- ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን
- ግን ምን?
- በይፋ መናገር አልነበረብንም።
- ለምን?
- ችግሩን ምን እንደሆነ በይፋ በመናገራችን ተዋናዮቹ ራሳቸውን ለመከላከል በየቦታው ግጭት እየቀሰቀሱብን ነው።
- ታዲያ ምንድነው ማድረግ የሚሻለን ትላለህ?
- ከእርሶ ባለውቅም አንድ ሐሳብ አለኝ።
- ምንድነው ሐሳብህ?
- የማይደፈር የሚባል አንድ ዓሳ ነባሪ ብንይዝ ሌላውን ማስደንገጥ ይቻላል
- ጥሩ ሐሳብ ነው ግን …
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ዓሳ ነባሪው ማነው?
- እሱ ላይ መነጋገር ይኖርብናል።
- ምንድነው የምንነጋገረው?
- ዓሳ ነባሪው ማን እንደሆነ ወይም …
- ወይም ምን?
- ማን እንደሚሆን!
- ግን ደግሞ ለሕዝቡ ቃል የገባነው ነገር አለ?
- ቃል የገባነው ምን አለ?
- የመንግሥት ሌቦችን ለመመንጠር ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁመን ጥቆማ እንዲሰጠን ጠይቀንዋል።
- ታዲያ ምን ችግር አለው … ይጠቁም!
- ቶሎ ዕርምጃ መውሰድ ካልጀመርን ሕዝቡ ተስፋ ይቅርጥብናል ብዬ ሰግቼ ነው።
- ሌሎች የሕግ ማስከበር ዕርምጃዎችን በመውሰድ ተስፋ እንሰጠዋለና ምን ችግር አለው።
- ምን ዓይነት ‹‹ዕርምጃ ልንወስድ እንችላለን?
- አንዳንድ ቤቶችን እናሽጋለን!
- የምን ቤቶችን?
- ሺሻ ቤቶችን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከምሑራን ጋር በተደረገው ውይይት ዙሪያ ከፖለቲካ ዘርፍ አማካሪያቸው ጋር ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]
- ሰሞኑን ከዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር የተደረገውን ውይይት ተከታተልክ?
- አዎ፣ ተከታትያለሁ።
- ምን ተሰማህ?
- ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው የተሰማኝ።
- ድብልቅልቅ ስሜት ስትል ምን ማለትህ ነው?
- በውይይቱ ወቅት የተገለጹት አንዳንድ ሐሳቦች ኃላፊነት የተሞላባቸውና ሕግን መሠረት ያደረጉ ናቸው።
- እሺ፡፡
- እንዳዶቹ ግን ሕጋዊነት የጎደላቸው እንዲሁም ግለኝነት የተጫናቸው ስለሆኑ ባይነገሩ እመርጥ ነበር።
- ቆይ የትኞቹ ንግግሮች ናቸው እንዲህ ያስባሉህ?
- በምሳሌ ልጥቀስልዎት?
- ይሻላል …
- ለምሳሌ ፓርቲያችን በሚቀጥለው ምርጫ ቢሸነፍና የፓርቲያችን ሰዎች ተሰብስበው እንዴት እንለቃለን ቢሉ በግሌ ወጥቼ ተሸንፌያለሁና ኑ ሥልጣን ተረከቡ ብዬ በይፋ እናገራለሁ ያሉት ተገቢና ኃላፊነት የተሞላበት እንዲሁም ሕጋዊነትን የተላበሰ ነው።
- እሺ ሌላውስ?
- ሌላው ሲሉ?
- ባይነገር እመርጣለሁ ያስባለህን ማለቴ ነው።
- አዎ። ይኼኛውም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተሰጠ አስተያየት ነው።
- በተመሳሳይ ስትል?
- የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን የተመለከተ ነው ማለቴ ነው።
- ምንድነው ያሉት?
- ሕዝብ በድምፁ ከሰጠኝ የአምስት ዓመታት ኮንትራት ውስጥ ሦስት ዓመት ገደማ አለኝ። ከዚህ ውጪ የሚሆን ነገር የለም። በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ላሳካቸው የምፈልጋቸው ህልሞች አሉ የሚል ንግግር ተናግረዋል።
- ታዲያ ይህን ማለታቸው ምን ችግር አለው? እውነት አይደለም እንዴ?
- ሕዝብ በድምፁ ለአምስት ዓመት እንድንመራው መምረጡ እውነት ነው።
- ታዲያ ችግር ያልከው ምንድነው?
- አንደኛ ግለኝነት የተጫነው ንግግር ነው።
- ምን ማለት ነው?
- አንደኛ ሕዝብ ድምፁን የሰጠው ለፓርቲው እንጂ በግል ለእሳቸው አይደለም። ስለዚህ ፓርቲው እንጂ ሦስት ዓመት ያለው እሳቸው አይደሉም።
- እሺ ሁለተኛውስ?
- ሁለተኛ የምንከተለው ሥርዓት ፓርላሜንታራዊ ሥርዓት ነው።
- ቢሆንስ?
- ጥሩ። አንደኛ የመረጣቸው ሕዝብ ካመነበት ዛሬውኑ ውክልናውን በማንሳት ከፓርላማ ወንበራቸው እንዲነሱ ማድረግ ይችላል። ይህንን ሕጋዊ መብት በመጠቀም ውክልናውን ካነሳ ደግሞ ከፓርላማ ብቻ ሳይሆን የያዙትም ሥልጣን ያሳጣቸዋል።
- ለምን?
- ምክንያቱም የፓርላማ አባል ያልሆነ ሰው ሥልጣን መያዝ አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ …
- እሺ በሌላ በኩል … ቀጥል …
- ለዚህ ሥልጣን የመረጣቸው ፓርቲም በተመሳሳይ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ ሌላ አባል መርጦ እሳቸውን መተካት ይችላል። በእርግጥ …
- እህ … ቀጥል
- ፓርቲው ይህንን ያደርጋል ማለት አይደለም ቢያስብም በቀላሉ የሚፈጸም አይደለም። ነገር ግን
- ነገር ግን ምን?
- ግላዊነትን የሚያጎላ ነገር ባይነገር ይሻላል።
- ግላዊነት ስትል?
- ሦስት ዓመት ይቀረኛል … ከዚያ በፊት ማንም ከሥልጣኔ ሊያነሳኝ አይችልም … ላሳካቸው የምፈልጋቸው ሕልሞች አሉኝ የሚሉ ነገሮችን ባይናገሩ ማለቴ ነው።
- ምን ቢሉ ይሻል ነበር?
- ገዢው ፓርቲ ሦስት ዓመታት ይቀሩታል … ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸው ሕልሞች አሉት … ገዢው ፓርቲ በመጪው ምርጫ ከተሸነፈ ሳያቅማማ ሥ
- ልጣን ይለቃል ቢባል የተሻለ ነው።