በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡ በተለይም የትምህርት ዘርፉ ላይ በደረሰው ውድመት በርካታ ዜጎች ከትምህርት ገበታቸው ሊሰናከሉ ችለዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ጦርነቱ በተፈጸሙባቸው ቦታዎች ላይ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተፈጠረው ስምምነት መሠረት በጦርነት ውስጥ ከርመው የነበሩ ቦታዎች ላይ ልማቶችን እንደ አዲስ ለማቋቋም መንግሥት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
በዚህም መሠረት ትምህርት ሚኒስቴር በጦርነትና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፣ በዚህም 71 ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለማስገንባት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን እንደ አዲስ መልሶ ለማቋቋምና ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ ዘንድሮ በማጠናቀቅ ለ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለማስተማሪያነት እንደሚከፈቱም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ምቹና የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም ከ47 ሺሕ ትምህርት ቤቶች ስድስቱ ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ትግራይ ክልልን ሳይጨምር 3,300 ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን፣ 4,000 የሚሆኑት ደግሞ በከፊልም ቢሆን ጉዳት እንደደረሰባቸው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የወደሙና በልዩ ሁኔታ የሚገነቡት 71 ትምህርት ቤቶች መካከል 50ዎቹ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዓለም ባንክ ድጋፍና ትብብር፣ 16ቱ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት እንዲሁም አምስቱ በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንደሚገነቡ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 13 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለመገንባት የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ እየተገባደደ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ለእነዚህንም ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚውል ሲሚንቶ ለማቅረብ ሚኒስቴሩ ከአራት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ውል መፈራረሙን፣ ይህም የግንባታ ሒደቱን በፍጥነት ለመጨረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የብረታ ብረት ጥሬ ዕቃዎችንም ለማቅረብ ውል መገባቱን ገልጸው፣ የሚገነቡት ትምህርት ቤቶችም በዚህ ዓመት ተገንብተው እስከመጪው መስከረም ወር ድረስ ለአገልግሎት ይበቃሉ ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ለአገልግሎት የሚውሉ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የተመረጡ የሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜና ደረጃ ጥራቱ በተሟላ መልኩ ለመገንባት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ሊገነቡ የታሰቡ ትምህርት ቤቶችን ዕውን ለማድረግ እስካሁን 2.8 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
ትምህርት ቤቶቹን ለመገንባት ሚኒስቴሩ ባለፉት ወራት የቅድመ ዝግጀት ሥራ ሲሠራ እንደነበረ ያስታወሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ አርክቴክት ማኅበር ጋር በተፈጸመው የመግባቢያ ሰነድ የዲዛይን ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከ10 አማካሪ ድርጅቶች ጋር ውል መፈጸሙን እንዲሁም ሚኒስቴሩና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ስለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ፣ በተቋራጮች ምርጫና ሥምሪት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የማንዋል መግባቢያ ሰነድ እንደተፈራረሙ ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ፣ በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶች ግን የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ግንባታቸው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በግንባታ ማስጀመርያ መርሐ ግብሩ ላይም የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር)፣ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሠናይ ድርጅት አገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ፣ ኮንትራክተሮች፣ የግንባታ አማካሪዎች ተገኝተዋል፡፡