Sunday, December 10, 2023

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ ግፊቶች እየታዩ ነው፡፡ የለውጥ ግፊቱ እየመነጨ ያለው በራሱ በመንግሥት ተነሳሽነት መሆኑ ደግሞ፣ የዘርፉን ጥያቄ ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ ሊቀይር ይችላል የሚል ግምት እያሳደረ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሬት በነባሩ የመሬት ሕግ እየተዳደረ መቀጠሉ ዘርፉን ጥቅም አልባ እንዳደረገው በቅርቡ ጠንከር አድርገው ተናግረው ነበር፡፡ መሬት በሕገ መንግሥቱ ‹‹የሕዝብና የመንግሥት›› ነው ቢባልም፣ ካድሬና ደላላ መሬትን በመቀራመት እየከበሩበት እንደሆነ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሬት ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉን፣ እንዲያውም የሙስናና ምዝበራ ምንጭ መሆኑን አጠንክረው ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡ አያይዘውም ቢያንስ የከተማ መሬት ይዞታን ወደ ግል በማዞር፣ በመሬት ሥሪቱ ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ነበር፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ደግሞ መንግሥት የመሬት ፖሊሲውን ለማስተካከል ትልቅ ፍላጎት እንዳለው ግምት እያሳደረ ነው፡፡ ይህ ግምት ሳይቀዘቅዝ እንደተሰማው ከሆነ ደግሞ የገጠር መሬትን መሸጥና መለወጥ የሚያስችል አሠራር ለመተግበር መንግሥት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ተካቶ መቅረቡ በተነገረው በዚህ የገጠር መሬት አጠቃቀም ማሻሻያ ውስጥ ደግሞ፣ በግል ብቻ ሳይሆን በጋራ የመሬት ባለቤት መሆንን የሚፈቅድ አሠራር ተካቷል፡፡ መሬትን አስይዞ የመበደር አሠራርን ጨምሮ የመሸጥና የመለወጥ መብቶች መካተታቸው ተሰምቷል፡፡

ይህ ዕርምጃ መሬት በኢትዮጵያ ትርጉም ያጣ ሀብት ወይም የካፒታል ምንጭ መሆን ያልቻለ ንብረት ሆኗል እየተባለ ሲቀርብ ለቆየው ትችት፣ አንፃራዊ ምላሽ የሰጠ መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን ብድርም ሆነ ድጋፍ አግኝቶ ለማያውቀው፣ እንዲሁም የኢንሹራንስ ሽፋን ለማይሰጠው የግብርና ዘርፍ አዲሱ የመሬት አጠቃቀም ማሻሻያ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር እየተገመተ ነው፡፡

በተንጠለጠለና የባለቤትነት ዋስትና በማይሰጥ የመሬት አሠራር ሕግ የዘለቀው ግብርና ከፋይናንስ በተጓዳኝ ቴክኖሎጂና ዕውቀትን የሚስብ አዋጭ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲሆን፣ የመሬት አጠቃቀም ማሻሻያው ታላቅ ዕርምጃ ስለመሆኑ ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡

ከነዚህ አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የአካባቢ ጥበቃ ሕግ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ ዳምጤ (ዶ/ር)፣ ማሻሻያው ታላቅ ዕርምጃ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

‹‹እግዜር እውነት ባደረገልን እንጂ አዲሱ የገጠር መሬት ማሻሻያ ሙት ሆኖ የቆየውን የመሬት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በእጅጉ ያስነሳዋል፤›› በማለት ነበር፣ በመሬት ሥሪት ሕጎችና አሠራሮች ላይ ሰፊ ጥናት የሠሩት ምሁር የተናገሩት፡፡

በሚዲያዎች በሚያቀርበው የፖለቲካ ትንታኔ የሚታወቀውና በመሬት ሥሪቱ ዙሪያ ‹‹ዲ.መ.ቴ ኢትዮጵያ ዕዳዋ ስንት ነው?›› የተባለ ጥናታዊ መጽሐፍ ያበረከቱት አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በበኩላቸው፣ የመሬት ጥያቄ ረዥም ዘመን ሳይመለስ ያስቆጠረ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጥያቄ መሆኑን ያወሳሉ፡፡

‹‹መሬት ለአራሹ የሚለው በ1960ዎቹ የተነሳው የተማሪዎች አብዮት ሥረ መሠረቱ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው፡፡ የመሬት ባለቤትነት በጥቂት ባላባቶች የተያዘና ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ጭሰኛ ያደረገ ነው በሚል ነበር መሬት ለአራሹ የሚል መፈክርን አንግበው ወጣቶች የተነሱት፡፡ ጥያቄው መጀመርያ ኢኮኖሚያዊ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ እንዲደረግበት ተጠይቆ አልመለስ ሲል ግን በሒደት ወደ ፖለቲካ ትግል አመራ፡፡ ከዚያ በኋላ በመጡ ሥርዓቶች መልስ አገኘ ቢባልም፣ ነገር ግን መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው ተብሎ ባለቤት አልባ ሆኖ ቀረ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ሆነ መለስ ዜናዊ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው በመባሉ ብቻ ገበሬውን የመሬት ባለቤት አድርገናል ይሉ ነበር፡፡ ሁለቱም መሪዎች መሬት ለገበሬው ሰጠን የሚሉት ግን፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገበሬ በመሆኑ የሰፊ ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ገበሬው በመሬቱ ጉዳይ ተጠራጣሪ በመሆኑ ማኅበራዊ መሠረትን ለማስፋት በሚል መሬትን ለአርሶ አደሩ ሰጠን እያሉ፣ በተጨባጭ ግን መሬትን ባለቤትም ሆነ ጥቅም አልባ አድርገውት እንደቆዩ ብዙ አጥኚዎች ከድምዳሜ ደርሰዋል፤›› ሲሉም አቶ ሸዋፈራሁ ያክላሉ፡፡

ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ›› በሚል ርዕስ በ2013 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ መሬትን በሚመለከት ሥር ነቀል ለውጥ አምጥተዋል ስለሚባልላቸው የገጠር መሬት አዋጅና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ የወጡበትን ሒደት በሰፊው አትተዋል፡፡

የጊዜው መሪ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በተለይ የገጠር መሬት አዋጁ ሲወጣ፣ ‹‹ፊውዳሉን ሥርዓት ከሥሩ መንግሎ የሚጥል አዋጅ›› ብለው እንዳሞካሹት በዚህ መጽሐፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ‹‹ደርግ ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል የሚስተካከለው እንደሌለ› የደርጉ መሪ መግለጻችውም ታክሎበታል፡፡

ሆኖም ይህ ለብዙ ዘመናት ጭሰኛ ሆኖ የኖረውን የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከጭሰኝነት በመገላገል የመሬት ባለቤት ያደርጋል የተባለ አዋጅ ያጎናፀፋቸው መብቶች በጊዜ ሒደት መሸራረፋቸው ነው የሚነገረው፡፡ ኢሕአዴግ በደርግ እግር ሲተካ ደግሞ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው በሚል የቀደመውን አዋጅም የሚቀለብስ ድንጋጌ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡  

የመሬት ባለቤትነት በኢሕአዴግ ዘመን ለብሔር ብሔረሰቦች መሰጠቱም ሌላው የዘርፉን ዕድገት ያቀጨጨ በሚል ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ መሬትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ የወጡ ድንጋጌዎች ‹በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀር ሊሻሻሉ አይችሉም› የሚል የፖለቲካ ድምዳሜ ላይ መደረሱም፣ የመሬት ጉዳይን ምላሽ አልባ ሆኖ እስካሁን እንዲቀጥል እንዳደረገው ብዙዎች ይገልጹታል፡፡  

በአንዳንዶች አገላለጽ የፖለቲካ ማስፈራሪያ ሆኖ የኖረውና ከለውጥ ርቆ የቆየው የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት፣ አሁን ግን አስገዳጅ ለውጦችን ማድረግ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገራል፡፡ አሁን የታቀደው የገጠር መሬት አጠቃቀም ማሻሻያ በመሬት ጉዳይ ለረዥም ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ነባር ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን የሚጠራጠሩ ግን ብዙዎች ናቸው፡፡ በተቃራኒው ግን ዕቅዱ በዘርፉ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያስችላል የሚሉትም ጥቂት አይደሉም፡፡  

ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ዕቅዱ ሕገ መንግሥቱንም ቢሆን መለወጥ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ በአዋጅ አውጥቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚቻልና በራሱ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ዕቅድ እንደሆነም ያሰምሩበታል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በተጨማሪ ሲያብራሩም፣ ‹‹ያለፍንበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቆፈን ገና አለቀቀንም፡፡ በአንዴ ሕገ መንግሥትን የመቀየር ዓይነት ትልቅ ለውጥም ለማምጣት ከባድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አንፃራዊ ማሻሻያም ቢሆን በተግባር ከተረጎምነው ውጤቱ ትልቅ ነው፡፡ በግሌ ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው የመሬት ባለቤትነት እንዲቀየር ብፈልግም፣ ያ ዕውን እስኪሆን ድረስ የገጠር መሬትን ወደ ኢኮኖሚ መቀየር ከተቻለ በራሱ ጥሩ ጅምር ነው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ሰፊው አርሶ አደር ማኅበረሰብ የመረጠው መንግሥት ለረዥም ዘመን ያለ ተቀናቃኝ በሥልጣን ለመቆየት ይችላል በሚል ሥሌት ብቻ፣ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመንግሥትና የሕዝብ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች ሀብት ነው የሚል የመሬት ፖሊሲ ለረጅም ጊዜ መስፈኑ መሬትን ጥቅም አልባ አድርጎት እንደቆየ አቶ ሸዋፈራሁ ይናገራሉ፡፡ የመሬት ባለቤትነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዜጎች የበለጠ ለቀቅ መደረጉ፣ እንደ አገር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ይከራከራሉ፡፡

ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. በ1605 እና 1609 አካባቢ ቅኝ ገዥዎቹ እንግሊዞች በአሜሪካ ቨርጂኒያና ጀምስ ታውን ግዛቶች የመሬት ባለቤትነት ማሻሻያ ማድረግን፣ ለምርታማነት ማሳደጊያ እንደ መፍትሔ እንደተጠቀሙበት ያስታውሳሉ፡፡

‹‹በእነዚህ ዓመታት በሁለቱ ግዛቶች ጥቁሮችና ቀይ ህንዶች ነበሩ በቀን ሠራተኝነት የሚሠሩት፡፡ ምርት ሲቀንስ እንግሊዞቹ ምንድነው ብለው ችግሩን አስጠኑ፡፡ በውጤቱ የሚሠራውም የማይሠራውም እኩል ክፍያ እንደሚከፈለውና ይህም ምርታማነትን እንደጎዳ ደረሱበት፡፡ ሌላው ሠራተኞች የሚያገኙት ደመወዝ ለኑሮ እንደማይበቃና ይህም ትጋታቸውን እንደቀነሰው አወቁ፡፡ መፍትሔ ብለው ደግሞ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ አንድ ሔክታር በነፍስ ወከፍ የአንተ ናትና አልማት ብሎ መስጠትን ዘየዱ፡፡ ሠራተኛው በዚህች መሬት ትምባሆና ጥጥ እያመረተ እንዲያስረክባቸው አደረጉ፡፡ መሬት ለአራሾች በመፈቀዱ የተነሳ በዚያ ዘመን ምርታማነት በእጅጉ እንዳደገ ታሪክ ከትቦታል፡፡ ቅኝ ገዥዎቹ እንግሊዞች መሬትን ለግል በማስተላለፍ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ግብርናን ወደ ትልቅ ቢዝነስ እንደለወጡት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ መረዳት ይቻላል፤›› ሲሉ አቶ ሸዋፈራሁ እንደ አንድ ተሞክሮ አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊ የመሬት ድንጋጌ ልክ እንደ ጥንቱ የታሪክ አጋጣሚ ሁሉ መሬትን ጥቅም አልባ የሚያደርግ፣ ስንፍናንም የሚያበረታታ መሆኑን ነው አቶ ሸዋፈራሁ ያስረዳሉ፡፡

‹‹መሬት የብሔር ብሔረሰቦች ነው ብሎ ሕገ መንግሥቱ በዘር የመሬት ባለቤትነትን አረጋግጦ ሳለ ሰው መሬቱን ለማልማት ለምን ይተጋል? ከዓለም ብርቅዬ እንዳደረገን እንደ ዋልያ ሁሉ ከሌላው ዓለም ፍፁም በተለየ ሁኔታ መሬትን ለብሔር ብሔረሰብ ባለቤትነት ሰጥተናል፡፡ መሬትን የሕዝብና የመንግሥት እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች ነው ብለህ ጥቅምም ሆነ ባለቤት አልባ አድርገህ ስለብልፅግና ማውራት አይቻልም፤›› በማለት ነው የመሬት ሥሪቱ የዕድገት መሰናክል እንደሚሆን የተናገሩት፡፡   

የመሬት ባለቤትነት ወደ ግል ቢዞር መሬት ለቅርምት ይጋለጣል የሚል ሥጋት መኖሩ ሌላው የመሬት ሥሪቱን ላለመቀየር እንደ አንዱ ዋና ምክንያት መሆኑ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ መሬት በጥቂቶች እጅ ይገባል የሚለው ሥጋት ለመሬት ሥሪቱ ሳይነካ መቀጠል ሥጋት መሆኑ ይነገራል፡፡ መሬት በግለሰብ ሆኖ ይሸጥ ይለወጥ ቢባል መግዛት የሚችሉ ሰዎች ይጠቀልሉታል የሚለውን የመንግሥት የቆየ መከራከሪያ የሚደግፉ አሉ፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ (ዶ/ር)፣ ‹‹መሬት በጥቂቶች እጅ እንዲገባ አልፈልግም፡፡ ጥቂቶች እንዲጠቀልሉትና እንዲቀራመቱት አልደግፍም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንድ ሰው ምን ያህል መሬት መያዝ እንደሚችል ጣሪያ መቀመጥ አለበት፡፡ እንደ አካባቢው፣ እንደ ክልሉ ወይም እንደ ወረዳው ነባራዊ ሁኔታ አንድ ሰው መሬት ሲገዛ ከዚህ ሔክታር መሬት በላይ መግዛት አትችልም ተብሎ መጠን ሊቀመጥ ይገባል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ ምጣኔን ማስቀመጥ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፤›› ሲሉ ነው ለመሬት ቅርምት ሥጋት መፍትሔ የሚሉትን የሚናገሩት።

የመሬት ሥሪቱን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መቀየር ባይቻል እንኳ፣ የመሬት ባለቤትነትና አጠቃቀም አማራጮች እንዲሰፉ የሚፈልጉ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ እየበረከቱ ናቸው። በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የመሬት አጠቃቀም አማራጮችን ማስፋት እንደማይሞከር የሚያስቡ በርካታ ቢሆኑም እንኳን፣ የሕግ ምሁራን ግን አመቺ የሕግ መንገዶች ለዚህ መኖራቸውን ይናገራሉ።

የፍትሕና ሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት (Justice and Legal System Research Institute) ለሚባለው ተቋም በዳንኤል ወልደ ጊዮርጊስና በመልካሙ በላቸው ተዘጋጅቶ በ2000 ዓ.ም. የቀረበ የሥልጠና ሞጁል ላይ፣ መሠረታዊ የመሬት ሕግ ምንነትንና የመሬት አጠቃቀም ሕጎችን በተመለከተ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሰፊ ትንታኔዎች ሰፍረዋል፡፡

በቀላሉ የሚታወቅ ከሚመስለው ከመሬት ምንነትና የሕግ አተረጓጎም የሚነሳው ሞጁሉ፣ ከመሬት ጋር ስለተያያዙ መብቶችና ሕጎችም በሰፊው ይተነትናል፡፡

የመሬትን የሕግ አተረጓጎም ሲያስቀምጥም፣ ‹‹መሬት ከገጸ ምድር እስከ ውስጠኛው ኮር የሚባለው ጥልቅ የምድር ከርስ ድረስ ያጠቃለለ ነው፤›› ይላል፡፡ መሬት ላይ ያለ ቋሚ ንብረትም ‹‹ከአፈርና ድንጋዩ ጀምሮ፣ ዛፍ ቅጠሉ፣ ቤት፣ አጥር፣ ውኃ፣ የውኃ ጉድጓድ ሳይቀሩ የመሬቱ አካል›› ተደርገው በሕግ ፊት እንደሚታዩ ይዘረዝራል፡፡ መሬት በመሬቱ ገጽ ላይ ያለውን ነገር ብቻ ሳይሆን በዚያ መሬት አፈር ውስጥ የተቀበሩ፣ ‹‹በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ መንገድ የተገኙ ቁሶችን›› እንደሚያጠቃልል ነው የሕግ መማሪያው የሚያስረዳው፡፡ 

