በበድሉ አበበ
አንዳንዶች እንደዚህ ይሉኛል፡፡ እገሌ እኮ በጣም ጤነኛ ነው፡፡ ፍፁም ጤናማ፡፡ አንድም ቀን እንኳን ‹‹አመመኝ›› ሲል፣ ‹‹ላቦራቶሪ ታየሁ›› ሲል፣ ‹‹አደጋ ገጠመኝ›› ሲል፣ ‹‹ሕክምና ሄድኩ፣ ሄጄም ዳንኩ›› ሲል ሰምቼው አላውቅም፡፡ ስለዚህ፣ ‹‹ጤናማ ነው፣ ምንም አያመውም›› ይሉኛል፡፡
አያርፉም ይቀጥላሉ፣ ‹‹…እንዲያውም አንድ ጊዜ ሲያወራኝ የታመምኩት በ1991 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት፡፡ ያመመኝም የወባ ወረርሽኝ እንደ አገር ስለነበረ ወባ ነው፡፡ በእርግጥ ያኔ አልጋ ይዤ ነው የዳንኩት፡፡ በወቅቱ ብዙ ሰው ታሞ ሞቷል፡፡ እኔም ያኔ ነው ያመመኝ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ፈጽሞ አሞኝ አያውቅም፣ ሰይጣን ይህንን አይይብኝና…›› ብሎናል ይሉኛል፡፡
እኔም አንገቴን በመነቅነቅ አዎንታዬን እየገለጽኩ ባለመስማማት መስማማት ውስጥ እዋልላለሁ፡፡ በውስጤ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ትንሽም ብትሆን መርምሬ ጤናም ብትሆን ትንሽ ተምሬአለሁና፣ ‹‹ኧረ ተው በማይታይ መጠን በሽታማ›› አለበት እላለሁ በውስጤ፡፡ በማይታይ መጠን እሱም በማያውቀው መጠን እንደሚያመው መቶ በመቶ ጤናማ የሰው ልጅ ሊሆን ስለማይችልና ‹‹የማይታይ መጠን የቫይረስ ብዜት›› የሚባል ዓይነት የመታመም በሽታ አውቃለሁና በማይታይ መጠንማ ያመዋል እላለሁ፡፡ በማይታይ መጠን ስል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሰው ልጅ ፍፁም ክፉ አይደለም፡፡ መቶ በመቶ፣ ፈጽሞ አንድ መቶ በመቶ ሰናይ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እጅግ መልካም የሆነው ሰው በማይታይ መጠን ትንሽ ተንኮል አያጣም፡፡ እጅግ ክፉ ሰዎችም በማይታይ መጠን እንጥፍጣፊ በጎ ነገሮችን አያጡም ለማለት ነው፡፡
ደግሞም እንዲህ ይሉኛል፣ ‹‹እገሌኮ እጅግ ትሁትና በጎ ሥነ ምግባር ብቻ እንዳይመስልህ ያለው፣ ከትህትህናው ብዛት ራሱን ለሰዎች ሲል እጅግ የሚጎዳ ሰው ነው››፡፡ ይኼ ልጅኮ እንደዚህ ይባላል ስላቸው፣ ‹‹በፍፁም እሱ ይኼን አደረገ ብትለኝ አልሰማህም፡፡ ምክንያቱም ዕድገቱም፣ ኑሮውም፣ ሕይወቱም ከግብረ ገብነት ጋራ የተሳሰረና ያልተበረዘ ለራሱም ለቤተሰቡም፣ ለማኅበርሰቡም ለአገሩም እጅግ ትሁት ነው፣ በፍፁም ቅን ያልሆነ ነገር አያደርግም ይሉኛል፡፡ የአገሩን ባህሎች፣ እሴቶች፣ ሃይማኖቶች በሙሉ ራሱ በትህትና ነው የሚያልፋቸው፡፡ እሱማ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሕዝቦች፣ ባህሎች፣ ሕጎች፣ ሃይማኖቶች፣ በጎ በጎ ሥነ ምግባሮችን ይገዛል፡፡ ሕግም፣ ሃይማኖትም፣ ባህልም አክባሪ ነው፡፡ እጅግ በጣም ስልህ፡፡ … እኔኮ እንደ እሱ በሆንኩ እኮ ነው የምልህ፡፡ ሰው ያከብራል፣ ራሱን ያከብራል፣ የመሥሪያ ቤቱንም የአገሩንም ሕግ ያከብራል፡፡ በቤትም በውጭም የተመሰከረለት ነው፡፡ እስቲ ዝም ብለህ አንድ ሁለት ሰው ጠይቅ፣ እኔ ያልኩህን ነው የሚደግሙልህ፡፡ በዚህ በኩል ምንም ነቀፋ የለበትም፡፡ የሚነቅፉት ካሉ እንኳን የሚነቅፉት ወይ ቀንተውበት አልያም በሌላ ምክንያት ይሆን ይሆናል እንጂ በጭራሽ እሱ ይኼን አያደርግም፡፡ እሱ ትሁት አይደለም የሚሉህ ምናልባትም የእሱን ትህትና ሊወስዱበት ወይም ሊጠሩበት ፈልገው ይሆናል እንጂ እሱ እጅግ ትሁት ነው፡፡ … እንዲያውም የእሱን ትህትናስ እነሱም ትንሽ ትንሽ በወሰዱ እላለሁ ከእሱ ቀንሰው እላለሁ›› ይለኛል ሌላኛው፡፡ አለፍ ስል አሁንም ስለሱ ሰማለሁ፡፡ ትንፋሽ ወስደው ይቀጥሉልኛል፡፡
‹‹ሰውን ቀና ብሎ እንኳን የማያይ፣ ትንሽ ትልቁን፣ ደሃ ሀብታሙን፣ የተማረ ያልተማረውን… ሁሉንም አክባሪ ነው… እንኳን ሌላ ሰው እኔ እንኳ ጥሎብኝ ለረዥም ጊዜ ተከታትዬዋለሁ ስልህ! …፡፡ ፍፁም ሐሰት ነው እሱ እንዲያው እንዲህ ዓይነት ነገር ፈጽሞ አይነካካውም… humble ነው በጣም እጅግ humble…›› ይሉኛል፡፡ እንደ ተጠራጥርኳቸውና ሙሉ በሙሉ እንዳላመንኳቸው ሲረዱ የእሱን የመልካም ነገር መገለጫዎች በሙሉ ይዘረዝሩልኛል፡፡ የታዛዥነቱን መጠንም ሁለቴ ይገልጹልኛል፡፡ የትዕግሥቱን ወሰን አልባነት ያጠናክሩልኛል፡፡ ለሰው ያለውን ፍቅር፣ ለቤተሰቡና ለወዳጆቹ የከፈለውን መስዋዕትነትም ይጠቅሱልኛል፡፡ አስትራቂነቱም፣ አቀራራቢነቱም፣ መልካም ስሙ፣ መልካም ቤተሰቡ፣ ስኬቱ ልምዱ አቃፊነቱም አይቀራቸውም ስለሱ ሲመሰክሩልኝ፡፡ ኧረ ተው እግዜር አደረጋችሁትኮ እናም በማይታይ መጠንም ቢሆን ጥቂት መልካም ነገሮችማ ያንሱታል በደንብ ቀርበን ብናጠናው እላቸዋለሁ፡፡
በመሀል የልጅነት ዘመኔ መምህር፣ ተደባዳቢው በፍልጥ ያባረረን፣ ‹‹ና ውጣ›› የሚቀናው መምህሬ ትውስታ ውል ይልብኛል፡፡ ‹‹… እናንተ ድንጋዮች ናችሁ፡፡ አይገባችሁም፡፡ ከዚህ በላይ እንዴት ፈትፍቼ ላስተምራችሁ? ምን ቀረ! ቀኑን ሙሉ ለፈለፍኩ ይኼው አንድም የያዘ ተማሪ የለም፡፡ እናንተን ከማስተማር ጦጣና ዝንጀሮ ማስተማር ይሻላል፡፡ በምን ቀኔ አስተማሪ እንደሆንኩ እንጃ፡፡ … ያምናው ስንል የዘንድሮው ባሰ፡፡ ይገርማል፡፡ ይቺ አገር… ከእናንተ እንደሆን መቼ ይሆን የሚገላግለኝ?›› ያለን መምህር ፊቴ ሲደቀን ሳይገባን ቀርቶ ሳይሆን በማይታይ መጠን ትምህርትም የትምህርት፣ ጥቅምም ልጅነትም፣ በወቅቱ አታሎን እሱም ፍቅሩን እንጂ ተበሳጭቶብንማ አይደለም፡፡ በማይታ መጠን የቤት ወይም የትምህርት ቤት ችግር ቢያጋጥመው እንጂ አስተማሪ ተማሪውን ሊጠላ አይችልም እላለሁ፡፡
‹‹ያ ሰው ደካማ ነው፣ ልፍስፍስ ነው፡፡ ምንም አይችልም፣ በሥራው ብትል በቤተሰቡ፣ በኑሮው ብትል በሃይማኖቱ፡፡ በቃ እኔ ‹ኮንፊደንስ› የሌላቸው ብዙ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ እንደሱ ግን አይቼ አላውቅም፡፡ ምንም ‹ኮንፊደንስ› የሚባል አልፈጠረበትም ስልሽ፡፡ እኔ soft mind ትያለሽ እንዴ mind አለው ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ ስልሽ… ሰው እንዴት እንደዚህ ሆኖ ይፈጠራል? በፈጣሪ ሥራ ውስጥ አስገባሀኝ…›› እያሉ ሲያሙልኝ በግማሽ ልቤ ሌላ ሥራ እየጀመርኩ ተው መስፈርታችሁ እንጂ፣ ከእሱ በላይ ምናልባትም ደፋር በማይታይ መጠን ይታየኛል እላቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም ምናልባት ‹‹ጥንካሬን መምታት›› በሚል ሳይንስ ‹ኦቨር ኮንፊደንት› ስለሆነ እንዲህ እንምታው የምትል ሴራ በማይታይ መጠን ትሸተኛለች!
በአንፃሩ ይህም አይቀራቸውም፣ ደግሞ የሰውን ክፋት እንዲህ ብለው ይነግሩኛል፣ ‹‹… እዚህ የደረሰው እኮ በድሎ፣ አጭበርብሮ፣ በአጭር ጊዜ ይደረጋል የማይባለውን አድርጎ ነው፡፡ ይገርምሃል እኔ ክፉ ሰው ብዙ አጋጥሞኛል፡፡ እንደ እሱ ግን የሰይጣን ቁራጭ የሆነ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡ ክፋት እኮ ልክ አለው፡፡ እሱ እኮ ሕፃን አይል ትልቅ ሁሉንም እኮ ነው የበደለው፡፡ … እንዲያው ምንም ሠርቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ሁሉንም ነገር አጭበርብሮ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ተው እባክህ እንደ እሱ ዓይነት ሴረኛ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡ ምን አያደርግም የራሱን ሰው ከልሆነ አይቀርብ አያስቀርብ፣ ለራሱና ለቤተሰቡ እንጂ ሌላ ቦታ አታየው? እንዲያውም ባለፈው…›› ሌላ የጨለማ መልኮቹን ሊነግረኝ ሲጣደፍ የአዕምሮዬ ጉዳይ ደግሞ ምንም ቢሆን፣ በማይታይ መጠን የዚህ ሰው ደግነትና መልካም ጎኖች ይመጡብኛል ባላውቀውም፡፡ ስለዚህ እነሱን ላለመናገር ቀስ ብዬ ከእነዚህም ሰዎች እርቃለሁ፡፡
ይኼም አይቀራቸውም፣ ‹‹… እኔ የተማረ ሰው አይቻለሁ እንደ እሱ የተማረ የተመራመረ ምሁር አላየሁም፡፡ ምሁር ነው ስልህ፣ የዕውቀት ልክ፡፡ ጨዋነቱ፣ መልካም ሥነ ምግባሩ፣ ትህትናው፣ አመለካከቱ፣ አመለካከቱን የሚገልጽበት መንገድ የተማረ ሰው ባህርይ ነው፡፡ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ እንዲያው እንደ እሱ ዓይነቱን ቢያበዛልን እንዲያው ምናለበት?›› ሲሉ፣ በማይታይ መጠንም ቢሆን የልተማረ ሰው ባህርይ ያሳያል መጨረሻውን እንይ ተው እላቸዋለሁ፡፡
የበደላቸውን ሰው ከፍቷቸው እንዲህ ያማርሩብኛል፣ ‹‹… ዕድሌን ያበላሸው፣ እዚህ ያስቀረኝ እሱ ነው፡፡ ልንገርህ… ተወው በሆዴ ይቅር… ልንገርህ… ይኼውልህ ምን ያላደረገኝ ነገር አለ ብለህ ነው፡፡ በቃ እኮ ጠመደኝ፡፡ ይኸው ሕይወቴ እንዲ ሆኖ ቀረ ዕድገት ያስከለከለኝ እሱ፣ ደመወዝ ጭማሪ ያስከለከለኝ እሱ፣ ቤተሰቤን በአግባቡ እንዳልመራ ያደረገ እሱ፡፡ ሕይወቴን ምስቅልቅሉን ያወጣ እሱ ነው፡፡ እሱ እንዲህ ባያደርገኝ… እሱ በቀናነት እንደዚህ ቢያደርግልኝ ኖሮ እኮ ልጆቼ የተሻለ ትምህርት ቤት ይማሩልኝ ነበር፡፡ ወይም በገንዘቤ ደህና ትምህርት ቤት አስተምራቸው ነበር፡፡ እግዜር ይይለት እንጂ ምን ያላደረገብኝ ነገር አለ…›› ብለው ሲያማርሩ፣ ሐዘናቸው እየተጋባብኝም ቢሆን ምንም ቢሆን ሰው ነው እንዴት አንድ ሰው ላይ ሁሉን ነገር ሊያደርግ ይችላል?
ስለዚህ በማይታይ መጠን የማይታዩ ሰዎችም ተፅዕኖ ይታየኛልና ሙሉ በሙሉ ለዚህ ሰውዬ አልሰጥም፡፡ ይኼንኑ ገልብጠው ደግሞ መልካም ስላደረጉላቸውና ምናልባትም አሁን ለደረሱበት ስኬት እነዚያ ሰዎች እጅግ ብዙ ውለታ እንደዋሉላቸው ሲናገሩ ግን፣ መልካም ልቦናዬ በማይታይ መጠን የሰው ልጅ ክፉ ነው የሚለውን ሐሳብ አለመዘንጋት አይቻለውም፡፡ መልካምነት መልካምነትን አለመውለድ ያቅታታልና እንኳን ከመልካም መልካም ካልሆኑም ነገሮች መልካም ነገር ማጨድ እንደሚቻል፣ ‹‹ዕይታን› ብቻ መግራት ይበቃል ብዬ አስባለሁና የማየት መጠን ክፋቶች ይጠፉኛል፡፡
በመጨረሻም የማይታይ መጠን የቫይረስ ብዜት ማለት አንድ ኤችአይቪ/ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መድኃኒቱን እንደ ሐኪሙ ትዕዛዝ በአግባቡ ከወሰዱ፣ ሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ ብዜት በአንድ ሲሲ ውስጥ ከ1,000 ኮፒ በታች ሲሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ቫይረሱ የማይታይ መጠን ብዜት አለው ይባላል፡፡ ያ ማለት ግን ሰውየው ከኤችአይቪ ቫይረስ ነፃ ነው ማለት አይደለም፡፡ መድኃኒቱን በአግባቡ ስለሠራ እጅግ ጥሩ ለውጥ አምጥቶ የታማሚውም ጤና በእጅጉ ተሻሽሏል ማለት ነው እንጂ፡፡
እናም እኔም የሰውን ልጅ ለመረዳት ባደረግኩት ጥረት ብዙ መልካም መልካም ነገሮችን የምመለከትና በጎ ያልሆኑ ነገሮች አዕምሮዬን የሚያሙኝን ያህል፣ የሰው ልጅ ደግሞ ፍፁም ምሉዕ አይደለምና ‹‹በማይታይ መጠን›› እኔም እንደዚህ አስባለሁ::
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bediluab@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