በጊደና መድኅን
‹‹Every bad system will beat a good person every time.›› W. Edwards Deming
በትግራይ ክልል ከስንት መከራ በኋላ ፖለቲካዊ ለውጥ አይቀሬ ይመስላል። ለ17 ዓመታት በትጥቅ ውጊያ፣ ለ27 ዓመታት በመንግሥትነትና እንደገና በሦስት ዓመታት በተዋጊነት፣ ላለፉት 48 ዓመታት በትግራይ ፖለቲካዊ ምኅዳር የነበረው የተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓሕት – TPLF) ፖለቲካዊ ማሽን ኪሳራው በመብዛቱ አሁን አሁን ወጣቱ ጥያቄ እያስነሳበት ይገኛል። በመሆኑም ለውጥ አይቀሬ ከሆነ፣ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በፖለቲካ ተዋናይነት የቆየው ተሓሕት በትግራይ ክልል የፈጠረውን ፖለቲካዊ ባህል፣ ፖለቲካዊ ገበያ፣ ፖለቲካዊ ሥነ ምኅዳርና የፖለቲካ ተዋንያን ማየቱ የግድ ይላል።
ከዚያም ቀጣዩ የትግራይ ክልል ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ ሕይወት አዋጭ እንዲሆን ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊ፣ አገራዊና ክልላዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ገዥ ሁኔታዎችን የዋጀ ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጥ አለበት፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ተሓሕት፣ በትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ወና (Political Vacuum) እና የትውልድ ክፍተት (Generational Gap) ፈጥሯል ብሎ ያምናል።
ሌላውን ትተን የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ወና (Political Vacuum) እንደምን እናስተካክለው የሚለው ኩነት በቀላሉ የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ አንዳንድ ትልልቅ ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ ሐሳብ መስጠት እፈልጋለሁ።
ፖለቲካዊ ባህላችን (Political Culture) እንዴት ነበር? ምን ይሁን?
ሉችያን ፓይ (Lucian Pye) ፖለቲካዊ ባህል ማለት ለፖለቲካዊ ሒደቱ ሥርዓትና ትርጉም የሚሰጡና የፖለቲካዊ ሥርዓቱን ባህሪ የሚያስተዳድሩ ተነጣፊ (ውስጣዊ) ግመታዎችና መመሪያዎችን የሚያቀርቡ የሁኔታዎች፣ የእምነቶችና የስሜቶች ስብስብ ነው ይሉታል። በሌላ መንገድ ሲታይ፣ ፖለቲካዊ ባህል ማኅበረሰቡ ስለፖለቲካዊ ሥርዓቱ የያዛቸው የወል ዕይታዎችና ፍረጃዎች ስብስብ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ከእነዚህ ብያኔዎች ተነስተን ላለፉት 48 ዓመታት ትግራይ ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ባህል ስንገመግመው አንድ ፓርቲንና መሪዎችን ምትክ አልባ፣ ሁሉን አዋቂዎች፣ አይነኬዎች፣ ዘለዓለማዊ አድርጎ ‹‹የሾመ››፣ ሞግዚታዊነትን (ከላይ እስከ ታች)፣ የጥቂቶች አዛዥ ናዛዥነትን ያነገሠ ባህል ነበር/ነው። ተሓሕት ይህንን የሐሳብ ብዝኃነትን፣ ልዩነትን፣ ተቃውሞን ወዘተ የማይቀበል ፖለቲካዊ ባህል ሕዝቡ ላይ ከትቦታል፣ ቆዳው ላይ ሰፍቶታል፣ በደንብ አድርጎ ነቅሶታል።
ፖለቲካዊ ምኅዳራችንስ (Political Landscape)?
ፖለቲካ ወና (Vacuum) ላይ አይፈጠርም፡፡ ምኅዳር ያስፈልገዋል። የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ምኅዳር የተበላሸው የፖለቲካዊ ባህላችን መገለጫና ተጠቂ ነው። እጅግ አባጣ ጎርባጣ (Rugged) የሆነ፣ ዳገትና ቁልቁለት (Ups and Downs) የበዛበት፣ ኢፍትሐዊ የሆነ፣ አምባገነን፣ ለገዥው ፖለቲካ ፓርቲ የቆመና የተመቸ ሜዳ ነበር/ነው። ገና ተሓሕት ከውልደቱ ጀምሮ የትግራይ ፖለቲካዊ ምኅዳር፣ ከአንድ ድርጅት ውጪ ማስተናገድ የለበትም ብሎ ትግራይ የነበሩ አራት ሽምቅ ተዋጊዎችን በአፈሙዝ አባሯቸዋል። ከዚያ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላም ትግራይን ብቻውን በሞኖፖል በመያዝ የፖለቲካ ምኅዳሩን ተቆጣጥሮት ቆይቷል። ምናልባትም በትልቋ ኢትዮጵያ ከነበሩት ፖለቲካዊ ምኅዳሮች የትግራዩ እጅግ ጠባብ፣ ጥፍንግ ያለ፣ የተወሳሰበና የአንድ ቡድን ፖለቲካዊ መኪና ብቻ የሚሽከረከርበት እጅግ አስቸጋሪ ነበር።
ፖለቲካዊ ገበያው (Political Market)
ገበያ የራሱ ልማዳዊም ይሁን ዘመናዊ ሕግ ያለው ባለሸቀጡም (ሻጩም) ይሁን ባለገንዘቡ (ገዥው) በነፃነት የሚገባያዩበት ነፃ መድረክ ነው። ፖለቲካዊ ገበያም ልክ እንደ ንግዱ ገበያ፣ ሸቀጥ (የፓርቲዎች ፖለቲካዊ ዓላማ) ያለው፣ ገዥ (መራጩ ሕዝብ)፣ ሻጭ (ፖለቲካ ፓርቲዎች)፣ ቦታ (የፖለቲካ ምኅዳሩ)፣ ምርጫ አስፈጻሚ (ምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎች)፣ የሕግ አስከባሪ (ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ወዘተ) ያለው የፖለቲካ ግብይት (Political Merchandise) የሚካሄድበት በሕግና ሥርዓት የሚታዳደር ነፃ ቦታ ነው። የትግራዩን ፖለቲካዊ ገበያ ከወሰድን ግን፣ ተሓሕት ራሱ ሻጭ (ተወዳዳሪ)፣ ራሱ ገዥ (መራጭ)፣ ራሱ አስፈጻሚ፣ ራሱ ሕግ አስከባሪ የሚሆንበትና ብቻውን ተወዳድሮ ራሱ የሚያሸንፍበት ሌላ ሻጭ ብቅ የማይልበት ኢፍትሐዊ የገበያ ቦታ ነበር/ነው።
የፖለቲካ ተዋንያን (Political Actors)
በፖለቲካ ገበያው ውስጥ እውነተኛ፣ ባለመርህ፣ ሀቀኛ፣ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ አገርንና ሕዝቡን የሚወዱ፣ አዋቂ የፖለቲካ ተዋንያን ማግኘት መታደል ነው። የትግራይ ክልል የፖለቲካ ተዋንያን ሲፈተሹ በተለይም መሪ ተዋናዮቹ (The Protagonists) የገዥው ፓርቲ (ተሓሕት) መሪዎችና አባላት ናቸው። በትግራይ ፖለቲካዊ ምኅዳርና ገበያ የናኙበት እነዚህ ፖለቲካዊ ፍጥረቶች ብቻቸውን ነበሩ። በ2012 ዓ.ም. ባካሄዱት ምርጫ ግን የተሓሕት መሪዎች ሌሎች ጫጩት ተዋንያንን ፈልፍለው የፖለቲካ ቴአትር በመተወን፣ እንደተለመደው አንድ ወንበር ብቻ ከአዲሶቹ ተዋንያን ለአንዱ በችሮታ በመተው መቶ በመቶ የፖለቲካ ቴአትር ቤቱ (ክልላዊ ምክር ቤቱ) ወንበሮችን ተቆጣጠሩዋቸው።
ከላይ ለማየት እንደ ተሞከረው የትግራይ ክልል በተለይም ላለፉት መቶ ዓመታት ፖለቲካዊ ትኩሳት የማይለየው (Politically Charged የሆነ) አካባቢ ቢሆንም፣ እንዳለመታደል ሆኖ ጦርነት የማይለየው፣ የአምባገነኖችና የጨካኞች መፈንጫ፣ የዴሞክራሲ ሽታ ይሁን የሕዝብ ወሳኝነት የሌለበት፣ ተንኮልና ሸር የሚዘውሩት ፖለቲካዊ ማሽን የተተከለበት አካባቢ መሆኑ ያሳዝነኛል።
በትግራይ ክልል ለውጥ አይቀሬ ከሆነ ምን እንጠብቅ?
መቼስ ካሁን በኋላ ተሓሕት በትግራይ ፖለቲካዊ ምኅዳር አዛዥ ናዛዥ የሚሆንበት፣ የፖለቲካዊ ገበያውን እንደፈለገ የሚነግድበትና ብቻውን መሪ የፖለቲካ ተዋናይ (Protagonist) በመሆን ፖለቲካዊ ሥልጣኑን የሚቆጣጠርበት ጊዜ ያበቃ ይመስለኛል። በትግራይ ወጣት ላይ የምመለከተው የለውጥ ስሜትና በተሓሕት ላይ የሚያሳየው የተቃውሞ ግለት እንዲህ እንድል አድርጎኛል።
ከላይ የተቀመጡት ወሳኝ ፖለቲካዊ ዕሳቤዎች በወጉ ተረድቶ አዋጭና ተገቢ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የትግራይ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ለማያዳግም ለውጥ መነሳት አለበት። የትግራይ ሕዝብ ላለፉት 48 ዓመታት ተቀልዶበታል፣ በመስዋዕትነቱና በዕጣ ፈንታው ቁማር ተጫውተውበታል።
- የሚመጥነውና የሚያዋጣው፣ ዴሞክራሲንና ማኅበራዊ ፍትሕ የሚመጣበት፣ ሕዝባዊ መንግሥትን የሚተክል የፖለቲካ ባህል መቅረፅና መላበስ አለበት።
- እውነተኛ፣ ባለመርህ፣ ሀቀኛ፣ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ አገርንና ሕዝቡን የሚወዱ፣ አዋቂ ተዋንያን የሚፈጠሩበት መድረክ ያስፈልጋል።
- የተደላደለ፣ ነፃና ፍትሐዊ የሆነ፣ ማንም ሕጋዊ ፖለቲካዊ ግለሰብ ይሁን ፓርቲ የሚሳተፉበት ፖለቲካዊ ምኅዳር መፍጠር ያስፈልጋል።
- ፖለቲካዊ ገበያውም ለሁሉም ሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት የሆነ፣ ግልጽ የግብይት ሕግ ያለው፣ ሐሳቦችና የሐሳብ ፍጭቶች የሚካሄዱበት፣ የፖሊሲ አማራጮች በግልጽነት የሚቀርቡበት፣ ሕዝቡም በነፃነት አማራጮችን ዓይቶና መዝኖ የሚያዋጣውን የሚመርጥበት ብሎም መሪዎቹን በካርዱ የሚሾምበትና የሚሽርበት መድረክ መሆን አለበት።
የትግራይ ሕዝብ የዘመናት የዴሞክራሲ፣ የማኅበራዊ ፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው። በመሆኑም እስካሁን የትግራይ ሕዝብና ልጆቹ የከፈሉት የሕይወት፣ የአካል መስዋዕትነትና ሌሎች ኪሳራዎች ካሁን በኋላ መክፈል የለበትም። በመሆኑም ቀጣይ ዕጣ ፈንታው በ‹‹አውቅልሃለሁ ባይ›› ፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን ሊወሰንለት አይገባም። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስተካከል፣ ፖለቲካዊ ባህሉን ፈትሾ በመቃኘትና ፖለቲካዊ ገበያውን ለሕዝቡ ጥቅምና ክብር በሚፈይድ መንገድ በማስኬድ መሪዎቹን በጥይት ሳይሆን በኮሮጆ የሚሾምበት፣ የሚሽርበትና በሌላ አገላለጽ ሕዝቡ ሥልጣኑን የሚቆጣጠርበት ጊዜ አሁንና አሁን ነው።
የትግራይ ወጣትም በአንተ ሕይወት፣ አካልና መፃኢ ዕድል በሴረኛና ስግብግብ የፖለቲካ ተዋንያንና የፖለቲካ ማሽን ተቀልዶብሃል፣ ቁማር ተጫውተውብሃል። ስለዚህ ያለፈውን ጉዞህን ገምግም፣ የሚያዋጣህን መንገድ ምረጥ፣ አትሸወድ፡፡ ዝለል ስትባል ዝምብለህ የምትዘል ሳይሆን ዝለል ያለህ ማን እንደሆነ፣ ለምን ዓላማ ዝለል እንዳለህ፣ ምን ያህልና ወዴት አቅጣጫ እንደምትዘል፣ በመዝለልህ አንተና ሕዝቡ ምን እንደሚጠቀም መጠየቅና መገምገም ይገባሃል። ስላንተ ሕይወትም ሆነ አካል መጉደል የሚጨነቅ ምንም ፖለቲካዊ ተዋናይ አይኖርም፡፡ ይብላኝላት ለወለደችህ እናትህ እንጂ!
በተጨማሪም ወጣቱ ጠያቂነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ በልዩነት ማመንን፣ አንባቢ መሆንንና ዕውቀት መላበስን፣ ሕዝብን መውደድ፣ ፖለቲካዊ ሴራን ማወቅና ማጋለጥን፣ ወዘተ የመሳሰሉ ፖለቲካዊ ባህሪዎችን በመላበስ ከደቦ አስተሳሰብና ፍርድ በመውጣት፣ የትግራይ መፃኢ ዕድል በእጁ ሊያስገባና የትግራይ ፖለቲካዊ ገበያን መቆጣጣር አለበት። ብሎም አብዛኛው ወጣት የትግራይ ሕዝብን በማሳተፍ የሚቆጣጠረውና የሚዘውረው ፖለቲካዊ ምኅዳር መፍጠር የግድ ይለዋል።
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ይህ ድርጅት ተሓሕት (TPLF) እንጂ ‹‹ወያነ›› የሚለውን የሕዝቦች (የእንደርታ፣ የራያ፣ የተንቤን፣ የኽልተ አውላዕሎ፣ ዓጋመ፣ ወዘተ) ለፍትሕና ለእኩልነት ያደረጉትን ቀና ትግል በውስጡ ያለበትን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት – TPLF) አይገባውም ብሎ ያምናል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው goldenethiopiagid@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