Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ›› ስለተባልን፣ በለቅሶ የተቀላቀልናት ዓለም ላይ የኑሮ ትግሉን ተያይዘነዋል። የሕይወትን ትርጉም፣ የመኖርን ጣዕም አጣርተን ሳናውቅ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ነገን እንጓጓለን። መነሻውን ባልደረስንበት የጉጉት ሰቀቀን ጎዳናው ላይ ወዲያ ወዲህ እንመላለሳለን። ግራ የገባው፣ በከፊል የገባው የመሰለው፣ ምንም ያልገባው፣ የሚሄድበትን የማያውቀው፣ እግሩ እንደመራው የሚራመደው፣ መድረሻውን የወሰነው፣ እንኳን መድረሻ መነሻ የሌለው ሳይቀር እየተግተለተለ ይተራመሳል። ዕፎይታ የናፈቀው የወገናችን ኑሮ ዛሬ ደግሞ ከአደገኛ ጽንፈኝነት ጋር ትንቅንቅ ገጥሟል። የትናንቱ አሰልቺ እንግልት ዛሬም በደከመ ጉልበት ሊደገም ጎህ ቀዷል። ለአንዳንዱ ደግሞ ገና ሳይነጋ መሽቶበታል። አስቀድሞ የክስረት ሒሳቡን ላወራረደ የሰማይ ዓይን መግለጥና የምድር ዓይን መክደን ትርጉም አይኖራቸውም። ብቻ ጎዳናው የተሸናፊውም የአሸናፊውም መድረክ ስለሆነ፣ ይኼኛው ከዚያኛው እኩል ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ታክሲ ይጠብቃሉ። ከጽንፈኝነት ራቁ ቢባልም ሰሚ ያለ አይመስልም፡፡ ወይ አበሳችን!

አሁንም አሁንም አፍንጫውን የሚጎረጉረው ከሲታ ወያላ በታክሲዋ ዙሪያ እየተሽከረከረ ይቁነጠነጣል። አስቀድሞ እሱ ራሱ በከፋፈታቸው መስኮቶች በኩል አንገቱን ያስገባና ተሳፋሪዎችን ይለክፋል። ‹‹እሺ እዚህ ጋ! አንችኛዋ ትንሽ ጠጋ በይ!  እዚያ ጋ! ሄይ ጩጬ ተማሪዎች! ዋ! መጻፊያችሁን ቦርሳችሁ ውስጥ ክተቱ። ነግሬያለሁ ወንበር ላይ ብትጽፉ፡፡ በተለይ ፖለቲካን በተመለከተ አንድ ነገር ጻፉና እናንተን አያድርገኝ። ይኼን ጊዜ ስንት ያልሠራችሁት የቤት ሥራ አለ…›› ይላል። ደግሞ በዋናው በር በኩል ዞሮ፣ ‹‹ገና በጠዋቱ እንዳንለካከፍ መልስ አዘጋጁ። አዳሜ በብላክ ማርኬት እየዘረዘርሽ አገር ማራቆት ለምደሽ፣ እኔን መልስ ብትሉኝ አልሰማችሁም…›› ይላል። ታክሲው ውስጥ 20 ሰዎች ታጭቀው እሱም ሆነ እነሱ ምንም ሳይመስላቸው፣ ‹‹ዛሬ ቁርስ የበላኸው የፍየል ምላስ ነው እንዴ ፍሬንድ? ይልቅ ሞልቷል ሳበው በለው…›› ይላል አንድ የቸኮለ ወጣት ተሳፋሪ፡፡ ይኼኔ ታክሲያችን መንቀሳቀስ ትጀምራለች። እኛም ምንም ሳይሰማን ጉዞ ጀምረናል፡፡ ጉዞ ከተባለ ለማለት ነው!

ደላላ፣ ነጋዴ፣ ሸማች፣ አሠሪ፣ ሥራ ፈላጊ፣ ወዘተ. በታክሲያችን ጣሪያ ሥር ታጭቀን ጉዞ ጀምረናል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመች ወጣት፣ ‹‹ይኼ የፖለቲካ ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ጋር የተያያዘ አይደለም…›› ስትል ፈዘዝ ብለን የነበርነው ተነቃቃን። ሁላችንም እርስ በርስ ተያይተን ወደ ልጅቷ አፈጠጥን። ልጅት ቀጥላለች፣ ‹‹ነገር ግን መስዋዕትነት ተከፍሎበታል የተባለውን ዴሞክራሲና ነፃነት እንዳሻቸው ሲፈነጩበት ማየት ከምንም በላይ ስለሚያም ነው። አሁንም ድሮም ሆነ ወደፊት ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን በፅኑ እቃወማለሁ…›› ብላ ስታበቃ እጇን ወደ ላይ ማንሳት ነበር የቀራት። ጨዋታዋ አብሯት ከተቀመጠ ጎልማሳ ጋር ኖሯል። መጨረሻ ወንበር ለተቀመጡ ተሳፋሪዎች አንዱ፣ ‹ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሰላማዊ ሠልፍ ስንሳተፍ ሌላው ቢቀር እንደ እሳት የሚፋጀው የኑሮ ውድነት ሳይታዘበን ይቀራል ትላላችሁ? ኧረ አንድ በሏት…› ይላል። ‹‹ሰው ያለ ከልካይ የበላ የጠጣውን የሚለጥፍበት የፌስቡክ ግድግዳው አልበቃ ብሎት፣ ደግሞ ጎዳናውን በብሶት ‘ፖስት’ ካላተራመስኩት ይላል። መተሳሰብ እኮ ትተናል…›› ስትል አንዲት ወይዘሮ የእንኑርበት መልዕክቷን ታስተላልፋለች። ያለንበት ሁኔታ ያሳሰባት አትመስልም! 

ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹ሰው ለበላው ቁርስ አያዝንም? ምናለበት ምሳ ሰዓት ሳይደርስ በነገር እየተነቋቆረ ለረሃብ ባይቸኩል?›› እያለ በማያገባው ሲገባ ሾፌሩ፣ ‹‹ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው ብላለች ዘፋኟ። ይልቅ ወሬውን ትተህ ‘ስፖክዮውን’ አስተካክለው አይታየኝም…›› ብሎ ኩም ያደርገዋል። ከወገቡ በላይ በመስኮት ሾልኮ ሲወጣ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት መምህራን ተሳፋሪዎች ስለኑሮ ውድነት ያወራሉ። ‹‹መምህርነት ድሮ ቀረ፡፡ አሁንማ ኑሯችን ትላለህ ፖለቲካው፣ ትዝብታችን፣ ሐዘናችን ሳይቀር የጽንፈኞች ወሬ ሸፍኖታል። ችግሮቻችን ሁሉ እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ አገር አተራማሾች ከየአቅጣጫው እየተነሱ ችግር ሲፈጥሩ ተስፋ ያስቆርጣል…›› አንዱ መምህር፡፡ ይህን ጊዜ የባከነ ሰዓት ላይ መድረሳችን ታወቀን። በስንቱ እንደ ምንባክን አልገባን አለ እኮ!

 ወያላው ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። ጋቢና የተሰየሙትን ሴቶች ሾፌሩ እንዳትቀበል ስላለው ወያላው ተነጫንጯል። ‹‹በቃ አጠገቡ ሴት ከተቀመጠች እኮ በነፃ ‘አላስካ’ ደርሶ ይመለሳል፣ ምን አገባኝ እኔ?›› እያለ ለራሱ እያጉተመተመ መጨረሻ ወንበር ተደራርበው ወደ ተቀመጡት ታዳጊዎች ሲደርስ ‹‹ሒሳብ!›› ብሎ ጮኸባቸው። ነገረ ሥራቸው ሁሉ ፈገግ የሚያሰኝ እነዚያ ታዳጊዎች የሞባይል ስልካቸውን እየጎረጎሩ ቀና ብለው እንኳ ሳያዩት ዝም አሉት። ‹‹ምድረ ጩጬ አትከፍሉም?›› ወያላው ደገመላቸው። “ቆይ አንዴ፣ ‘ሪከርድ’ ልሰብር ስለሆነ ነው እሰጥሃለሁ…›› ብሎ አንደኛው መለሰ። ወይዘሮዋ አፏን ሸፍና ሳቀች። አጠገቧ የተሰየመች ቀዘባ ደግሞ ፈገግ ብላ፣ ‹‹አይ ኢትዮጵያ አገሬ፣ በዱር በገደሉ ለነፃነትሽ የተዋደቁ አርበኞች ልጆችሽን ባየሽበት ዓይን፣ ዛሬ ‘የጌም’ አርበኞች ሲተኳቸው ስታይ ምን ትይ ይሆን?›› ብላ ወደ ሰማይ ቀና አለች። ሰማዩ ምን እንዳላት እንጃ!

