Sunday, December 10, 2023

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን ምንነት ሲተነትን እንደሚከተለው ያስቀምጣል፡፡ “Education is the process of facilitatiing learning or the acquisition of knowledge skills, values, beliefs and habits.” ይለዋል፡፡ በግርድፉ ሲተረጎም ትምህርት የዕውቀት፣ ክህሎት፣ እሴቶች፣ አመለካከቶችና ልማዶች የምንጨብጥበት መንገድ ነው ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

ዩኔስኮ ከዚህ ጎን ለጎን ስለትምህርት ጥራት ሲያስረዳ፣ ትምህርቱ የሚሰጥበት መንገድ ተገቢ የክህሎት መጨበጫ መንገዶችን ባሟላ ሁኔታ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የፆታ ወይም የአካል ጉዳተኝነትን መነሻ ሳያደርግ ትምህርቱ ሲቀርብ ጥራት ተረጋገጠ እንደሚባል ያመለክታል፡፡ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት፣ የትምህርት ግብዓት፣ የትምህርት መሣሪያ (ቁሳቁስ) መሟላት ለጥራት መረጋገጥ ያለውን አስፈላጊነት ዩኔስኮ ያብራራል፡፡

አያይዞም የትምህርት ተደራሽነት ችግርን በተመለከተ በመላው ዓለም ከ103 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የፊደል ገበታን እንደማያውቁ ከእነዚህ መካከል ደግሞ 60 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው በማለት ዓለም ከተጋፈጠቻቸው ችግሮች አንዱ ይህ ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡

በታዳጊ አገሮች የትምህርት ተደራሽነትን ዋና ችግር ነው የሚለው ዩኔስኮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ጉዳዩ እንደሚብስ ይጠቅሳል፡፡ ለአብነት ያህል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን በታዳጊ አገሮች 91 በመቶ ቢደርስም፣ አሁንም ቢሆን 57 ሚሊዮን ታዳጊዎች የትምህርት ቤቶችን ደጃፍ አልረገጡም ይላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሰሃራ በታች አፍሪካ አገሮች ችግሩ ይብሳልም ሲል ያክላል፡፡

በተመድ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች፣ እንዲሁም አሁን እየተተገበረ ባለው የዘላቂ ልማት ግቦች ትምህርት አንዱ ቁልፍ የልማት ግብ ተብሎ መቀመጡን ነው ዩኔስኮ የሚጠቁመው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሁሉም ዓይነት የትምህርት ችግሮች የሚፈተኑ አገሮች ተደራሽነትን ከማስፋት እኩል፣ የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ጉዳይም በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ይነገራል፡፡

የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በሚል በሚወስዱት ያላሰለሰ ጥረት የትምህርት አቅርቦቱ ሊያድግ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ጎን ለጎን የጥራቱን ጉዳይ ታሳቢ ያደረገ መንገድ ካልተከተሉ ዞሮ ዞሮ አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆነው እንደሚቀሩ ነው የሚገመተው፡፡ በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ አጋጠመ የሚባለውም ይህ ሲሆን፣ የትምህርት አቅርቦቱን ከማስፋት እኩል ጥራትን ለማስጠበቅ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ዘርፉን ጎድቶታል የሚለው ነጥብ ጎልቶ ይነሳል፡፡

ከትምህርት ጥራት ችግር ጎን ለጎን ደግሞ የኢትዮጵያ ትምህርት በርካታ የፖለቲካ ችግሮች የሚገጥሙት ዘርፍ እየሆነ ነው የሚል አስተያየት ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ጉዳይ ከባድ ቀውስ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ሲፈጥር ይታያል፡፡ የካሪኩለም ቀረፃና ትግበራ በትምህርት ዘርፉ ላይ እሳት ሊያጭር ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሚሰቅሉት ባንዲራና የሚዘምሩት ብሔራዊ መዝሙር ሳይቀር፣ እጅግ የከረረ የፖለቲካ ቀውስ ማስነሻ ጉዳይ ሲሆን የታየበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ትምህርት በኢትዮጵያ እጅግ ውስብስብ ለሆኑ የፖለቲካ ቀውሶች መነሻ ሲሆን የታየበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በየጊዜው የሚያገረሸው የብሔር ፖለቲካ ውዝግብና የተማሪዎች ግጭት ከጥናትና ምርምር ይልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን ዝነኛ ሲያደርግ ይታያል፡፡ ብሔራዊ ፈተናዎች ጊዜያቸው በደረሰ ወይም ውጤት በተለጠፈ ቁጥር፣ በአገሪቱ የሚነሳው የፖለቲካ ውዝግብ ደግሞ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው፡፡