የተለያዩ ዓይነት የመሬት ባለቤትነቶች በዓለም ላይ እንዳሉ የሚጠቅሰው ሞጁሉ በዋናነት የግል፣ የጋራና የመንግሥት ተብለው ቢታወቁም ነገር ግን ሌሎች አማራጮች መኖራቸውን ያሳያል።  

ለአብነትም የጥምር መሬት ባለቤትነት (ጆይንት ኦውነርሺፕ) አለ ይላል። በጥምረት የመሬት ባለቤትነት ጊዜ ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የመሬት ባለቤትነቱ ሊይዙ ይችላሉ ይላል፡፡ ለምሳሌ በኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች አካባቢ ያለው መሬት ጥምር ባለቤትነት ያለው ሊባል ይችላል ይላል። በሕጉ ዘንድ የጥምር መሬት ባለቤቶች እኩል መብት አላቸው፡፡ ስምምነት በማድረግም የመሬቱን አስተዳደርና አጠቃቀም በቀላሉ ማስተላለፍ ይችላሉ ሲል ሞጁሉ ይስቀምጣል፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ በኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕጎች የሚታወቅ ነው ይላል።

የጋራ የመሬት ባለቤትነት (ኮመን ኦውነርሺፕ) የሚባል የመሬት አሠራር ሌላ አማራጭ መሆኑ በሞጁሉ ተጠቅሷል። ባልና ሚስት ሲጋቡ አንዱ ለሌላው የመሬት ባለቤትነትን በማጋራት በሁለቱም ጥንዶች መሬቱ እኩል ባለቤትነት ይኖረዋል፡፡ መሬቱ በዚህ ጊዜ አይከፋፈልም። አንዱ የሌላውን ፈቃድና ይሁንታ በማግኘት ነው መሸጥ መለወጥ ማከራየትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት መጠቀም የሚቻለው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕጎች በተለይም በቤተሰብ ሕጉ ላይ የተደነገገ አሠራር ነው ይላል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝም ተራራ፣ መስኖ፣ ሐይቅ፣ ወንዝ፣ ጫካ፣ የግጦሽ መሬትና የመሳሰሉት በዚህ በጋራ መሬት ሥር የሚተዳደሩ ሊሆኑ እንደሚችልም ያትታል፡፡ እነዚህን መሰል የመሬት ባለቤትነቶች የመንግሥት መሬት ተብለው ሊታቀፉ እንደሚችሉ ሞጁሉ ያስረዳል። ከዚህ በመነሳትም የመሬት ባለቤትነትና አስተዳደር በአንድ ወጥ ሕግ ወይም በፖሊሲ አሠራሩ ሊለወጥ ባይችል እንኳ፣ በተለያዩ መንገድ መጠቀም የሚቻልባቸው የሕግ አማራጮች መኖራቸውን ነው የሕግ ሰዎች የሚያስረዱት።

በሌላ በኩል የመሬት አጠቃቀምና ባለቤትነት የተሻለ ለማድረግ ዘርፉ የፖሊሲ ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባል የሚለው ሐሳብም ጎልቶ ይደመጣል። ይህን የዘርፉን የፖሊሲ ክፍተት ትልቁ ራስ ምታት እንደሆነ የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ (ዶ/ር) መሬት ባለቤት የሌለው ዘርፍ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

‹‹የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲው ብቻም ሳይሆን ዘርፉን የሚመራ ተቋምም የለንም፡፡ ሁሉ ነገር የሚሠራው መሬት ላይ ነው፡፡ ትራንስፖርት፣ እርሻው፣ ኢንዱስትሪው፣ ግድቡ፣ ከተማው፣ ወዘተ የሚሠራው መሬት ላይ ነው፡፡ ሁሉም ዘርፎች ደግሞ የሚመራቸው የሚኒስቴር ተቋም አላቸው፡፡ መሬት ግን የለውም፡፡ የሁሉም መሠረትና የበላይ ሆኖ ከሁሉም ወደኋላ ቀረ፤›› በማለት ነው ምሁሩ ክፍተት ያሉትን ያስረዱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -