Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየፀረ ሙስና ትግሉ ጅማሮና የመንግሥት ሠራተኛው

የፀረ ሙስና ትግሉ ጅማሮና የመንግሥት ሠራተኛው

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው  

በኢትዮጵያ ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለው የሰው ኃይል ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ መምህራን፣ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊትን የመሰሉትን ሰፋፊ መዋቅሮች ለተመለከታቸው ደግሞ አይደለም በፌዴራል ደረጃ ክልሎችም አሥርና መቶ ሺዎችን ያሠለፉባቸው ናቸው፡፡ ከዝቅተኛው ደመወዝተኛ እስከ ከፍተኛው ተከፋይ ወይም ከፍተኛ ኃላፊነት የወደቀበት ዜጋ ድረስ ሰፊ ስብስብ የያዘ መስክም ነው፡፡

ከዚህም በላይ የመንግሥት ሠራተኛ ስሙም እንደሚያመለክተው፣ የመንግሥት ፖሊሲና ሕግጋት ዋነኛ አስፈጻሚና ለአገር መቀጠል ወሳኝ ድርሻ ያለው ኃይል ነው፡፡ በሌሎች አገሮችም እንደሚታወቀው እርስ በርሳቸው በተግባርና ሥርዓት የተሳሰሩና ተመጋጋቢ የሆኑ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅሮች ሕግና ሥርዓት ያወጣሉ፣ ዕቅድና ፖሊሲ ያስፈጽማሉ፣ ሕግ ይተረጉማሉ፣ ተጋምደውም አገርን ይገነባሉ፡፡ ተወደደም ተጠላም ይህ ኃይል የሚመሰለው ግን  በፖለቲካ ሥርዓቱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ ይህ ዘርፍ ምንም እንኳን ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ሥርዓቶችን በማገልገል የሚታማ ነው፡፡ በየአስተዳደሩ ውስጥ በሙስናና በብልሹ አሠራር ዜጋው ሲመረርበት የኖረ፣ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደማምሮ አገር ወደ ብልፅግና እንዳትሄድ የጎተተ ነው እየተባለ ቢተችም፣ ከእነ ጉድለቱ አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡ ሚሊዮን ተቀጣሪዎችና ቤተሰቦቻቸውን ይዞ መዝለቁም ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡

ያም ሆኖ አሁን አገሪቱ ከደረሰችበት ደረጃና ዓለምም እየተራመደበት ካለው ጎዳና አኳያ፣ የሲቪል ሰርቪሱን ቅኝት መፈተሽና ጉድለቶቹን መቅረፍ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ በአንድ በኩል በተቻለ መጠን የመንግሥት ሠራተኛውን ጥቅምና መብት እያስከበሩ፣ አሠራርና ሕግጋትን እያሻሻሉ ለተሻለ አፈጻጸምና ውጤታማነት ማነሳሳት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል መዋቅሩ በሥነ ምግባርና በሥርዓት የሚመራ፣ ሌብነትና ሙስናን የሚፀየፍና እርስ በርሱ የሚተጋገል በማድረግ የሕዝቡን ቅሬታ መቅረፍም ግድ ይላል፡፡

በዚህ ረገድ ከአምስት ዓመታት በፊት (አሁን ያለው መንግሥታዊ አመራር ወደ ሥልጣን ሳይመጣ) አገሪቱን ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶው በሚል ንቅናቄ በሕዝቡና በመንግሥት ሠራተኛው ውስጥ በስፋት ውይይት እያደረገ ነበር፡፡ በወቅቱ የምክክሩ ዋነኛ ግብ የተፈጠሩትን መሠረታዊ ችግሮች በመፍታት ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማስቻል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነበር፡፡ ግን የመንግሥት ሠራተኛውን በጅምላ ከመውቀስ ባለፈ የሌብነት አካሄዱን ነጥሎ የሚመታ ትግል ሳይደረግበት መክኗል፡፡