ፈተና በጋራ መሥራት፣ መኮራረጅና የፈተና መሰረቅ ጉዳዮች ሁሌም አሳሳቢ ናቸው፡፡ አምናና ካቻምና የብሔራዊ ፈተናዎች በተሰጡበትና ውጤቶች በታወቁበት ወቅት አጋጥመው የነበሩ ችግሮች፣ በዋናነት የክልል ወይም የብሔር ፉክክሮችን የተንተራሱ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ የብሔራዊ ፈተና አሰጣጥና ውጤት አወጣጥ ደግሞ ተጨማሪ ውዝግቦችን ይዞ የመጣ ነበር፡፡

ዘንድሮ የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን በየዩኒቨርሲቲው በመውሰድ ለኩረጃ ፍፁም አመቺ በማይሆን መንገድ እንዲፈተኑ የማድረጉ ዕርምጃ፣ ትምህርት ሚኒስቴርን ለብዙ ትችቶች ያጋለጠ ደፋር ዕርምጃ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ብዙ ውዝግቦች ያስነሳው የትምህርት ሚኒስቴር ይህ ዕርምጃ፣ አሁን ደግሞ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ውጤት ሲወጣ ሌላ መልክ ይዞ ተከስቷል፡፡

ከሰሞኑ የወጣው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ችግር ምን ላይ እንዳለ አጋልጦ ያሳየ እየተባለ ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ለመድፈን ጥቂት ከቀረው ተፈታኞች ውስጥ 996 ሺሕ ያህሉ ፈተናውን ወስደው ውጤት እንደተሰጠ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

አማካይ የተፈታኞች ውጤት 29.25 በመቶ ብቻ ነው ያለው የትምህርት ሚኒስቴር፣ 32.9 በመቶ አማካይ ውጤት የተገኘበት ኬሚስትሪ ከፍተኛው ሲሆን ዝቅተኛ 25.5 ሳይንስ ሒሳብ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

በፆታ ውጤቱን ከፍሎ ያስቀመጠው ትምህርት ሚኒስቴር የወንዶች 30.23 በመቶ አማካይ ውጤቱ እንደሆነ፣ የሴቶች ደግሞ 29.09 በመቶ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች 31.63 በመቶ ሲሆን ማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ 27.79 ነው ውጤታቸው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የውጤት ዳታ (አኃዝ) መሠረት 570 ሺሕ 852 የማኅበራዊ ሳይንስ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ሳይንስ 337,404 ዘንድሮ ፈተናውን ወስደው ነበር፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ ከ700 ነጥብ 666 ከፍተኛው ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከ600 ከፍተኛው ውጤት 524 ሆኖ የተመዘገበው፡፡

አስገራሚና አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ግን በማኅበራዊ ሳይንስ ከ500 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር፣ በመላ አገሪቱ አሥር ብቻ ናቸው የመባሉ ጉዳይ ነበር፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ከ600 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመላ አገሪቱ 263 ብቻ ናቸው መባሉም እንዲሁ አሳሳቢ በሚል የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡

የፈተናውን ውጤት በፆታ፣ በትምህርት መስክና በተፈታኝ ቁጥር ከማነፃፀር ባለፈ በክልሎች እያነፃፀረ ያስቀመጠው ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ ክልል በተነፃፀሪነት ከሁሉ የተሻለ ውጤት እንደተመዘገበባቸው ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹የክልል ነገር ሆዳችሁን የሚያማችሁ ካላችሁ በማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት ካመጡ አሥር ተማሪዎች መካከል በአማራ ክልል አንድ፣ በአዲስ አበባ ስምንት፣ እንዲሁም በሲዳማ ክልል አንድ ተማሪ ናቸው፤›› በማለት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

‹‹በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ 70 በአማራ፣ 51 በኦሮሚያ፣ አንድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አሥር በደቡብ፣ ሁለት በሐረሪ፣ 117 በአዲስ አበባ፣ ሁለት በድሬዳዋ፣ አሥር በሲዳማ ክልል በአጠቃላይ 263 ተፈታኞች ከ600 በላይ አስመዝግበዋል፤›› ሲሉ ነበር ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ውጤቱን ያስቀመጡት፡፡

ከዚህ መነሻነት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃ ውጤት ስላመጡ ተማሪዎች የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በሕጉ መሠረት ከግማሽ ወይም 50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት ለዚያ ብቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በተፈጥሮ ሳይንስ ከ339,642 ተፈታኞች ውስጥ 22,936 ተማሪዎች ብቻ ወይም 6.8 በመቶ ብቻ ናቸው ያለፉት፤›› በማለት አስደንጋጭ አኃዝ ይፋ አድርገዋል፡፡

‹‹በማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከ55 ሺሕ 6878 ተፈታኞች ውስጥ 6,973 ወይም 1.3 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ያለፉት፤›› በማለት ሌላ እጅግ አስደንጋጭ አኃዝ ይፋ አድርገዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ዘንድሮ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 29,909 ወይም 3.3 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ 20,343 ተማሪዎች ወንዶች መሆናቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ልክ እንደ አምናውና ካቻምናው ሁሉ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት መገለጹ ከፍተኛ የፖለቲካ አዋራ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ አንዳንዶች ከፈተና አሰጣጥ ሒደቱ ጀምሮ ውጠት አወጣጡን የተወሰኑ ክልል ወይም ብሔሮችን ተጎጂ ያደረገ ነው በማለት እየተቹ ነው፡፡ መንግሥት በትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ስም የብዙ ተማሪዎችን የወደፊት ሕይወት በፈተና እያበላሸ ነው የሚል ትችትም ይሰጣል፡፡ ሌሎች ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የፖለቲካ አቋምን ጭምር ከጉዳዩ ጋር አያይዘው ሲራገሙ ታይተዋል፡፡

በተቃራኒው ግን ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና አሰጣጥና ዕርማት ሒደትን ትምህርት ሚኒስቴር በጥብቅ ሒደት እንዲካሄድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ትምህርት የሚገኝበትን የጥራት ጉድለት ችግር ገላልጦ ስለማሳየቱ በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር)፣ ዘንድሮ የተሠራውን ሥራ አበረታች ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ‹‹የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው፡፡ የተሠራው ሥራ ግን በአንድ በኩል እጅግ አበረታች ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ውስጥ ገባ ብለን ባለማየታችን ብዙ ችግሮችን ታቅፈን እንደኖርን አሳይቶናል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች ቀላል የማይባሉት ስማቸውን መጻፍ እንኳን የማይችሉ የሆኑት ያለ ምክንያት አለመሆኑን ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡

ከታች ጀምሮ በቅጡ ሳይፈተንና ሳይመዘን አልፎ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ፣ በግፊት ከዩኒቨርሲቲ የሚወጣ ትውልድን የትምህርት ተቋማት ማምረታቸው አገሪቱን እንዳልጠቀመ በተጨባጭ በተግባር እንደታየ ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ የትምርት ጥራት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በመንግሥት ለማሻሻል ጥረት መጀመሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀረብ ብለው ከመምህራን ጋር በተደጋጋሚ መምከራቸው፣ እንዲሁም የትምህርት ዘርፍ ሪፎርሞች መሞከራቸው ዘርፉን ይታደገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹በመቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ትምህርት ታሪክ የትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች ቀርቶ የትምህርት ኮሌጆች የሉንም፡፡ በትምህርትና በመማር ማስተማር ላይ አተኩረው የሚሠሩ የበቁ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አለመኖራቸው ነው ለትናንቱ ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ አንድ መሠረታዊ ምክንያት፤›› በማለትም ዘርፉ ይጠይቃል ያሉትን ጉዳይ ይናገራሉ፡፡ መምህራንን የበቁ መምህራን አድርጎ የሚያወጣ ካሪኩለምና የትምህርት ተቋም ቅድሚያ የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን፣ ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር) አጠንክረው ገልጸዋል፡፡

የዘርፉ ምሁራን የትምህርት ዘርፉ ሊሻሻል ስለሚችልባቸው ነጥቦች ለማንሳት የሰሞኑን የ12ኛ ክፍል ውጤት እንደ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ቢሆንም፣ በተቃራኒው ግን ጉዳዩን ለፖለቲካ ውዝግብ ሊያውሉት የሞከሩም በርካቶች ነበሩ፡፡

የትውልድ ማፍራት ሒደቱ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሆነ አደጋ ተደቅኖበታል የሚሉ መፍትሔ የሚጠቁሙ በርካቶች ቢሆኑም፣ እንደ አምና ካቻምናው ሁሉ ጉዳዩን ለብሔር ወይም ለክልል ፖለቲካ ውዝግብ ግብዓት ሊያደርጉ የሞከሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

ትምህርት በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ከፖለቲካ ሊነጠል ይገባል የሚለው ድምዳሜ ገዥ ሐሳብ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ከዚህ ይልቅ ትምህርት ለፖለቲካ ቁርሾ መነሻ ሲውል ነው በተደጋጋሚ የሚታየው፡፡ በዚህ ሁኔታ የትምህርት ጥራትን ወይም የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ የሚሞክሩ ጥረቶች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንዴት ይችላሉ የሚለው በሒደት የሚታይ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -