Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት የአጎዋን የንግድ ዕድል ለመመለስ ግፊት እያደረግኩ ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2022 ጀምሮ ተፈጻሚ የሆነባትን ከአሜሪካ መንግሥት ታገኘው የነበረው ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) ስረዛ እንዲነሳላት፣ የኢትዮ አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ግፊት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ወልዱ ችግሩ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለው፣ አሜሪካ የፖለቲካ መሣሪያ አድርጋ የወሰደችውን የአጎዋ ዕድል በኢኮኖሚ ረገድ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያመጣና ጥቅሙም ሰፊ ስለሆነ፣ ዕገዳው እንደገና እንዲታይ የንግድ ምክር ቤቱ ለአሜሪካ መንግሥት  በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

‹‹የአጎዋ ጥያቄ በጣም ትልቅ ነው፤›› ያሉት አቶ ኤልያስ፣ የኢትዮ አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት የንግዱን ማኅበረሰብ በመወከል ዕገዳው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ደብዳቤ በመጻፍ፣ የኮታና ቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድሉ በኢትዮጵያ ሊፈጥር የሚችለውን የኢኮኖሚ ችግር በማስመልከት ሰፊ ንግግሮችን ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛት አስተዳደሮችና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የአጎዋ የንግድ ዕድል በመሰረዙ ምክንያት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ኩባንያዎች ፋብሪካ የመዝጋት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኅዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የ2015 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አካባቢ የሚኖሩ ከ400 በላይ የሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የንግድ ማኅበረሰቦችን በማደራጀት የተመሠረተው የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቢዝነሶች የተሰማሩ የምክር ቤቱ አባላትን ያካተተ የልዑካን ቡድን የመጀመርያውን የንግድ ተልዕኮ በኢትዮጵያ እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ባከናወናቸውና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን የተለያዩ ተግባራትን አስመልክቶ ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የቢዝነስ ፎረም አስናድቶ ነበር፡፡

የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የተዘረጉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመረዳት ኢንቨስት በማድረግ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ እንዲሁም በአሜሪካ የሚገኙ የቢዝነስ ፍላጎቶችንና ዕድሎችን ለኢትዮጵያ የቢዝነስ ማኅበረሰብ መረጃ በመስጠት ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል አገልግሎት ለማመቻቸት የተቋቋመ የንግድ ምክር ቤት መሆኑ በፎረሙ ላይ ተጠቅሷል፡፡

እ.ኤ.አ በሜይ 9 ቀን 2018 በአሜሪካ ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ የመጀመርያ ውይይት በማድረግ የተጠነሰሰው የንግድ ምክር ቤት፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የንግድ ማኅበረሰቦች በአባልነት በማቀፍ፣ የቢዝነስ ማማከር፣ የገበያ፣ የሥልጠና፣ ጥናትና ምርምር የንግድ ትርዒቶችንና ሌሎች ሁነቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቢዝነሶች የተሰማሩ የምክር ቤቱ አባላትን ያካተተው የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታውም፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ መንግሥታዊና የሙያ ማኅበራት ጋር ጠንካራ የሥራ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ሒደት ውስጥ የሚገኙ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ውይይቶችን እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

በተያያዘም በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በተሰናዳው የቢዝነስ ፎረም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር)፣ ከኢትዮ አሜሪካ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በሁለቱ የንግድ ምክር ቤቶች የተደረገው የውል ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የቢዝነስ ዕድሎች መረጃ ልውውጥን ለማጠናከር፣ የጋራ የውይይት መድረኮችን ለማመቻቸት፣ በአቅም ግንባታ ድጋፍ፣ በልምድ ልውውጥና ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ አብሮ ለመሥራት ትኩረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለማልማት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ዋነኛው ችግር የሒደት (መጓተት) መብዛት እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት የኢትዮ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ፣ እነዚህን መቀልበስ የሚያስችሉ ሥራዎች ከተከናወኑ ትልልቅ ተግባራትን መፈጸም እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀጣይ አምስት ዓመታት በሚነድፈው ዕቅዱ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ በአሜሪካ የሚገኘውን የንግድ ማኅበረሰብ በይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ፣ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ወደ አገር ቤት መጥተው አስተዋጽኦ እንዲያደረጉ ግፊት ማድረግ ተጠቃሽ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች