡፡ መትጋትና መጣር ያለብን ይህንን እናስፋው፣ ይበልጥም እናጎልብተውና ብቸኛም መንገድ እናድርገው እንጂ ‹‹አማራጭ› እንዲሆን አይደለም፡፡ መጠየቅና መጠያየቅ ያለብን የፖለቲካ ሐሳቦች የሕዝብ ቅሬታዎች፣ ወደ ጠመንጃ፣ ወደ ብረት ትግል፣ ወደ አመፅ የሚሄድበት ዕድል እየጠበበ ሰላማዊና ሕጋዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶ ጭምር እያደገ፣ እየለመለመ መጣ ወይ እንጂ ‹‹ዋ!›› አለዚያ! የሚባል ማስፈራሪያ አማራጭ የጨዋታው ሕግ እንዳሻው ማስተናገድ የለበትም፡፡ መንግሥትም ቢሆን የሕግ ማስከበር ሥራው አንድ አካልና አምሳል አድርጎ መያዝ ያለበት ከሕገወጡ ይልቅ ሕጋዊውና ሰላማዊው መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያድግ የፖለቲካ የባህልና የአሠራር ሁኔታ መልማቱ ላይ በማተኮር ነው፡፡ ጉዳዩ በየትኛውም ወገን በኩል በጥበብና በልበ ሰፊነት መያዝ ያለበት አጣዳፊውን ጉዳይ አጣዳፊ ካልሆነው በመለየት ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› በማለት ጭምር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...