Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊገበሬዎችን በመንደር የማሰባሰቡ አዲስ ትልም

ገበሬዎችን በመንደር የማሰባሰቡ አዲስ ትልም

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ከሰማንያ በመቶ በላይ ሕዝቦቿ በግብርና የሚተዳደሩባት ኢትዮጵያ፣ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በሚገባት ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ይነገራል፡፡ በተለይ ደግሞ የዘርፉ ተዋናይ የሆነው አርሶ አደር በፀሐይ አርሶ በዝናብ አብቅሎ ቀን ከሌሊት ለፍቶ የሚያገኘው ምርት ከዕለት ፍጆታ የማያልፍ ነው፡፡ የዕለት ፍጆታም ብርቅ ሆኖበት በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ያለው አርሶ አደርና የአርሶ አደር ቤተሰብ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

‹‹ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ›› ሆኖ ሳለ ከዘመኑ ጋር እኩል የማይራመድ የግብርና መርህ በመከተል ለዕርዳታ የተዘረጉ እጆች በርካታ ናቸው፡፡ ለግብርናው ዘርፍ መድከም ከአየር ንብረት መዛባት ከድርቅና ከኋላቀር የአመራረት ዘዴ ባሻገር በተለይ ደግሞ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል አብዛኛው ኅብረተሰብ ተራርቆና ተበታትኖ የሚኖር በመሆኑ በክላስተር ተደራጅቶ በጋራ ለመሥራት አመቺ አለመሆኑ እንደ አንድ ችግር ይነሳል፡፡

ይህንን ተራርቆና ተበታትኖ የሚገኝ የማኅበረሰብ ክፍልን ወደ አንድ መንደር በማሰባሰብ ዘመናዊ የአስተራረስና የአኗኗር ዘዴን በመቀየር ከተሜነትን እንዲከተል ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርሶ አደሮች ከ70 እና ከ80 ዓመት በላይ ሲሠራበት ከቆየው የአመራረት ዘዴ ወጣ በማለት በክላስተርና በኩታ ገጠም በማምረት ምርታቸውን ለገበያ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡

ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው በተለያዩ ምክንያቶች በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በርካታ አርሶ አደሮች የሰው እጅ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ በበርካታ የመጠለያ ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ ወገኖች ምስክር ናቸው፡፡

ምርትን በከፍተኛ ደረጃ አምርተው ከራሳቸው አልፈው ኑሮ እንደ ተራራ የከበደበትን ከተሜ በበቂ እንዲመግቡ ለማድረግ፣ ከዚህ ከፍ ሲል ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በሠሩት ልክ እንዲያገኙ ለማድረግ ትኩረት ላልተሰጠው አርሶ አደር፣ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ከተሠራ፣ ችግሩ ከምንጩ ለማድረቅ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ብሏል ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፡፡

የዜጎችን አንገት የሚያስደፋውንና የኢትዮጵያን ስም የሚያጎድፈውን ድህነትና ተረጅነትን ለማስወገድ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበትና ባለቤት የሚሆኑበትን ‹‹የገበሬዎች መንደር›› ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሥሐ እሸቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ አንድ ሺሕ ለሚሆኑ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ያሟላ አንድ ሺሕ ሔክታር ላይ ያረፈ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ለመገንባት ያሰበ ሲሆን፣ መንደሩም መታሰቢያነቱ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ታላቅ አስተዋጽኦ ላበረከተው አንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ይሆናል ተብሏል፡፡

ፍሥሐ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሮጀክታቸው ‹‹ሃሽታግ ኖ ሞር ሃንገር›› የሚል ትልቅ ራዕይ ይዞ በቅርብ ወደ ሥራ እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በድርቅና በጦርነት እንዲሁም፣ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ ችግሮች ተፈናቅለው በከፋ ረሃብና ችግር ውስጥ መሆናቸውን አንስተው፣ በዚህም የቀጥታ ተረጅ ሆነው እንደሚኖሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ችግሩን ለማቃለል ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ፣ ከፕሮጀክቱ ትርፍ ባልተናነሰ ሁኔታ በኅብረተሰቡ በሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ ትኩረት በማድረግ ‹‹የገበሬው መንደርን›› ለማቋቋም መነሳቱን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 720 እና 80 ዓመታት ለረሃብና ለድህነት እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው ዕርዳታ ብቻ ነው ያሉት ፍሥሐ (ዶ/ር) ምንም እንኳን እንቅስቃሴው በመጥፎ ጎን የሚታይ ባይሆንም ችግሩን ከምንጩ ከማድረቅ ይልቅ፣ ሰዎችን የዕርዳታ ጥገኛ የማድረግና እንደ ዜጋም ተመፅዋችነትና ተረጅነት የሁላችንንም አንገት እያስደፋ ያለ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ድህነትን በዘላቂነት ለመፍታት ገንዘብን በቀጥታ ከመስጠት ይልቅ፣ በራሳቸው ሠርተው እንዲመልሱ በማበደርና የሚሠሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከተረጂነት ስሜት ወጥተው ትርፋማ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ድህነትን በዘላቂነት እንዲፈቱ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው ይላሉ ፍሥሐ (ዶ/ር)፡፡

‹‹የገበሬው መንደርን›› ዕውን ለማድረግ በመጀመርያ በተለያዩ ችግሮችና መጠለያ ውስጥ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ውስጥ 50 ሺሕ የሚሆኑ ገበሬዎችን በአንድ አካባቢ በማሰባሰብና መሠረታዊ የሚባሉትን አገልግሎቶች በማሟላት አንድ ሺሕ አባወራዎችን በአንድ ሺሕ ሔክታር ላይ በማሥፈር ራሳቸውን ሠርተው የሚቀይሩበትን የእርሻ ማሳ በማዘጋጀት በማሳቸው ላይም 365 ቀናትን የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩና ምርትን እንዲያመርቱ በማድረግ ከብት ማደለብ፣ ንብ ማነብ፣ ዶሮ ማርባትና ሌሎችንም ሥራዎችን እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋልም ብለዋል፡፡

የመሐሙድ አህመድ ‹‹የገበሬዎች መንደርን›› በሁሉም አካባቢዎች ዕውን ለማድረግ የታሰበ ሲሆን፣ በቅድሚያ ግን የመንደሩን የመሥሪያ ቦታና ሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ምቹ ያደረገ ክልል ላይ ግንባታውን ለማከናወን ታቅዷል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን በአፋር ክልል ቦታ መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡ ለመዲናዋ ቅርብ የሆነ አካባቢ ላይ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ እንዳሰቡም ተናግረዋል፡፡

የመንደሩ መገንቢያ ውጭም ‹‹ረሃብን የማጥፋት እንቅስቃሴ›› በተሰኘ ተነሳሽነት በተዘጋጀው የአክሲዮን ሥርዓት በአገር ውስጥና በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገዙት አክሲዮን ነው ተብሏል፡፡

አርሶ አደሩ ከፕሮጀክቱ በብድር የወሰደውን ገንዘብ ቢያንስ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሠርቶ እንደሚመልስና ትርፋማ እንደሚሆን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት እንዳቀዱ፣ ግንባታውንም ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሊገነባ በታሰበው የመሐሙድ አህመድ የገበሬዎች መንደር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...