በደቡብ ክልል የታጠቁ ኃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን፣ የአማሮና የቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤቶች አስታወቁ፡፡ በቡርጂ ልዩ ወረዳ ሁለት ሰዎች ተገድለው ሁለት መቁሰላቸውን፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ ደግሞ አንድ ሰው እንደተገደለና ሰሞኑን በታጣቂዎች ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ጽሕፈት ቤቶቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በቡርጂ ልዩ ወረዳ ሰውና እህል ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የልዩ ወረዳው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቱሎ ዓለሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከሟቾች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ በንፁኃኑ ላይ ጥቃቱን ያደረሱት ከቡርጂ ተነስተው በአማሮ በኩል ወደ ዲላ እየተጓዙበት በነበረው ተሽከርካሪ ላይ ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት መሆኑን አክለዋል፡፡
በንፁኃን ሰዎች ላይ ግድያና ከባድ ጉዳት አድረሰዋል የተባሉት ታጣቂዎች ድርጊቱን የፈጸሙት ከአማሮ ቶሬ ወደ ዲላ በሚወስደው መንገድ ጫካን ተገን በማድረግ መሆኑን፣ ከአሁን በፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ እንደነበር የአማሮ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ጥቃቱን የፈጸሙት አካላት በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ፣ በማጣራት በተገኘው መረጃ ግን የሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ድንገት በተከፈተው ተኩስ በንፁኃኑ ላይ ጉዳት የደረሰው እሑድ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ መሆኑን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በመንገደኞቹ ላይ በተከፈተው ተኩስ ሕይወታቸው ያለፈው ንፁኃን ዜጎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ቱሎ፣ አንዲት ነፍሰ ጡር እናት መገደላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ታጣቂዎቹ በነፍሰ ጡር ሴት ላይ ሳይቀር ጥቃት እያደረሱ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹መንገድ ላይ ጥቃቱን የከፈቱት ሆን ብለው ነው፡፡ በርካታ ጥይት ስለተተኮሰ ተሳፋሪዎች የነበሩበት ተሽከርካሪ የመገልበጥ አደጋ ደርሶበታል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ደጉ ጭራ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ ሁለቱ ንፁኃን ሰዎች መገደላቸውንና ጤፍ ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረው ተሽከርካሪ መዘረፉን ተናግረዋል፡፡
ጫካን ተገን ያደረጉ ታጣቂዎች በተሳፋሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ጉዳት ሲያደርሱ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ አቶ ቱሎ ገልጸዋል፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ በተሽከርካሪ በሚጓዙ ንፁኃን ሰዎች ላይ ከአምስት ጊዜ በላይ ታጣቂዎች ጉዳት በማድረሳቸው፣ በየጊዜው ሁለት ሦስት ሰው የሚሞትበት አጋጣሚ እንደነበረና በአጠቃላይ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡
ሰሞንኛው ጥቃት ደረሰበት በተባሉት አካባቢዎች የሸኔ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ፣ ከዚህም ባሻገር ሸኔን በማሳበብ ሌሎች ማንነታቸው በመጣራት ላይ ያሉ አካላትም ጥቃት እንደሚያደርሱም ተነግሯል፡፡ ከአራት ዓመታት በላይ ታጣቂዎች በአካባቢው የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለማስቆም፣ የመንግሥት ኃይሎችን የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑም አቶ ቱሎ ጠቁመዋል፡፡
በቡርጂ ልዩ ወረዳና በጉጂ ዞን ሲከሰት በነበረው ጥቃት ሳቢያ ተቋርጦ የነበረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በዕርቅ እንዲፈታ በመደረጉ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ የሸኔ ታጣቂዎች መንገድ ላይ ጠብቀው በተሽከርካሪ ውስጥ በሚገኙ ንፁኃን ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከማድረስ አልታቀቡም ተብሏል፡፡
በደቡብ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የታጠቁ ኃይሎች ከአራት ዓመታት በላይ፣ በንፁኃን ላይ የተኩስ ጥቃት እያደረሱ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