መሀል መቀመጫ ያለ ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹እነሱ ምን ያውቃሉ? እኛ ነን የጠቀምናቸው እየመሰለን በዚህ ዕድሜያቸው ሞባይል ገዝተን የምንሰጥ። ወላጆች ነን ልጆቻችንን እያበላሸናቸው ያለነው…›› ብሎ ተነፈሰ። አኳኋናቸው ሁሉ ፈገግታን የሚያጭረው ታዳጊ ተማሪዎችን ወይዘሮዋ ጎንበስ ብላ አለሳልሳ ጥያቄ መጠየቅ ጀመረች። ‹‹ማነው ስምህ?›› ይነግራታል። ‹‹አንተስ?›› ያም ይመልሳል። ‹‹ወንድማማቾች ናችሁ?›› ስትላቸው፣ ‹‹መንታዎች ነን…›› ሁለቱም ተመሳሳይና እኩል ናቸው፡፡ ‹‹ስንተኛ ክፍል ናችሁ?›› ‹‹አምስት!›› ይመልሳሉ። ‹‹ወደፊት ስታድጉ ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?›› ከማለቷ ሁለቱም ከሞባይል ስልኮቻቸው ዓይኖቻቸውን ነቅለው፣ ‹‹ባለሥልጣን!›› አሉዋት። ለምን እንደምትስቅ አንዳንዴ እሷ ራሷ የገባት የማትመስለው ወይዘሮ፣ ይኼንን ስትሰማ ከጣራ በላይ ተንከትክታ፣ ‹‹ሌላስ?›› ብትላቸው፣ ‹‹ጋንግስተር!›› ብለዋት አረፉት። የባሰ አታምጣ ማለት አሁን ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። ታዳጊዎቹ ወንድማማቾች ሒሳባቸውን ከፍለው ወርደው ሲጓዙ በሩቁ ላያቸው ልዩ ስሜት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ወልዶ ያልሳመን ያስተክዛሉ። ወያላው በእነሱ ምትክ ሌላ ሰው ያሳፍራል። አዲሱ ተሳፋሪ፣ ‹‹ስማ ገና አልተቀመጥኩም እኮ፡፡ ችግሩ ምንድነው ስል አይ አንተ ከሄድክ ስለማትመለስ ‘ኬዝህን’ አላመነበትም አትለኝም አስተርጓሚዋ። ኧረ ትንሽም ቢሆን ድርጅት አለኝ ይኼው የባንክ ወጪና ገቢዬ ብል ማን ይስማኝ? ለነገሩ እነሱ ምን አለባቸው ለኮቴ የሚቀበሉት ብቻ እኮ በዓመት የትናየት ሚሊዮን ብር መሰለህ? በትንሹ በአምስት ሺሕ ብር በቀን 100 ሰው ይገባል ብለህ አስላው፡፡ ማን መፅዋች ማን ተመፅዋች እንደሆነ እኮ ነው ግራ የሚገባህ። ግድ የለም ቆይ…›› እያለ በብስጭት በሞባይል ስልኩ ያወራል። ‹‹የአሜሪካ ‘ቪዛ’ ተከልክሎ እኮ ነው…›› አለኝ ይኼን ያህል ሰዓት ዝምታ ውጦት የተቀመጠ አጠገቤ የነበረ ተሳፋሪ። ተሳፋሪው ስልኩን ከመዝጋቱ ደግሞ ይባስ ብሎ ያም ያም ያፅናናው ጀመር። ‹‹ገና ከጦርነት ውስጥ ወጥተን ሳናበቃ ቪዛ መጠየቁ ይገርማል፡፡ ይኼኔ እኮ የግንባሩ ሥር እንደተገታተረ ይሆናል የሄደባቸው…›› እያለ የሚስቀው አጠገቤ የተቀመጠው ነው፡፡ ሳቅ አንተ ምን አለብህ!

‹‹አይዞን ነገም ሌላ ቀን ነው…›› ሲል አንዷ ቆንጂት ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ምንም አይደለም፣ እነሱም እኛኝ ቪዛ ለምነው የሚመጡበት ቀን ሩቅ አይደለም…›› ትለዋለች። ከወደፊት የተቀመጠ ስለቢዝነስ አብዝቶ የሚያወራ ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹እህቴ አንቺ የምትይው ገና ሩቅ ነው፡፡ ወንድሜ አይዞህ እኔም እንዳንተ ሆኜ ነበር። ምን አደረግኩ መሰለህ? አንድ የአውሮፓ አገር ቪዛ ጠይቄ ከዚያ ላጥ አልኩና ዲሲ ገባሁ። ዋናው ተስፋ ሳትቆርጥ በሩን በደንብ ማንኳኳት ነው። አንተ ደህና ሆነህ ጠብቅ እንጂ መሳካቱ አይቀርም…›› አለው። ሰውየው ከተከለከለው ቪዛ ይልቅ የሚሰማቸው የማፅናኛ ቃላት ብዛት እንዳስደሰተው ያስታውቃል። ‹‹የእኛ ሰው ግን አሜሪካ ሲባል ምን ሆኖ ነው እንዲህ ጆሮው የሚቆመው…›› ይለኛል አጠገቤ ያለው ነገረኛ፡፡ እንጃ!

ይኼኔ ከየት መጣ ሳይባል ከኋላችን አንድ አይሱዙ መጥቶ ተላትሟል። የታክሲያችን የኋላ መስታወት ሿ ብሎ መሬት ላይ ተበትኗል። ተሳፋሪዎች ‘ምን መዓት ነው?’ እየተባባሉ እርስ በርስ ይተያያሉ። ትንሽ ስንረጋጋ ተሽቀዳድመን ከታክሲያችን ወረድን። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች ማንኛቸውም አለመጎዳታቸው ቢያስደስተንም፣ የገጨንን መኪና አሽከርካሪ ጤንነትና ሕጋዊነት ለማጣራት ስንሰባሰብ ወጣቱ የአይሱዙው ሾፌር ጥምብዝ ብሎ ሰክሯል። የትራፊክ ፖሊስ ደርሶ መንጃ ፈቃድ ሲጠይቀው የቀበሌ መታወቂያ ካርዱን አውጥቶ ሰጠው። ለወሬ የተሰበሰበው መንገደኛ ይኼን ሲያይ በሳቅ ይንከተከታል። ድንጋጤው አመድ ያስመሰላት ወይዘሮ፣ ‹‹እኮ በዚህ አያያዝህ እንኳን ሰው ሆነህ ልትኖር ወግ ያለው ሞት ለመሞትም ዕድል የምታገኝ ይመስልሃል?›› ብላው እያማተበች ራቀች። ‹‹ለነገርና ለሞት ቸኩለን እንዴት ይሆናል?›› ብላ ሁሉን አሳታፊ ጥያቄ የምትጠይቀው ደግሞ ቆንጂት ናት። ‹‹ሳይነጋ አይምሽባችሁ የተባለው ለካ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ነው?›› ይላል ሌላው፡፡ ማን ሰምቶ!

በዚህ መሀል አንድ ከየት መጣ የተባለ ወፈፌ ብጤ፣ ‹‹መኪና ቢጋጭ ይሠራል፣ ሰው ቢጎዳ ነበር የሚያሳዝነው…›› ብሎ፣ ‹‹ለነገሩ አንዳንዱ እኮ ግዑዝ ነው፣ አሁን ደግሞ እያለ የሌለ የሚመስል እየበዛ ነው… በገዛ ንብረቱ ላይ እንደ ቅርጫ ዕጣ ብትጣጣሉ የማይገባው ግዑዝ እኮ ነው መንገዱን ሞልቶ በደመነፍስ የሚራመደው… ከግጭት ታቀብ ሲባል ዱላ የሚያነሳው… የባለሙያ ምክር ስማ ሲባል ጆሮውን የሚደፍነው… ሕግጋት አክብር ሲባል የሚጥሰው… በጣም እየበዛ ነው…›› እያለ ሲስቅ በዝምታ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ለመሆኑ ይህ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን! መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት