Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን በሕገወጥ መንገድ ይገባል ከሚባለው መጠን ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነው፡፡ የአገሪቱን ሬሚታንስ ገቢ በተመለከተ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች የሚጠቁሙትም ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው ሬሚታንስ በሕገወጥ መንገድ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ብልጫ እንዳለው የሚያመለክት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደሚጠቁሙትም በውጪ አገሮች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የሚላክ የውጪ ምንዛሪ በአገራችን ኢኮኖሚና ጠቅላላ አገራዊ የምርት ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ብልጫ ያለው ሆኖ መገኘት በተፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆን አላስቻለም፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ከወጪ ንግዳችን ከሚገኘው ገቢ የበለጠ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ከውጭ ወደ አገር ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕጋዊ መስመር ተከትሎ የሚመጣ አይደለም፡፡ ይህም በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና አቅርቦት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለበት ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት አንፃር በቂ የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብና ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ማቅረብ ቢጠበቅበትም ከውጪ አገሮች የሚላክ የውጪ ምንዛሪ ላይ የተከሰቱ ተግዳሮቶች በባንኩ ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ማሳረፉንም አቶ አቤ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ጉዳይ በርካታ ተጠቃሽ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ፣ ከውጭ አገር የሚላክ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚደርሰው በጥቂት ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል መሆኑንና ደንበኞች በትንሹ እስከ አሥር በመቶ የሚደርስ የኮሚሽን ክፍያ የሚጠይቁ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የጥቁር ገበያና ሌሎች ከባንክ ውጪ ያሉ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘዴዎች መስፋፋትም ችግሩን ካባባሱ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም አቶ አቤ አስረድተዋል፡፡

‹‹የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየውም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አገሮች የሚገባው የውጪ ምንዛሪ የጠቅላላውን ግማሽ ያህል ይሆናል፡፡ አገራችንም የዚህ ችግር ተጋሪ ነች፤›› ያሉት አቶ አቤ፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታና መጠን ከፍ ሊል እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በመሆኑም ከውጭ ወደ አገር የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ እንዲገባና ከሬሚታንስ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ባንካቸው የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ 

የባንኩን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ አገራዊ ኢኮኖሚውንም ለማገዝ ባንኩ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ የሚልኩት ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ለታለመለት ሰው እንዲደርስ የሚያስችለውን አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ 

የሬሚታንስ መጠንን ለመጨመርም ሆነ ከውጭ ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች ያለምንም ክፍያ መጠቀም የሚያስችላቸው አዲስ ቴክኖሎጂ ‹‹ኢትዮ ዳይሬክት›› የተባለ ዲጂታል ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት መተግበሪያ ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት ይህንን መተግበሪያ አስመልክቶ ሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስተዋውቀዋል።

በመግለጫ ላይ እንደተጠቆመውም ይህንን የዲጂታል ገንዘብ መላኪያ ቴክኖሎጂ ያበለፀገው ኤግል ላይን ሲስተምስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን አገልግሎቱ በሐዋላ ኤጀንቶችና በስዊፍት በኩል ይላክ የነበረውን የገንዘብ አላላክ ዘዴ የሚለውጥና ጥሩ አማራጭ ሆኖ የቀረበ ነው።

እስካሁን ከውጭ ወደ አገር የሚላክ ገንዘብ በሐዋላ ወኪሎችና በስዊፍት አማካይነት ከባንክ ወደ ባንክ የሚደረግ እንደነበር የገለጹት አቶ አቤ በእነዚህ ገንዘብ መላኪያ ዘዴዎች ገንዘብ ሲላክ ደግሞ ለአገልግሎቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ጥቂት የማይባሉ ተገልጋዮች ሌላ አማራጭ ሲጠቀሙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ከመላክ ወደ ጥቁር ገበያ እንዲሄድ በማድረግ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚገባው ሬሚታንስ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ 

እንደ አቶ አቤ ገለጻ በሐዋላና በስዊፍት ከባንክ ወደ ባንክ የሚተላለፈው የእስካሁኑ አሠራር በዋናነት ለገንዘብ ላኪዎች የሚመች ባለመሆኑና ተጨማሪ መላኪያ ወጪን የሚያስከፍል በመሆኑ ላኪዎች ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ማስገደዱን፣ በዚህም በሕጋዊ መስመር የሚገባው የሬሚታንስ ገቢው በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስተዋወቀው ‹‹ኢትዮ ዳይሬክት›› የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ ይህንን የገንዘብ ላኪዎች ችግር በመገንዘብ መፍትሔ የሚሰጥ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ከውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ለሚልኩ ሰዎች በተሻለ ተመራጭ እንደሚሆንና የሬሚታንስ ገቢውን ሊያሳድግ እንደሚችል ታምኖበታል።

አሁን ግን በኢትዮ ዳይሬክት በሞባይል ብቻ በመጠቀም ገንዘብ መላክ የሚያስችለው አሠራር መተግበር መጀመሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ ወደ አገር ገንዘብ የሚልኩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የትም መሄድ ሳያስፈልጋቸው ሞባይላቸውን በመጠቀም ብቻ በኢትዮ ዳይሬክት ገንዘብ መላክ እንደሚችሉ ተገልጿል። ይህ በመሆኑም ላኪዎች ከዚህ ቀደም ያጋጥማቸው የነበረውን ጫናና ወጪ መቀንስ እንደሚችሉ፣ ገንዘብ ለመላክ ወደ ባንክ ወይም ወደ ሐዋላ ኤጀንት መሄድ ሲያስፈልጋቸው በቀለሉ ገንዘብ ለመላክ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ የሐዋላ ኤጀንቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እርስ በርስ እየተፎካከሩ በአገልግሎት ክፍያ ላይ የተወሰነ ቅናሽ ቢያደርጉም አሁንም ቢሆን ገንዘብ ከውጭ ለመላክ የሚጠይቀው ኮሚሽን ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

ይህን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል ብዙ መድከማቸውን፣ ባንካቸውም በጉጉት ሲጠብቃቸው ከነበሩ ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ አቤ፣ ‹‹ኢትዮ ክሬዲት›› ዲጂታል ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት የባንኩ የዘመናዊ አገልግሎት ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

የ‹‹ኢትዮ ክሬዲት›› ዲጂታል ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎትን የሚጠቀሙ በውጭ ያሉ ላኪዎች ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚጠይቁት ክፍያ እንደማይኖር ገልጸዋል። ይህም ማለት በሌሎች አማራጮች ገንዘብ ሲልኩ እንዲከፍሉ የሚጠየቁት ኮሚሽን የሚያስቀርላቸው እንደሆነ አስረድተዋል። የተለያዩ ገንዘብ ላኪዎች፣ ለሐዋላ አስተላላፊዎች የአገልግሎት ክፍያ ላለመክፈል ሲሉ፣ ሕጋዊ ያልሆኑ አማራጮችን እንዲከተሉ ማድረጉን ገልጸዋል። 

ባንካቸው የጀመረው አዲስ የገንዘብ መላኪያ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ በአጠቃላይ ሲታይ ገንዘብ ለመላክ አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎችን የሚያስቀር፣ እንዲሁም አገሪቱ ከሬሚታንስ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያድግ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ይህንን ቴክኖሎጂ ለማስጀመር ከገጠሟቸው ብዙ ውጣ ውረዶች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ለማግኘት ረዥም ጊዜ መውሰዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎቱ የዓለም ዋነኛ የክፍያ ተዋንያን ከሆኑት ቪዛና ማስተር ካርድ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የሚሠራ እንደመሆኑ መጠን እነሱን አሳምኖ ይሁንታቸውን ለማግኘት ብዙ ድካም እንደነበረው አስረድተዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይዞት የመጣው ቴክኖሎጂ የእነሱንም ገበያ የሚነካ ከመሆኑ አንፃር የእነሱን ይሁንታ ማግኘት ቀላል አልነበረም ብለዋል። ቆይቶም ቢሆን አገልግሎቱን ከእነዚህ ዋነኛ የዓለም የክፍያ ተዋንያን ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ተደርሶ አገልግሎቱን ማስጀመር የተቻለ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ካርዶችም አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡  

ባንኩ፣ ከቪዛና ማስተር ካርድ ኩባንያዎች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በውጭ የሚገኙ ላኪዎች የኢትዮ ክሬዲት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው መላክ የሚችሉት የገንዘብ መጠን ከአምስት ዶላር እስከ አንድ ሺሕ ዶላር ድረስ አንደሆነ አቶ አቤ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቴክኖሎጂውን ለማበልጸግ ሲወሰን እስከ 20 ሺሕ ዶላር መላክ እንዲያስችል ታሳቢ በማድረግ ቢሆንም፣ ለጊዜው ተባባሪ የውጭ የክፍያ ካርድ አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያዎች የፈቀዱት የገንዘብ መጠን እስከ 1000 ዶላር ብቻ በመሆኑ በዚሁ መጠን አገልግሎቱ በዚሁ መጠን ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል።

እስከ 1000 ዶላር መላክ እንዲቻል የፈቀዱትም የሚላከው ገንዘብ ለቤተሰብ ድጋፍ እንደሚውል በመረዳታቸው ነው ያሉት አቶ አቤ፣ በተፈቀደው የገንዘብ መጠን በሚገባ መጠቀም ከተቻለ የማይናቅ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባንኩ ያቀደው የገንዘብ መጠን ባይፈቀድም በውጭ የሚገኙ ዘመድ አዝማዶች አብዛኛውን ጊዜ ለቤተሰብ የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከ1000 ዶላር የማይበልጥ በመሆኑ በዚህ መጀመሩ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ መጠኑን እንዲያድግ ድርድር እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በኢትዮ ክሬዲትን በመጠቀም ገንዘብ ይላክባቸዋል ተብለው በመጀመርያው ዙር የተለዩት በርካታ ዳያስፖራዎች ያሉበትና ከፍተኛ የሐዋላ መጠን ይላክባቸዋል የተባሉ ዘጠኝ አገሮችን በማስቀደም ነው፡፡ እነዚህም ካናዳ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጣልያን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ስዊድን ናቸው፡፡ በቀጣይ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር በመነጋገር ሌሎች አገሮች እንዲካተቱ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው ዓለም ከ750 ከሚሆኑ የውጭ ባንኮች ጋር የሚሠራ በመሆኑ በዚህ መሠረት ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ገንዘብ ለመላክ ሰፊ ዕድል ያለው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ 

ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ የሚቀበሉ ሰዎች ገንዘቡን የሚያገኙበት ሦስት ዋና ዋና አማራጮችን ባንኩ እንዳስቀመጠም ተገልጿል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አቤ ገንዘቡን ለመቀበል ካቀረቡት አማራጮች መካከል አንደኛው አማራጭ የሚላከውን ገንዘብ በቀጥታ በተቀባዩ የሒሳብ አካውንት ማስገባት የሚያስችል ሲሆን፣ ሁለተኛ አማራጭ በባንኩ በሚጀምረው የሲቢኢ (CBE) ዋሌት የተሰኘ የሞባይል ባንክ አገልግሎት የሚከፈል ነው። የሲቢኢ ብር ዋሌት አገልግሎት በቅርቡ ይጀምራል ተብሏል፡፡

ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ ተቀባዮች ገንዘባቸውን በጥሬው እንዲቀበሉ የሚያስቻል ሲሆን፣ በኢትዮ ዳይሬክት ገንዘብ ሲላክ ተቀባዮች ገንዘቡን በጥሬ ገንዘብ መቀበል እንዲችሉ ይደረጋል ብለዋል። ለጊዜው ይህንን አገልግሎት መጀመር ያለመቻሉ ተገልጿል፡፡ ገንዘብ ከውጭ የተላከለት ሰው ገንዘቡን በጥሬ ገንዘብ በቀጥታ ለመቀበል የሚያስችለውን አማራጭ አንድ ላይ መጀመር ያልተቻለው ተጨማሪ ድርድርን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ተብሏል። በአሁኑ ወቅት ከተባባሪ የክፍያ ካርድ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ጋር ድርድር እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ድርድሩ እንደተቋጨ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ 

በጥሬ ገንዘብ ለመቀበል የሚያስችለው ሲስተም አሁን ላይ እንዳይተገበር ምክንያት የሆነው ኩባንያዎቹ በሬሚታንስ መልክ የሚገባው ገንዘብ ለማን እንደተላከ ለማረጋገጥ ስለፈለጉ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አቤ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡ ለቤተሰብ የሚላክና ሌላ ዓላማ የማይውል መሆኑን በማሳመን ላይ በመሆኑ በጥሬ ገንዘብ ለመቀበል የሚያስችለው ሲስተም በቅርቡ ይተገበራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ 

እንደ አቶ አቤ እምነት ከሆነ ኢትዮ ዳይሬክት ዓለም አቀፍ ዲጂታል ገንዘብ መላኪያ ቴክኖሎጂ ገንዘብ ላኪዎችንና ተቀባዮችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ ከመሆኑ ባሻገር የባንኩን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ያሳድጋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስተዋወቀውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ በተመለከተ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በቴክኖሎጂው ስኬታማነት ላይ ጥርጥር የላቸውም። ነገር ግን ከሬሚታንስ አገልግሎት የሚገኝ የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ የቻለበት ዋናው ምክንያት በውጭ የሚገኙ ላኪዎች ገንዘብ ለመላክ እንግልት ገጥሟቸው ወይም የአገልግሎት ክፍያ አማሯቸው እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

በሬሚታንስ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደረገው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወሰነው የብር የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው ተመን መካከል ያለው ልዩነት እንደሆነ ይገልጻሉ። 

በኢትዮጵያ ለሚገኝ ቤተሰቡ አንድ መቶ ዶላር የሚልክ ሰው ታሳቢ የሚያደርገው ቤተሰቡ እጁ ላይ ምን ያህል ይደርሰዋል የሚለውን እንደሆነ የሚገልጹት አንድ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚላከው አንድ መቶ ዶላር በባንክ መስመር ከሚላከው በከፍተኛ መጠን ልዩነት ያለው ምንዛሪ የሚያስገኝ በመሆኑ ላኪዎች ይህንኑ ጥቅም ለመምረጥ እንደሚገደዱ ያስረዳሉ። 

በሬሚታንስ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው ተመን መካከል ያለው ልዩነት በአሁኑ ወቅት በአማካይ ከ40 በመቶ በላይ እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው፣ ይህ ልዩነት ካልጠበበ ላኪዎች አሁንም ሕጋዊ ያልሆነውን አማራጭ እንደሚከተሉ ገልጸዋል።

ይህንን ልዩነት ማጥበብ ካልተቻለ መንግሥት ለሬሚታንስ አግልግሎት ብቻ ልዩ የምንዛሪ ተመን በመወሰን ልዩነቱን ማጥበብ እንዳለበት በተለያዩ መድረኮች ምክረ ሐሳቦች እንደቀረቡለትም ያነሳሉ። የንግድ ባንክ አዲስ ይፋ ያደረገው ገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ የበለጠ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው መንግሥት ከላይ የቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ አዲሱ የንግድ ባንክ ቴክኖሎጂ የአገልግሎት ክፍያ የማይከፈልበት በመሆኑ ገንዘብ ላኪዎች ከጥቁር ገበያው የሚያገኙትን የምንዛሪ ልዩነት ቀሪ በተደረገላቸው የአገልግሎት ክፍያ በተወሰነ ደረጃ ማካካስ እንደሚችሉ አስበው ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ይበረታታሉ ብለዋል። 

ነገር ግን መንግሥት በሬሚታንስ ለሚገባው የውጭ ምንዛሪ ብቻ ከፍ ያለ የምንዛሪ ተመን ቢያስቀምጥ ንግድ ባንክ ያስተዋወቀው ቴክኖሎጂ የበለጠ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሰል ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎቶችን እያስፋፋ መሆኑ ተጠቅሷል። 

የባንኩ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በየዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት በስድስት ወር ብቻ በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ያስተላለፈው የገንዘብ መጠን ከመቶ ፐርሰንት በላይ ብልጫ ማሳየቱ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡  

ከባንኩ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2015 ግማሽ ዓመት ብቻ ደንበኞቹ በሁሉም ዲጂታል አማራጮች 365.5 ሚሊዮን ግብይቶችን በመፈጸም፣ 1.3 ትሪሊዮን ብር አንቀሳቅሰዋል።

የባንኩ ደንበኞች በ2014 የሒሳብ ዓመት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት 178.7 ሚሊዮን ግብይቶችን በመፈጸም 386.4 ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በ2015 ግማሽ ዓመት የተፈጸመው ግብይትና የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በ104 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች