Monday, December 11, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የትምህርቱ ነገርና መራር ገጠመኞች

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

‹‹መማር ያስከብራል፤ አገርን ያኮራል!›› የሚለው ብሂል፣ ትምህርት ለግል አዕምሮአዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለአገርም ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው ያመላክታል፡፡ አገር በትምህርት ውስጥ የሚያልፉ ዜጎቿ በጨመሩ ቁጥር፣ ምክንያታዊ ትውልድን እያፈራች ዕድገትና ልማቷን የማፋጠን ዕድሏ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ዜጎቿ ችግሯን የሚሸሹ፣ ሲከፋም ችግር የሚፈጥሩባት ሳይሆን በቅርብ ሆነው መፍትሔ የሚሰጡና የችግርን መፍቻ ቁልፍ የታጠቁ ናቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ዜጎች ለአገር ሸክም ይሆናሉ፡፡ የተሠራን የሚያጠፋና የሚያወድም ትውልድም ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ታድያ ቁልፍ መሠረቱ ትምህርት ነው፡፡

ከዚሁ እውነታ ጋር በሚናበብ መልኩ፤ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) በ1956 ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይም ስለ ትምህርት አስፈላጊነትና ፋይዳ ሲያትቱ፤ ‹‹ስለትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከሆነ ማናቸውም የሕይወት ችግር ሊፈታ ይችላል፣ ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው፣ እነዚህን ነጥቦች ያልተረዳ ማኅበረሰብ ሆነ ሥርዓተ ትምህርት፣ በትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ መቸገሩ አይቀርም፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ከላይ በመንደርደሪያነት ያነሳኋቸው የሊቃውንቱ ሐሳብ ትምህርትን ወሳኝነትና ያለውን ከፍተኛ ፋይዳውን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ የትምህርት ነገር በአገራችን በብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ተተብትቦ እንዳለ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለአብነትም ያህል፣ ከሰሞኑ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች አስደንጋጭ ውጤት ጋር በተያያዘ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹ድሮውንስ በተበላሸና በወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ካለፉ ተማሪዎች ከዚህ ውጪ ምን ዓይነት ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ ብለን ነበር የጠበቅነው?›› የሚሉ ዓይነት አግራሞትና ጥያቄ አከል ድምፆችን እዚህም እዚያም ጎልተው ሲነገሩ እየሰማን ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተባለው የትምህርት ነገር በአገራችን ኢትዮጵያ በብርቱ ሕመምና ሥቃይ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል፡፡ ይህን ሐሳቤን ያጠናክርልኝና ነገረ ጉዳዬን በይበልጥ ፈር ለማስያዝ ያግዝኝ ዘንድም ጥቂት ገጠመኞቼን ላስቀድም፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንዲት የሥራ ባልደረባዬ የሆነች ጓደኛዬ ስልክ ደውላልኝ- ‹‹እባክህ አንድ ጉዳይ ላማክርህ ፈልጌ ነበር፤›› አለችኝ፡፡ የእኔን ዕርዳታና የምክር ዕገዛ የሚሻ ምን ጉዳይ አጋጥሟት ይሆን ይህች ወዳጄ በሚል ሥጋትና ፍርሃት ውስጥ ሆኜ- ምንድን ይሆን ጉዳዩ አልኳት፡፡ እንዲህ ስትል ጉዳዩዋን አጫወተችኝ፡፡

‹‹… ይኸውልህ ታናሽ እህቴ የሁለተኛ ዲግሪዋን በአንድ የግል ኮሌጅ እየተማረች ነው፡፡ እናም ለማስተርስ ዲግሪዋ ማሟያ የሚሆናትን የጥናት ወረቀት የሚሠራላት ሰው ትፈልጋለች፡፡ አንድ ሁለት ሰዎችን ጠይቃ ነበር ግን ከ15 እስከ 20 ሺሕ ብር ዋጋ ጠየቋት፡፡ መቼም የመንግሥት ቤት የደመወዝ ነገር ታውቃዋለህ… ዋጋው ተወደደባት፣ እናም ቀነስ ባለ ዋጋ የሚሠራ አንተ የምታውቀው ተባባሪ ሰው ካለ እንድትጠቁመኝ ብዬ ነው፤›› አለችኝ፡፡

እኔም፣ እንዴ!? ለምን ይህን ያህል የዋጋ ድርድር ውስጥ ከምትገባ የሚከብዳትን ነገር ካለ እያገዝናት በራሷ ጥረት/ችሎታ የመመረቂያ ወረቀቷን ለመሥራት አትሞክርም አልኳት፡፡ ‹‹አይ! ወንድሜ እሷ ከፕሮፖዛል ጀምሮ የመመረቂያ ወረቀቱን ሙሉውን ሠርቶ የሚያስረክባት ሰው ነው የምትፈልገው፤›› አለችኝ፡፡ ‹‹… ደግሞስ አናውቅምና ነው?! ለመሆኑ ከጥቂት ተማሪዎች በቀር አብዛኛው ሰው የሌላ ሰው የመመረቂያ ወረቀት ርዕሱን ብቻ እየቀየረ እያስገባ አይደል እንዴ የሚመረቀው … ሲጀመርስ እዚህ አገር ወረቀት ይኑርህ እንጂ ዕውቀት ቦታና ሥፍራ አለው እንዴ? ወንድም ዓለም፣ እኅቴ አሁን የምትፈልገው ትንሽም ብትሆን የደረጃና የደመወዝ የዕድገት ምክንያት የሚሆን የዲግሪ ሰርተፊኬት በእጇ ላይ እንዲገባላት ብቻ ነው፣ ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው፤›› አለችኝ በምሬት ፈርጠም ብላ፡፡

እኅቴ ይቅርታ ይህ ሌላ ጉዳይ ነው.. እኔ ግን የዲግሪና የማስተርስ ወረቀት ንግድ ጉዳይ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ በየኮሌጁና በየዩኒቨርሲቲው ደጃፍ ያለ ምንም ሃፍረትና መሳቀቅ ‹‹የመመረቂያ ወረቀት በተመጣጣኝ ዋጋ እንሠራለን!›› የሚሉ ማስታወቂያን የለጠፉ ብዙዎች አሉና እነሱኑ ብትደራደር/ብትለማመጥ ይሻላታል፣ ብያት ተለያየን፡፡ ከጥቂት ሳምንት በኋላ ይህችን የሥራ ባልደረባዬን አገኘኋትና እኅቷ እንዴት እንደሆነች ጠየቅኳት፡፡

‹‹እባክህ ምን ይደረግ ብለህ ነው? እንደምንም ተደራድረን በ12 ሺሕ ብር የማስተርስ ዲግሪ የመመረቂያ ወረቀቷን ሠርተው እንዳስረከቧት፤›› ነገረችኝ፡፡ አሁን ደግሞ ይኸውልህ ለዲፌንስ (የፓወር ፖይንት) ገለጻዋን በአማርኛ ተርጉሞ የሚያስረዳት ሰው እየፈለግን ነው፣ ብቻ እንደ ምንም ብላ በተገላገለች እኔንም ግራ አጋባችኝ እኮ … ብላኝ እርፍ አለች፡፡

እንግዲህ በአገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ምን ያህል ማጣጣርና በፅኑ ሥቃይ ውስጥ እንዳለ ይህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በተመሳሳይም በዚሁ ዓመት በግሌ የማውቃቸው ከሌላ የግል ዩኒቨርሲቲ በሌላ ተማሪ የተሠራ/የተገለበጠ የጥናት ድርሳንን እንደገና እነሱም ገልብጠው አቅርበው የተመረቁ ተማሪዎችን አውቃለሁ፡፡ የመመረቂያ ወረቀቶችን መሥራት ለነገሩ መሥራት ሳይሆን የአንዱን ከአንዱ እየገለበጡ መስጠት የጦፈና የሚያዋጣ ቢዝነስ ሆኗል፡፡ ከዚሁ ሐሳብ ሳንወጣ ሌላ መራር ገጠመኜን ላክል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜያት በሥራ በቆየሁበት አጋጣሚ በግል ኮሌጆች የሚማሩ ጥቂት የማይባሉ የኢሕአዴግ ሹመኞችና ካድሬዎች ከዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት በተማሪዎች የተሠሩ የመመረቂያ ወረቀቶችን እያስወጡና እየገለበጡ የራሳቸው እንደ ሆነ አድርገው በማቅረብ ይመረቁ እንደነበር እነርሱም ያውቃሉ እኛም እናውቃለን፡፡

እንግዲህ በዚህ ዓይነት የወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፉ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች ምን ዓይነት ተማሪዎችንና ዜጋን ሊያፈሩ እንደሚችሉ ማሰብ ነው፡፡ ለነገሩማ የነገረ ጉዳዩን አንዱን ሥር ስንመዝ፣ መንግሥት እንደ ጠበል በየክልሉ ካዳረሳቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጀምሮ በየመንደሩ የተከፈቱ የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን- የመምህራኑን የዕውቀት ደረጃ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ ሙከራዎች ጥራት፣ ዘመናዊነትና ተደራሽነት ብንገመግም  ተቋሞቻችን ብዙ የሚያስደነግጡ ጉዶችን ተሸክመው ነው ያሉት፡፡

በአገራችን የትምህርት ነገር ከላይ እስከ ታች ድረስ የተዘፈቀበትን ችግርና የገባበትን ቅርቃር አስመልክተውም – የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከዓመት በፊት በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ነበር ያሉት፡-

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሦስተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 69 በመቶ ነው፡፡ በሚያስተምሩበት ትምህርት የምዘና ፈተና ወስደው 50 በመቶ በማምጣት ያለፉ መምህራን ቁጥር ከ30 በመቶ በታች ነው፡፡ የትምህርት አስተዳዳሪ የሚባሉት የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ለቦታው መመጠናቸውን ለማረጋገጥ በተሰጠ ምዘና ፈተና ያለፉት 30 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ አስተማሪዎች ውስጥ 52 በመቶዎቹ በአግባቡ ትምህርት ቤት ወይም ክፍል ተገኝተው አያስተምሩም፡፡

በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ትምህርት ተብሎ ደግሞ ዲግሪ በየቦታው እንደ ከረሜላ ታድሏል፡፡ ይህ በጣም የሚያስገርምና አጠቃላይ የዘርፉን አስደንጋጭ ስብራት የሚያሳይ ነው፡፡ የትምህርት ተደራሽነት ማደጉን ሳንረሳ፣ ዘርፉ በእጅጉ በመጎዳቱ ላይ ግን ምንም ክርክር አይኖርም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ የነበረው አገር ወደ 47 አድጎለታል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ማደጉ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ በሚያሰኝ ደረጃ ላይ ነው ወይ ያሉት የሚለው፣ እንዲሁም ለተማሪዎች የሚሰጡት ዲግሪ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል የሚያሰኝ ነው የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ለመረዳት የሞከርነው ደግሞ ምንድነው ይህን ችግር የፈጠረው የሚለውን ነው፡፡ በመሠረታዊነት ትምህርትን ማዳረስ አስፈላጊ ነው ከሚለው ቀና አመለካከት ቢነሳም፣ ነገር ግን በቂ የትምህርት መሣሪያ፣ አስተማሪና የትምህርት አሰጣጥን ሳይፈጥሩ ሕንፃ እየገነቡ ብቻ ተማሪዎችን መሰብሰብ ችግሩን እንደፈጠረው ደረስንበት፡፡ በኢትዮጵያ በየትምህርት ዕርከኑ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል የተሟላላቸው ተማሪ ቤቶች ጥቂት ናቸው…፡፡

ሌላው የትምህርትን ነገር ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች የሚጠቀሰው፤ ትምህርት እንደ አንድ በአቋራጭ የመክበሪያ/የቢዝነስ መንገድ ተደርጎ መታየቱ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ትምህርትን ንግድ አድርገውት ያለ ምንም ሃፍረት የዲግሪና የማስተርስ ወረቀቶችን የሚቸርችሩ ጥቂት የማይባሉ የግል ኮሌጆች ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው መበራከቱ ነው፡፡ እነዚሁ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪም ሆነ የሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር የሚያበቃቸውን የጥራት ማረጋገጫ በእንዴት ባለ ማታለል፣ እጅ መንሻና ሙስና እንደሚያገኙት ብትሰሙና ብታዩ በእጅጉ ታዝናላችሁ፣ ትደነግጣላችሁም፡፡

አሳዛኙና አስደንጋጩ እውነታ ደግሞ እነዚህን የትምህርት ተቋማት በማቋቋም፣ በባለቤትነትም ሆነ በመምራት ረገድ ጥቂት የማይባሉ ‹‹ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች›› መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ትውልድን የሚያመክን ሥራ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ስትታዘቡ ድንጋጤያችሁንና ሐዘናችሁን በጣም ያከፋዋል፡፡

ለመውጫ ያህልም፣ ሰሎሞን በላይ ፋሪስ (ዶ/ር)፣ ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ መመረቂያ የሆነውን የፒኤቺዲ የጥናትና ምርምር ድርሳናቸውን፣ ‹‹ከዶክተርነት ደብተራና ወልይነት›› በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ዶክተር ሰሎሞን በዚሁ ወደ አማርኛ ቋንቋ በተረጐሙት የዶክትሬት መመረቂያ ድርሳን/መጽሐፋቸው ውስጥ- ከአገሩም ከውጭም ሳይሆን ግራ ተጋብቶ ስላለው የትምህርት ሥርዓታችን ጉዳይ ለጥናት ሥራቸው መረጃ ለማሰባሰብ ከአገረ ካናዳ መጥተው ያጋጠማቸውን እንዲህ በማለት በቁጭትና በሐዘን ይገልጹታል፡፡

‹‹… በመንግሥት ሥር ያሉም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያሉ የትምህርት ባለሙያዎች ሙያቸውን የተመለከተ ቃለ መጠይቅ ማድረግ አስቸጋሪና በጣሙን ፈታኝ ሆኖ አግኝቼዋለኹ፡፡ አንድም ከመጀመሪያውኑ ሥርዓተ ትምህርቱ አርቆና አሰላስሎ አሳቢ ስላላደረጋቸውና በሚናገሩበት ጉዳይ ላይም በቂ ሥልጠና/ችሎታ ስለሌላቸው መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ችግሩን የሚያከብደውና የሚያከፋው ደግሞ አጣምሞ ያሳደገን ትምህርት መጣመማችንን [መንገድ መሳታችንን] እንድናውቅ አለማድረጉና መጣመማችንን ደግሞ ልናቃናው ያለመቻላችን መርገምት ነው፡፡ የአገራችንን/የዛሬውንና የነገውን/ ትውልድ ዕጣ ፈንታችንን የምንወስንበትን ትምህርትን የመሰለ ነገር ሥርዓቱን ማሻሻልና መመርመር ካልተጋን ውጤቱ ከዛሬውም በጣሙን የባሰና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው…፤›› ይሉናል በጥናት ድርሳናቸው፡፡

እንግዲህ የዛሬው ከመቶ ሺዎች ተፈታኞች ሃያ ሺዎቹ ብቻ የማለፊያ ውጤት የማግኘታቸው ብዙዎቻችንን ያስደነገጠ ዜና እንዲሁ የአንድ ጀምበር ክስተት አይደለም፡፡ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ የተበላሸው የትምህርት ሥርዓታችን የተንጋደደ አካሄድ ውጤት ነው፤ ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ የትምህርት ጉዳይ በፅኑ ሕመምና በብርቱ ሥቃይ ውስጥ ነው ያለው፣ እናም እስከወዲያኛው ከማሽለቡ በፊት መንግሥት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትና ምሁራን ቅድሚያ ትኩረት ሊቸሩት ይገባል፡፡ አፋጣኝ የሆኑ ተከታታይ ዕርምጃዎችም ሊወሰዱ ይገባል፡፡ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩትን የለውጥና የማሻሻል ሥራዎችንም አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

እንደ መቆዘሚያ ያለ የውይይት ማጫሪያ ሐሳብ፤

እንደ ሕዝብ ችግራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መሄዱ የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድደናል፣ ‹‹ዘመናዊ ትምህርታችን ድህነትን የምንቀርፍበትን ክህሎት፣ ዕውቀትና ሰብዕና ሊሰጠን አሊያም ሊያጎናጽፈን ስለ ምን አልቻለም?››

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles