Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዓለም የቤት ውስጥ ሩጫን በድል የጀመሩት ኢትዮጵያውያን

የዓለም የቤት ውስጥ ሩጫን በድል የጀመሩት ኢትዮጵያውያን

ቀን:

የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የሰጠው የ2023 የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በጀርመን ካርልስሩኸ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ለስምንተኛ ጊዜ በተለያዩ አኅጉሮች በሚገኙ ሰባት ከተሞች በዙር በሚካሄደው ውድድር መክፈቻ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲካሄድ በመካከለኛ ርቀት፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ድል ቀንቷቸዋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ ከሁሉም የትራክ ውድድሮች ትኩረትን የሳበው በሴቶች 3,000 ሜትር ከተፎካከሩት መካከል በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባለሜዳሊያ የሆኑት አምስቱ ከኢትዮጵያ የተገኙ መሆናቸው ነው፡፡

የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮኗ ለምለም ኃይሉ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ቢሰጣትም፣ የ2021 የዓለም ከ20 ዓመት በታች የ5,000 ሜትር አሸናፊዋ ሚዛን ዓለም 2,000 ሜትሩን በፈጣን ሩጫ በ5፡53፡11 ደቂቃ በመምራት ማጋመሷ ትኩረትን ስባ ነበር፡፡

በዚያ ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው ዳዊት ሥዩም ሚዛንን ስትከተል፣ የዓለም የ3,000 ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ወርቅውኃ ጌታቸው ካጠገቧ ነበረች፡፡

ይሁን እንጂ ሻምፒዮኗ ለምለም ኃይሉ ውድድሩ ሊያበቃ ሁለት ዙር ሲቀረው ፍጥነቷን ጨምራ ስትገሰግስ ያቆማት አልነበረም፡፡ ወርቅውኃ የመጨረሻው ዙር ላይ ለመቅደም ብትሞክርም አልቀናትም፡፡ ለምለም ከጥንቃቄ ጋር በተደጋጋሚ ወደኋላ እየተመለከተች ሩጫዋን በማክረር በ8 ደቂቃ 37፡55 ሰከንድ ለማሸነፍ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያውያቱ ወርቅውኃ (8፡37፡98)፣ ዳዊት (8፡39፡20)፣ ዓለም (8፡39፡79)፣ ዘርፌ ወንድማገኝ (8፡42፡90)፣ በተከታታይ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ሆነው ውድድራቸውን ፈጽመዋል፡፡

የወንዶች 3,000 ሜትር ወጣቱ ባለድል

ከዘንድሮ በፊት አብዲሳ ፈይሳ የሚለውን ስም የሰሙ ጥቂቶች ቢሆኑም፣ በካርልስሩኸ በ3,000 ሜትር ውድድር ባስመዘገበው ድሉ ግን ስሙ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡

በውድድሩ ሒደት ተቀናቃኞቹ እንዳሻቸው እንዲፎካከሩ ችላ ያላቸው የ17 ዓመት ዕድሜው አብዲሳ በጥንቃቄ መከታተሉን ግን ቸል አላለም፡፡

ውድድሩን ጀርመናዊው መሐመድ ዓብዱላሂ እየመራ 2,000 ሜትሩን በ5፡08፡25 ሲያልፍ የተከተለው ሰርቢያዊው ኤልዛን ቢቢክ ነበር፡፡ ከዓብዱላሂ ጋር አብሮ የሚሠለጥነው ቤልጂማዊው ሮቢን ሄንድሪክስ ከመሪዎቹ ጋር ቢቀላቀልም አብዲሳና ሌላው ኢትዮጵያዊ አዲሱ ግርማ ግን በጥሩ አቋም ላይ ነበሩ፡፡

