አንድ ሊቅ ሰው ‹‹እኔ ጠንካራ ሠራተኛ ነው አእምሮዬ ሲደነዝዝ ቴኒስ በመጫወት እደሰታለሁ ኀዘኔን ልረሳው እንድችል ያደረገኝ ግን የተዋቡ ሙዚቆችን መስማት ነው፡፡›› አለ በእርግጥም በሰውና በዓለሙ መሃከል ፍጹም ሰላም ሰጭ ሁኖ የሚያስታርቀው የዕርቅ መሥዋዕት ጣዕም ያለው ዘፈንና ሙዚቃ ቃና ነው፡፡
ውብ ድምጽ ያላቸው ወፎች በረሃ ሃገራቸው ነው፡፡ ቃና ባለው ዜማ ከተዋበ ድምፃቸው ጋራ ሲዘምሩ ግን በረሃውን ገነት ያደርጉታል፡፡ እንዳዘነም ልብ የነበረውን ምድረ በዳ የገነት ያህል ሊለውጡት ችሎታ ሲኖራቸው አዳኞች አይተዋል፡፡ እንዲሁም የላባው ውበት ሊያኮራው የሚችል የቁራ አሞራ ደግሞ በዜማውና በድምጹ ክፋት እንደገነት ያማረችውን አገር በረሃ ያደርጋታል፡፡ ሰውም በሚኖርበት ርስቱ ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የተዋጣ ቅያስ ባላቸው መንገዶች መጓዝ አይታው ሁሉ ደስ ያሰኘዋል፡፡
አበበቦችም በተተከሉበት ቦታ መጠለል አዲስ ስሜትና ዕረፍት ይሰጠዋል፡፡ ቅርፁ እጅግ አምሮ በታነፀ ቤት መኖርም ይመቸዋል፡፡ በሰገነት መቀመጥም እጅግ ክብር ያለው ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን የነፍስን አሥራው በማንቀሳቀስ ሰውን ደስ ሊያሰኘው የሚችል ጣዕም ያለው ሙዚቃና ባህል ያለው ዘፈን ባይኖር የማንኛውም የሚታይ ውበት ሁሉ ግምቱ አባይ ይሆናል፡፡
- ተመስገን ገብሬ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (ኅዳር 1935)