በመንግሥት ሠራተኛው በኩል በተለይ ከሕዝብ ጋር በሚያገናኙት የአገልግሎት ዘርፎች የታዩት መጠነ ሰፊ ችግሮች ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መረገጥ፣ በመንግሥት ንብረት ያላግባብ መጠቀም፣ ተገቢ ላልሆኑና በሕገወጥ መንገድ ለሚሠሩ ሥራዎች ተባባሪ መሆን፣ ጠባብነትና ትምክህት፣ ዘረኝነትና ቡድንተኝነት፣ ሕዝባዊነትን መዳከምና ግለኝነት ማንገሥ፣ ወዘተ. የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረት ከሆነው ሙስናና ብልሹ አሠራር አንፃር የአብዛኛው ሕዝብ ቅሬታ መሠረቱ፣ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሕዝቡን በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ጉቦ መቀበል፣ ማመላለስ፣ የተለየ ጥቅም በመፈለግ ማጉላላት፣ ከመንግሥት ቢሮዎች ሕጋዊ ሰነዶችን ውጪ ላሉ ሙሰኞች አሳልፎ መስጠት፣ እንዲጠፉ ማድረግና ለማይገባቸው ሰዎች የሐሰት ሰነዶች ከፋይል ጋር ማያያዝ ሌሎችንም ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይህ ሁሉ ሕገወጥ የአሠራር መናጋት የነገሠው ብልሹ ባለሥልጣናትና ከሥራቸው ያሉ ተባባሪዎች ከሙሰኞች ጋር በመመሳጠር በሚፈጽሙት ድርጊት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በየቦታው በሕዝቡ ውስጥ የሚፈጽሙት ወንጀል ነው የሕዝብን ቁጣ ያስነሳው ተብሎ እንደ ጉድ ሲወገዝ መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር፡፡ በተለይ የመከረኛውንና የደሃውን ሕዝብ መሬት የመቀራመትንና የመቸብቸብን አዙሪት የመጣው ጥገኛ ሁሉ አልቦዘነበትም፡፡

አሁንም በአንድ በኩል ከቀደመው ሥርዓት በሌብነትና በአድርባይነት ሲርመጠመጡ ከርመው ወደ ብልፅግና የተቀላቀሉ፣ በሌላ በኩል በአዲስ ገጽታ መዋቅሩን ለግል ጥቅም ማዋል የሚፈልጉ ጥገኞች የሥርዓቱ ፈተና በመሆን ላይ ናቸው፡፡ በኃላፊነት ቦታ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ባለሙያዎችና ተራ ኤክስፐርቶች ሁሉ የባለሀብት ኪስ መግባትን ወይም የሕዝብ ሀብትን ቸብችቦ መንደላቀቅ መገለጫ እያደረጉት ነው፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከአርሶ አደሩ መሬት ካሳ፣ ምትክና በአርሶ አደር ልጅ ስም የተፈጸመ ሕገወጥነት ተነግሮ የሚያልቅ አይመስልም፡፡

ቀደም ሲል በአገልግሎት ዘርፍ ተሠማርቶ የሚገኘው አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ከውጭ ካሉ ደላሎችና ሙሰኞች ጋር በመተባበር የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በሚከተለው ሕገወጥ አሠራር ሕዝቡ እንዲማረርና ዜግነቱን እንዲጠላ አድርጎትም ነበር፡፡ በተለይ ጉዳይ ገዳይና ሕገወጥ ደላላን አሠማርተው የአገሪቱንና የሕዝቡን ሀብት የዘረፉና የመዘበሩ አሁን ቀና ብለው መሄድ ባይችሉም፣ ከእነ ሕገወጥ ሀብታቸው እዚህም ተሰደውም ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ተጠርጣሪዎችን በሕግ መዳኘት ሲገባ እንዴት ገና በለጋ የለውጥ ምዕራፍ ተጨማሪ ሌብነት ሊበራከት ቻለ? የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

አሁን ችግሩ ለምን ታየ ሳይሆን እንዴት ተባብሶ ቀጠለ ሲባል ነው ትግሉ ገና መቀጣጠል አለበት የሚያስብለው፡፡ ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› እንዲሉ የኢሕአዴግን ሥርዓት ከሥሩ መንቀል እንኳን ቢቀር፣ ጥገናዊም ቢሆን ለውጥ ተደረገ ተብሎ አንዳንዱ የአገልግሎት አሰጣጥና ሥርዓት ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ተባብሶ ሕዝብ ሲያማርር እየታየ መሆኑ ማንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ ይህንን ባለማስተካከል አደጋው መክፋቱ አይቀርም፡፡

በመሠረቱ የደኅንነት ሥጋት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር በአንድ ጊዜ የሚወገዱ ባይሆንም አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ተመጋጋቢና የተሳሰሩ ሆነው ለመቀጠላቸው ያለፉት አምስት ዓመታት ጥሩ ማሳያዎች ነው የሆኑት፡፡ ሙስኛና ጥገኛው ለአገር ህልውና ደንታ እንደሌለው ማሳያው አገር ጦርነት ውስጥ ገብታ እንኳን (ብዙዎች እየሞቱና እየተጎዱ) በተፈጠረው ግርግር ውስጥ ሌብነትን የሚያጧጡፉ መብዛታቸው ነው፡፡ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ ውዝግብን እያካረሩ በውስጥ ሌብነት እንዲደራ የሚራኮቱም ስለመኖራቸው ውስጥ ለውስጥ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላኛው አደጋ ነው፡፡

የጉዳዩ አሳሳቢነት በትልልቁ አገራዊ ጉዳይና ሀብት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር በሚያገናኙ አገልግሎት ሰጪ ሥራዎች ተሠማርተው የሚገኙትን ክፍሎችም የሚመለከት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በሠራተኛው ውስጥ በተካሄደው ግልጽ ውይይት እያንዳንዱ ራሱን እንዲፈትሽ፣ ስህተቱን እንዲያርም፣ ዳግም ሕዝብን የሚያስከፉ ብልሹ አሠራሮች ውስጥ እንዳይገኝ፣ በተመሳሳይ ሁኔታም በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች በቀጥታ ሠራተኛው ፊት ቀርበው ተገማግመው ነበር፡፡

ነገር ግን ሠራተኛውም ሆነ ኃላፊዎች ስህተታቸውን ለማረም ቃል የመግባታቸውን ያህል የተገኘ ውጤት ጎልቶ አልታየም፡፡ ዛሬም የሲቪል ሰርቪሱ ብቃት፣ ዕውቀትና ታማኝትን ከማስቀደም ይልቅ እንደ ብሔር ምጥጥን፣ የፖለቲካ ታማኝነትና መሰል መሥፈርቶችን ማስቀደሙ አገር እየመሩ ላይ ግንባር ቀደም ሰዎችም ሆኑ የለውጥ መሪዎች ምኞትን ያሳኩ አልሆኑም፡፡ ሕዝቡም ከቅሬታው ፈጥኖ ለመላቀቅ ተቸግሯል፡፡

አብዛኛው ሠራተኛ በየሥራ ክፍሉ በተናጠል በጋራ ደግሞ ሁሉም በተገኙበት ከየመሥሪያ ቤቶቹ ልዩ ባህሪ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ፣ ግልጽና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች መደረጋቸው አገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የአገር ፀር የሆኑ ድርጊቶችን ለመቅረፍ ግን ውይይትና ምክክር ብቻ ሳይሆን ጥብቅ ቁጥጥር፣ ቁርጠኛ የሆነ ዕርምጃና ሕዝብን ያሳተፈ ትግል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ራሱ ጤነኛው የመንግሥት ሠራተኛስ ለአገሩና ለስሙ ሲል አምርሮ የማይተጋገለው እስከ መቼ ነው?

እውነት ለመናገር ትናንትም ሆነ ዛሬ ሙስናው፣ ሌብነቱና የፍትሕ ጥሰቱ የሚካሄደው በአየር ላይ አይደለም፡፡ በተለይ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የራሱን የመንግሥት ማኅተም በመጠቀም ወንጀሉ ሲፈጸምበት ይታያል፡፡ በሕጋዊ ጨረታ ስም፣ በመንግሥት ግዥና ሽያጭ ሥርዓት ውስጥ፣ በሰው ኃይል ቅጥርና ምደባ፣ ጥበቃው በላላ የጋራ ሀብት ይዞታ ውስጥ የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓቱ መላላት በፈጠረው ክፍተት ከፈተኛ ዘራፊነትና አምታችነት እየተስተዋለ ነው፡፡

አገራዊ ችግሩ እየሰፋ ድንበር ጥሶ ያለፈበት ዋነኛ ምክንያት በራሱ በመንግሥት ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተመደቡት በተለያየ ደረጃ የነበሩና ያሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ሥነ ምግባርና ታማኝነት መሸርሸር ነው የሚሉ ትችቶች መደመጥ አለባቸው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ኔትወርክና አድርባይነትን ሊገፋ የሚችል ጠንካራ የምዘና ሥርዓትና ግምገማ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉም ነው፡፡

በተለይ አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ከቀበሌ፣ ወረዳና ክፍለ ከተማ አንስቶ ክልል ድረስ በመሬት፣ በገቢዎች፣ በግንባታ ፈቃድና ዕድሳት፣ እንዲሁም በፕላንና መሰል ዘርፎች አካባቢ ከፍተኛ የሚባል የተገልጋይ ምሬት ይሰማል፡፡ በዚያው ልክ ከገቢያቸው በላይ የሚኖሩና ላልተገባ የሀብት ብክነት የተዳረጉ ጥገኞች መበራከታቸውን ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ መንግሥትም የሚስተው አይደለም፡፡ ስለሆነም የፀረ ሙስና ትግሉን መሬት ማስያዝና በቁርጠኝነት ማቀጣጠል ከተፈለገ መንግሥት ከላይ እስከ ታች መዋቅሩን የሚፈትሽበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

እውነት ለመናገር በሚታየው አዝማሚያ ልክ የመንግሥትንና የሕዝብን ሀብት ሕግና ሥርዓቱን መጠበቅና ማስጠበቅ የሚገባቸው መንግሥታዊ አካላት፣ ለሙሰኞች አጋርና ተባባሪ፣ ሰነድ አውጪና ቀያሪ ባይሆኑ ይህ ክፍተት እዚህ ባልደረሰ ነበር የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንድ የሕግና የሰነድ ተቋማት ላይ ያሉ ተባባሪዎች የሐሰት ሰነዶችን ሕጋዊ አድርገው ሰጪና አቀባባይ ባይሆኑ ኖሮ፣ የሕዝብ ብሶትና መከፋት ድንበሩን ጥሶ ጣሪያ ባልነካም ነበር፡፡

ከላይ እስከ ታች ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሠራተኞቻቸው ሕጉንና ሥርዓቱን ተከትለው፣ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን አስቀድመው ቢሠሩ ሙስናና ሕገወጥነት ባልተንሰራፋ ነበር፡፡ ስለሆነም በቀጣዩ ጉዞም እንደ ወሳኝ መፍትሔ አቅጣጫ መቀመጥ ያለበት የትኛውም አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂና በዘመናዊ አሠራር የታገዘ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ ሥርዓት ማበጀት ለነገ የማይባሉ ተግባራት ናቸው፡፡ ሕዝቡም ጉቦን መፀየፍ መጀመር አለበት፡፡

ከዚህም በላይ የሙስናና የአቋራጭ መንገድን የሚያሰፋ ሕገወጥ ድርጊት ማደሪያቸው አድርገው በጉቦ አቀባይነትና ተቀባይነት፣ በተላላኪነት፣ በጉዳይ አስፈጻሚነት የግል ጥቅማቸውን በማሳደድ የተጠመዱትን፣ በዚህም ሕገወጥ ድርጊት የከበሩትን በሙሉ አጋልጦ ማውጣት ጤነኛ መንግሥታዊ አሠራርና አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ብልፅግና እውነተኛ የሕዝብ አደራ ተሸካሚና አገርን ወደፊት የመውሰድ ህልም ካለው በድፍረት መጀመር ያለበት ይህንን ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከተሃድሶው ጊዜ አንስቶ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመጀመር ቢሞከርም፣ ሕገወጦችን እየመነጠረ ሊያወጣ የሚችል ቁርጠኝነትና የሕዝብ አጋርነት አልታየም፡፡ እንዲያውም እንደ ምንም ዘርፎ የከበረ ድምፁን አጥፍቶ ከኖረ የሚነካውም ያለ አይመስልም፡፡ አሁን ግን ይህን ብልሹ መንገድ ለማስቀረት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አካላት የሀብት ምዝገባን ሥርዓት ማጠናከር፣ የንፋስ አመጣሽ ሀብት ምንጮችን የመለየትና ማጋለጥ፣ ተጠርጣሪዎችን በሕግ የመጠየቅ ሥራ መጠናከር አለባቸው፡፡ መንግሥትም የፍትሕ ሥርዓቱን ከአጠላበት አሉታዊ ገጽታ ማላቀቅ ይኖርበታል፡፡

ከዚህ አንፃር በሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ባሉ አመራሮችም ሆነ ሠራተኞች ውስጥ የሚካሄደው ማጥራትና ግንባታ፣ በተጨማሪም በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚመዘኑበት ሥርዓት መጀመር አለበት የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሥራዎችና የፖለቲካ ሥራዎችም በቅጡ ተለይተው መቀመጥም አለባቸው፡፡ እንደ ትናንቱ ሁሉ በቅርቡ የጀመረው የፀረ ሙስና ትግል እንዲዳከም ብሔርና ሃይማኖትን መደበቂያ ያደረጉ፣ ሕግን እንዳሻቸው እየጣሱ ወንጀላቸውን ለመሸሸግ የሚፈልጉ፣ እንዲሁም በሁከትና በብጥብጥ ትግሉን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና የሚሉ ሁሉ ብርቱ ትግል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ የግድም ነው፡፡

በመሠረቱ ዛሬም ሆነ ነገ ጠንካራ አገራዊና ሕዝባዊ ተልዕኮውን በውል ለይቶ የሚያውቅ፣ ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል ከሙስናና ከአድሏዊነት የፀዳ ሲቪል ሰርቪስ ብቻ ነው ለመንግሥትም ለሕዝብም የሚጠቅመው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ነግሦ የኖረው ሙስናና ጉቦን የሚያወድስ ኋላቀር አስተሳሰብ መልሶ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ በመሆኑ፣ ከሥሩ ተነቅሎ እንዲመክን ለማድረግ ሰፊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በመንግሥትም ሆነ በገዥው ፓርቲ በኩል ጠንካራ ሥራዎች  መሠራት አለባቸው፡፡

በአጠቃላይ እስካሁንም ባለው አገራዊ ጉዞ የመንግሥት ሠራተኛው አገሪቱ በየዘርፉ ላስመዘገበችው ዕድገት ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ አይካድም፡፡ ነገር ግን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነው ሠራተኛና ባለሥልጣን ሙስናን የማይፀየፍና ጥቅም አሳዳጅ እየሆነ፣ የሚጠበቅበትን ያህል የሕዝብ አገልጋይነትን መንፈስ ተላብሶ ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሐዊነትና የርትዕ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን ፈጽሞ መቀጠል የሚቻል አይሆንም፡፡ ከበረታን በጋራ ፀንተንና ታግለን አደጋውን መቀልበስ እንችላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...