Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ በየጥጋጥጉ ሰበብ እየደረደሩ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ ‹‹የዘራነውን ነው ያጨድነው›› ብሎ መተማመን የግድ መሆን አለበት፡፡ በፈተናው ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃውን ውጤት ያመጡ ተማሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ተብለው ሲወደሱ፣ ውጤት ያልቀናቸው ደግሞ ጠንክረው እንዲሠሩ ማበረታታት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የተማሪዎቹን ጭንቅላት በማይረባ ፕሮፓጋንዳ ለማበላሸት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ፣ አገርን ከማፍረስ የማይተናነስ ውንብድና መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ውጤት ያልቀናቸው ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆቻቸው በርትተው መሥራት ከቻሉ ከፊታቸው ብሩህ ቀን እንዳለ በማሰብ፣ የሴረኛ ፖለቲከኞች ሰለባ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ፈተና ከመስረቅና ኩረጃን ባህል ከማድረግ የማይመለሱት የዘቀጠው ፖለቲካ ተዋንያን፣ ለአገር ዕድገትም ሆነ ለወጣቱ የወደፊት ሕይወት ቅንጣት ስለማያስቡ ይህንን አጋጣሚ እንደ መልካም ዕድል መቁጠር ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካው ዝቅጠት ለአገር ፋይዳ የለውምና፡፡

የፈተናው ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ የትምህርት ሥርዓቱን ከገባበት ቅርቃር ውስጥ ማውጣት የሚጠቅመው፣ ለአሁንም ሆነ ለመጪው ትውልድ ጭምር ስለሆነ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ ላይ ይተባበሩ፡፡ በኩረጃ ወይም በስርቆት በተገኘ ውጤት መኩራራት ማብቃት አለበት፡፡ ለአገር ህልውና መጨነቅ የሚጀምረው ትውልዱን ከጥፋት በመታደግ ነው፡፡ የፈተና ውጤቱ በአገር ደረጃ ያሉብንን በርካታ ችግሮች በትንሹ ያሳየ  ስለሆነ፣ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት ችግሩ የሚቀረፍበት መፍትሔ ላይ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ካሉ ዙሪያ ገብ ችግሮች አኳያ የፈተና ውጤቱ ራሱን የቻለ ችግር ቢኖረው እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ የትምህርት ሥርዓቱ የከበቡትን ተግዳሮቶች በሚገባ ያሳየ ነው ማት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ውጤቱን በጋራ ተቀብሎ እርምት ላይ መተባበር የሚያስፈልገው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ መላ ቅጡ ጠፍቶ በክልሎችም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ጆሮ ዳባ ልበስ በተባለባቸው ዓመታት የደረሰው ጉዳት እንዲያበቃ፣ ከዘቀጠው የፖለቲካ አመለካከት ጋር ቁርኝት ያላቸው ሴረኝነትና ክፋቶች መወገድ አለባቸው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ከገባችበት የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ እንድትወጣ፣ በፈተናው የጀመረውን ምሥጉን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ጥራት ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ የበርካታ የዘርፉ ምሁራንና ልሂቃን፣ እንዲሁም የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትንና ዓለም አቀፍ አጋሮችን በማቀናጀት ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ከፍተኛ ጥረት ይጠበቅበታል፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ለመፍትሔ የሚበጁ ሥራዎች ላይ ማተኮር ያዋጣል፡፡ በትምህርት ጉዳይ ቀልድ አያስፈልግም፡፡ ከእንግዲህ በአግባቡ አስተምሮ በማስፈተን ለወግ ለማዕረግ ማብቃት ላይ ነው መተኮር ያለበት፡፡ ነጥብ በማሸጋሸግ ለፍቶ ተምሮና አጥንቶ ውጤት ካገኘው ጋር እንደተለመደው በኮታ ማሳለፍ፣ የብልሹውና የዘቀጠው ፖለቲካ ሰለባ ከመሆን ማንም ሊታደግ አይችልም፡፡  ከ1,161 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ የማለፊያ ውጤት አላገኘም ሲባል፣ ከአሁን በኋላ ተማሪዎችና ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ማንም የአገር ጉዳይ የሚመለከተው ሳይቀር እንደ ማንቂያ ደወል ይወስደዋል ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከበፊት ጀምሮ ትምህርትም ሆነ ፈተና በጣም የተከበሩ ነበሩ፡፡ በተለይ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደ ቀልድ የሚታለፍ ሳይሆን፣ በትምህርት ቤቶቻቸው የተመሰከረላቸው ተማሪዎች ብቻ ከፍተኛ ውጤት የሚያገኙበት እንደነበር በሕይወት ያሉ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡ ትውልድ ገዳይ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ግን ትምህርት እንዴት እንደረከሰና ፈተና እንዴት እንደተናቀ በሚገባ ታይቷል፡፡ ከአሁን በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ብቻ ሳይሆን የመውጫ ፈተናም ስለሚኖር፣ ወገብን ጠበቅ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ አገር የምትለማውና የምታድገው ጥራት ባለው ትምህርትና ሥርዓት ባለው አስተዳደር ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል የሚያፈሩት የትምህርት ሥርዓቱና አስተዳደሩ ሲስተካከል ነው፡፡ ትምህርት ክብር አግኝቶ አገር የሚያሳድግ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው፣ የዘቀጠው ፖለቲካ ከሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እጁን ሲያወጣ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደፊት በሥራ ላይ ያለው የተማረ የሚባለው ኃይል ጭምር በየሙያው የመመዘኛ ፈተና እየወሰደ፣ ብቃቱ መፈተሽና የሚመጥነው የሥራ መደብ ላይ መመደብ ይኖርበታል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሌላው ትልቁ ተግባሩ የመምህራን ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ብቁና ንቁ መምህራን በሌሉበት ውጤት መጠበቅ ‹‹ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ›› ይሆናል፡፡ በትምህርት ዘርፍ በሚገባ የሠለጠኑ፣ ሙያቸውን የሚወዱ፣ ለአገራቸው ፍቅር ያላቸውና ትውልድ ለመቅረፅ ሙሉ ፍላጎት ያላቸውን መምህራን ማፍራት ትልቁ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ እነዚህ መምህራን ተገቢው ክፍያና ጥቅማ ጥቅም እየተከበረላቸው፣ ሙያው ሳቢና ተፈላጊ እንዲሆን መንግሥት ከፍተኛ ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ትምህርትን ንግድ ማድረግና መሸቀጥ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በትምህርት መስክ የተሰማሩ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ትርፍ በረጅም ጊዜ ልፋት የሚገኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለአገራቸው የትምህርት ዕድገት የበኩላቸውን ቢወጡ መልካም ነው፡፡ አሁን የሚስተዋለው የሸቀጥ ማገላበጥ ዓይነት አጉል ድርጊት ለአገር ምንም የሚፈይደው ስለሌለ፣ ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለአገር ዕድገት የሚረዳ ተግባር ላይ ለመሰማራት ጥረት ያድርጉ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ በሚገባ ተመርቶ ውጤት ማግኘት የሚቻለው ጥቂቶች ትርፍ እያጋበሱበት፣ የሚለፉት ደግሞ እየተራቡበት ስላልሆነ ለመምህራንም ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመማር ማስተማሩ ሒደት የተቀላጠፈና በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን የትምህርት ፖሊሲው መፈተሽ አለበት፡፡ የትምህርት ጥራት ችግሩ መነሻ ፖሊሲው ስለሚሆን፣ በዚህ ላይ የሚመለከታቸው አካላትም ሆኑ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለፉ ባለሙያዎች ይምከሩበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዕገዛ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን ችግር በአንድ ፓርቲ ውሳኔ ወይም በተወሰኑ አካላት ምክክር ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ ሊያመነጩ የሚችሉ አገር ወዳዶች ሳይቀሩ ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ ለትምህርት ተደራሽነት ሰፊ ቦታ በመስጠት ለጥራት ትኩረት ያልሰጠው የትምህርት ፖሊሲም ሆነ ሥርዓተ ትምህርት፣ በተለያዩ ልምዶችና ተሞክሮዎች ታግዞ ከገባበት አረንቋ ውስጥ መውጣት የሚችለው የጋራ ርብርብ ሲደረግ ነው፡፡ መምህራን፣ ወላጆችና ከትምህርት ጋር በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙ አካላት ግብዓትም ያስፈልጋል፡፡ በፈተናው የተገኘው ውጤት ግን የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ መሆኑን መተማመን የግድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...