አንድ ዙር መቅረቱ የሚያበስረው ደወል እንደተደወለ ሄንድሪክ ሲያፈተልክ ዓብዱላሂ ማዝገም ጀመረ፡፡ ሄንድሪክስ ተፎካካሪዎቹን ርቆ የታየ ቢመስልም፣ ያደፈጠው አብዲሳ ግን እጁን አልሰጠም፡፡ ከፍፃሜ መዳረሻው ላይ አልፎት በመሄድ በ7፡40፡35 በሆነ ጊዜ አሸንፎታል፡፡

ይህም በዓለም የቤት ውስጥ ሩጫ በ17 ዓመቱ ያሸነፈ ብቻ ሳይሆን የዘንድሮ ፈጣን ሰዓትንም ለማስመዝገብ ችሏል ብሏል የዓለም አትሌቲክስ፡፡

ሄንድሪክስ በ7፡40፡53 ሁለተኛ፣ አዲሱ ግርማ በ7፡41፡53 ሦስተኛ ሆነዋል፡፡ ዓምና በካርልስሩህ በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር በሪሁ አረጋዊ በ7፡26፡20 በመሮጥ ድል ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በሴቶች 800 ሜትር ውድድር በምሽቱ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ድል እንዳታገኝ ያቆመቻት አኒታ ሆርቫት ናት፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ ኃይሉ የውድድሩን አጋማሽ በ57፡70 በማለፍ 600 ሜትር ላይ መሪነቷን ብትቀጥልም፣ የስሎቫኪያዋ አኒታ ከመከታተል አልተቆጠበችም፡፡ ሁለቱ ተያይዘው እስከ መጨረሻው መስመር ድረስ ያሳዩት ፉክክር የተጠናቀቀው በ0.02 ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት በአኒታ አሸናፊነት ነው፡፡

አኒታ በ2፡00፡44 ደቂቃ ስትፈጽም፣ ፍሬወይኒ በ2፡00፡46 አጠናቃለች፡፡ የስዊዘርላንዷ ሎር ሆፍማን በ2፡01፡40 ሦስተኛነቷን አስጠብቃለች፡፡

የ2023 የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድሮች የሚካሄድባቸው አኅጉሮች አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካና እስያ ናቸው፡፡

የውድድር ዓይነቶችም በወንዶች 400 ሜትር፣ 1,500 ሜትር፣ 60 ሜትር መሠናክል፣ ከፍታ ዝላይና ርዝመት ዝላይ፣ በሴቶች 60 ሜትር፣ 800 ሜትር፣ 3,000/5,000 ሜትር፣ የምርኩዝ ዝላይ፣ ሥሉስ ዝላይና አሎሎ ውርወራ ናቸው፡፡

ሁለተኛው ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን የምታስተናግደው የአሜሪካዋ ቦስተን ከተማ መሆኗ ታውቋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ እንዳስታወቀው፣ እስከ የካቲት 18 ቀን ድረስ ውድድሮቹ የሚካሄድባቸው ከተሞች ቶራን (የካቲት 1)፣ ኒውዮርክ (የካቲት 4)፣ ሌቪን (የካቲት 8)፣ ማድሪድ (የካቲት 15)፣ ቤርሚንግሃም (የካቲት 18) ናቸው፡፡

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና ባለፈው እሑድ በጃፓን ኦሳካ በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ሃበን ኃይሉ አሸናፊ ሆናለች፡፡

ለዘንድሮ የመጀመርያ የሆነውና የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በሰጠው ውድድር፣ የ24 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ሃበን ያሸነፈችው 2፡21፡13 በሆነ ጊዜ ነው፡፡ የአንድ ደቂቃ ያህል ልዩነት ዘግይታ ሁለተኛ የወጣችው መሠረት ጎላ (2፡22፡12) ስትሆን፣ ሦስተኛዋ የጃፓን ሯጭ ዩካ ኢንዶ (2፡22፡59) ናት፡፡ ከአራተኛ እስከ አሥረኛ ያሉትን ደረጃዎች የተቆጣጠሩት ደግሞ ጃፓናውያት መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ ዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...