በዳግም መርሻ
በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመንግሥት ሥልጣን ምንጭና ባለቤት ሕዝብ ነው። በዚህም ምክንያት የሥልጣን መንበሩን የያዘው መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው፡፡ ተብሎ ይታሰባል። ዴሞክራሲ የሕዝብ፣ በሕዝብና ለሕዝብ የቆመ ሥርዓት (A government of the people, by the people and for the people) ነው ሲባል ይህንኑ እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው። በዴሞክራሲ ሥርዓት የመንግሥት ህልውና በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታትና ጥያቄዎቹን መመለስ ይጠበቅበታል። ስለሆነም በዴሞክራሲ ሥርዓት የመንግሥት ጥንካሬና ውጤታማነት ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው፣ በምርጫ ወቅት በተገባው ቃል መሠረት የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎት በቅንነትና በታማኝነት መመለስ መቻሉ ነው። ይህ ደግሞ ሕዝብ በመንግሥት ላይ የሚኖረው ዕምነት ከፍ እንዲል ከማድረጉ በዘለለ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተሻለ መቀራረብና የሰመረ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ከዚህ በተቃራኒው በሕዝብ ፈቃድ ወደ ሥልጣን የመጡ ተመራጮች ለሕዝብ የገቡትን ቃል ችላ በማለት ከሕዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲሠሩ መገኘታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ዕምነት እንዲያጣ ብሎም ድጋፍ እንዲነፈገው ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል እንደ አንዱ ይጠቀሳል። “የመንግሥት ተዓማኒነት” ሲባል ዜጎች በመንግሥት፣ በመንግሥት ተቋማትና መዋቅሮች፣ መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ላይ፣ እንዲሁም በየተዋረዱ ያሉ አመራሮች ለሕዝብ የገቡትን ቃል መጠበቅ በቻሉበት ደረጃ በብቃታቸው፣ በሀቀኝነታቸውና በታማኝነታቸው ላይ ሕዝቡ ያለው ዕምነት ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንግሥት በማዋቀራቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መዋቅሮች አማካይነት በሥልጣን ላይ ያሉት አመራሮች/ባለሥልጣናት በሚሰጡት አገልግሎት ልክ፣ ሕዝቡ የሚሰጠው የዕውቅና ሰርተፊኬት ወይም በእኛው አማርኛ ‹ቅቡልነት› ነው ማለት ይቻላል።
ዜጎች በጥቅል መንግሥት በሚባለው አካል ላይ ካላቸው አመኔታ በተጨማሪ፣ ለልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማትና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አመራሮች የተለያየ አመኔታና ዕይታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር በጥቅሉ በመንግሥት ላይ ካላቸው አመኔታ በተለየ በሕግ አውጭው፣ በሕግ ተርጓሚው፣ በመከላከያውና በፖሊስ፣ እንዲሁም በሌሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት ላይ የተለያየ ዕምነትና ዕይታ ሊኖራቸው ይችላል ማለት ነው፡፡
ዜጎች በመንግሥት ላይ የሚጥሉት የአመኔታ መጠን እንደ አገሩ የመንግሥት ሥርዓት ይለያያል። ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ባሉ የፕሬዚዳንታዊ መንግሥታዊ ሥርዓትን በሚከተሉና ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ በሕዝብ በሚመረጥበት አገር፣ በግል በፕሬዚዳንቱ ላይ የሚኖር የሕዝብ ዕምነት በአጠቃላይ ለአገዛዙ ተቀባይነት ማግኘት ወሳኝ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ አለ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ደግሞ መሪው ለሥልጣን የሚበቃው በቀጥታ በሕዝብ ተመርጦ ባለመሆኑ በመሪው ላይ የሚኖር አመኔታ በገዥው ፓርቲ፣ በአስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው ላይ ለሚኖረው አመኔታ ወሳኝነት ላይኖረው ይችላል።
የሕዝብ አመኔታ ለአንድ ፖለቲካዊ ሥርዓት ቅቡልነትና ቀጣይ ህልውና ወሳኝ ጉዳይ ነው። የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበትና ድምፁ የማይሰማበት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው የውክልና ዴሞክራሲ የሕዝብን አመኔታና ቅቡልነት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም የሕዝብ አመኔታ ማሽቆልቆል የውክልና ዴሞክራሲን ዕውን መሆን የሚገዳደር ነው። ምክንያቱም የዴሞክራሲ ሥርዓት/ተቋማት ቅቡልነትና ህልውና ሕዝቡ ባለው አመኔታ ላይ ስለሚመሠረት ነው።
ሕዝብ በመንግሥትና በተቋማቶቹ ላይ አመኔታውን ሲጥል፣ የሚወጡ ፖሊሲዎችንና የልማት ዕቅዶችን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። እንዲሁም መንግሥት ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ያላቸው ተገዥነት ይጨምራል። ለተፈጻሚነታቸውም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ በማድረግ በኩል ያለው አበርክቶ የላቀ ነው። በመሆኑም የሕዝብ አመኔታ በአንድ አገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ቁልፍ ነገር ነው። ስለሆነም የመንግሥት ፖሊሲ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከቻለ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከተሳነው ፖሊሲው የዜጎችን አመኔታ እንዳላገኘ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
የሕዝብ አመኔታ ለአገር ኢኮኖሚ መነቃቃትና ማደግ ያለው ድርሻም ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ አኳያ የሕዝብ አመኔታ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ያለ ሥጋት ወደ ሥራ እንዲሠማሩ፣ በርካታ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩና የተሳለጠ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል። በተቃራኒው የሕዝብ ዕምነት ማጣት ከላይ የተዘረዘሩት ጠቀሜታዎች እንዳይኖሩ በማድረግ፣ አገርና ሕዝብን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። ይኸውም በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎችን ለማክበርና ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ካለመሆን ጀምሮ የብሔራዊ ሥጋት ምንጭ እስከ መሆን የሚደርስ አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚያስረዱት በተወሰነ ደረጃ ወይም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የሕዝብ ዕምነት ማጣት ትልቅ ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የአምባገነን አገዛዝ ባለበትም ሆነ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ዜጎች የገዛ መንግሥታቸውን መጠራጠራቸው የተለመደና ተፈጥሯዊ በመሆኑ ነው። በዚያው ልክ የመንግሥት ሹማምንት የቱንም ያህል ቅንና መልካም ሰዎች ቢሆኑም፣ በማንኛውም ወቅት ለሕዝብ የገቡትን ቃል ሊዘነጉ፣ ችላ ሊሉና ከሕዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲፈጽሙ መገኘታቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ አደጋ የሚሆነው ግን ችግሩ መከሰቱ ሳይሆን፣ መንግሥት ለሕዝብ ዕምነት ማጣትና ለቅሬታው መከሰት መንስዔ ለሆኑ ጉዳዮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በተለመደው አካሄድ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን የሚመርጥ ከሆነ ነው፡፡
በአንድ ወቅት የሕዝብ አመኔታ ያጣ መንግሥት በሌላ ጊዜ የሕዝቡን ስሜት ተረድቶ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች የሕዝብ አመኔታና ድጋፍ መልሶ ሊያገኝ ይችላል። በተመሳሳይም በሆነ ወቅት የሕዝብ አመኔታ የነበረው መንግሥት በሌላ ወቅት አመኔታው ተሸርሽሮ፣ መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል። ይህ የሚያሳየው ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ አመኔታ የሚጥሉት መንግሥት ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት እንደሚቆም እርግጠኛ ሲሆኑ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ የመንግሥት የመታመን ጉዳይ ሊመጣ የሚችለውም መንግሥት ራሱ ስለራሱ መልካም ሥራዎች ስላወራና ስለሰበከ ሳይሆን፣ ዜጎች ራሳቸው መንግሥት መልካም ነገር እየሠራላቸው መሆኑን በተጨባጭ ሲያዩና ሲገነዘቡ ብቻ ነው፡፡
ዜጎች መንግሥት ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ ትክክለኛውን ሥራ እየሠራ ነው ብለው ሲያምኑ ከፍተኛ እምነት ይጥሉበታል፡፡ በሌላ በኩል ከዜጎች ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ሥራ እየሠራ ነው ብለው ሲያስቡ ደግሞ አመኔታ ይነፍጉታል፡፡ ቁምነገሩ የሕዝብ አመኔታ መሸርሸር ገደቡን አለማለፉና በአገር ላይ የከፋ ቀውስ አለማስከተሉን ማረጋገጥ ነው።
የሕዝብ አመኔታ ፋይዳው እጅግ ብዙ ቢሆንም የተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሪፖርቶችና በሕዝብ አስተያየት ጥናት ውጤቶች መሠረት፣ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው አመኔታ በበርካታ አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ (Trust Deficit) መጥቷል። በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የሕዝብ ቅሬታ፣ አመፅና ግጭት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማሉ። ደረጃው ይለያይ እንጂ የሕዝብ አመኔታ መሸርሸር በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲ ቁንጮ ተብላ በሚነገርላት አሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊያን አገሮች ሳይቀር በተጨባጭ ሲከሰት ይስተዋላል። ለምሳሌ አሜሪካውያን በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት ከምንጊዜም በላይ እጅግ በወረደ ደረጃ እንደሚገኝ፣ የተለያዩ ጥናቶችና የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ባሮ ሜትሮች ያመላክታሉ፡፡ ‹‹Pew Resaerch Center›› የተሰኘው ታዋቂ የጥናት ማዕከል እ.ኤ.አ. በ2022 የሕዝብ አመኔታን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው አንድ ጥናት፣ ከአሥር አሜሪካውያን ሁለቱ ወይም 20 በመቶ ብቻ የሚሆኑት በመንግሥት ላይ እምነት እንዳላቸው አመላክቷል። ይሁንና እ.ኤ.አ. በ1958 በተደረገ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ሦስት አራተኛ (3/4) የሚሆኑ አሜሪካውያን በመንግሥታቸው ላይ አመኔታ የነበራቸው ሲሆን፣ ይህም በሌሎቸ ጊዜያቶች ከነበረው ሁነታ ጋር ሲነፃፀር ትልቅ ቁጥር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ከዚያ በኋላ ግን በ1960ዎቹ የቬትናም ጦርነትን ተከትሎ እንዲሁም በ1970ዎቹ በሪቻርድ ኒክሰን አስተዳደር የወተር ጌት ቅሌት ባስከተለው መዘዝና በአገሪቱ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት፣ የሕዝብ እምነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሽቆልቆል ችሏል፡፡ ይህ ሁኔታ በ1990 መጨረሻ አካባቢ በአገሪቱ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ መሻሻል እያሳየ የመጣ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 9 ቀን 2011 ከተከሰተው የኒዮርክ የሽብር ጥቃት በኋላ የሕዝብ አመኔታ እንደገና ሊያንሰራራ ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ የሕዝብ አመኔታ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የሕዝብ እምነት ማጣት በብዙ አገሮች ከፍ ያለ የፖለቲካ ኪሳራ አስከትሏል። አሁንም በማስከተል ላይ ነው። ለምሳሌ የዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የአገርና የሕዝብን ጥቅም ወይም ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም ተብሎ ሲታሰብ፣ አልያም የዜጎች እምነት እየቀነሰ ሲሄድ የአገሪቱ ፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ በማድረግ መሪዎቹ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ወይም ከሥልጣናቸው ዘወር እንዲሉ የሚደረግበት አካሄድ፣ እንግሊዝና ጃፓንን በመሳሰሉ አገሮች የተለመደ ነው። በተመሳሳይም አንዳንድ መሪዎች የነደፉት ፖሊሲ ወይም ዕቅድ ድጋፍ አላገኝ ሲልና የመተማመኛ ድምፅ ሲነፈገው ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቃሉ። ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ እምነት መልሶ ለማግኘት ይፋ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታያል። ጃፓን ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናት። ጃፓን ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሕዝብ አመኔታ ሲሸረሸር ፈጣን ፖለቲካዊ ውሳኔ በመወሰን ሥልጣን ቶሎ በመልቀቅ ይታወቃሉ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2012 ባለው ስድስት ዓመት ገደማ ጃፓን ስድስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለዋውጣለች።
በእንግሊዝም ተመሳሳይ ተሞክሮ አለ። በዚህ ረገድ አገሪቱ በስድስት ዓመታት ውስጥ አምስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለውጣለች። ለምሳሌ በቅርቡ ተሹመው የነበሩት ሊዝ ትረስን ብንወሰድ ሥልጣን ላይ የቆዩት ለስድስት ሳምንታት ብቻ ነው። እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ሳይቆዩ ከሥልጣን እንዲወርዱ የተገደዱበት ምክንያት ለገቡት ቃል አልታመኑም በሚል በደረሰባቸው ጫና ነው። የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሮንና ቴሬዛ ሜይም ተመሳሳይ ዕጣ ያጋጠማቸው መሪዎች ናቸው።
ሌላው ተቀባይነት ያለው (Legitimate) የመንግሥት ሥርዓትን ለመገንባትና የሕዝብን ዕምነት ለማሳደግ አገሮች ከሚወስዱት ዕርምጃዎች መካከል፣ ከሕዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች የፖሊሲ ሪፎርም፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ (አሜንድመንት) እንዲሁም፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት ነው። ከዚህ አኳያ አሜሪካ ወደ 27 ጊዜ፣ ፈረንሣይ 24 ጊዜ፣ ደቡብ አፍሪካ 17 ጊዜ፣ ህንድ 103 ጊዜ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረጋቸው ከዚህ መሠረተ ሐሳብ በመነሳት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በሌላ በኩል አንዳንድ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገሮች ለይስሙላ ብቻ ሳይሆን በተግባር ነፃ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ በማካሄድ ቅቡልነት (ሌጅትመሲ) ያለው መንግሥት ለመመሥረትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ጠንክረው እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ በአኅጉራችን ጋናን፣ ሴኔጋልን፣ ደቡብ ከፍሪካን፣ ቦትስዋናን… ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በጥቅሉ እነዚህና መሰል ዕርምጃዎች ከለውጥ ጋር ለመራመድ፣ የረጋ አገረ መንግሥትን ለመመሥረትና የሕዝብ አመኔታን ለማሳደግ በር ይከፍታሉ። ችግሮች ሳያድጉ እንዲቀጩም ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ መንግሥትንና የመንግሥት ሥርዓትን ያለማመን ችግር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን፣ በርካታ አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። በታሪካችን በተለይ ከዘውዳዊ ሥርዓት በኋላ መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ የሚያደርጋቸው በርካታ ግፎችና ወንጀሎች በዜጎች ላይ ተፈጽመዋል። አገሪቱ ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን በማፈን፣ በማስጨነቅ፣ እንዲሁም ግድያን ጨምሮ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽሙ በቆዩ መንግሥታትና መሪዎች መዳፍ ሥር ያለፈች በመሆኗ፣ አብዛኛው ሕዝብ ለመንግሥትና ለፖለቲካዊ ተቋማት ያለው አመለካከትና ዕይታ አሉታዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። “ፖለቲካን በሩቁ” የሚለው የቆየ አገራዊ ብሂልም ይህንኑ ታሪካዊ እውነታ መሠረት ያደረገ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ስም ምለውና ተገዝተው ወደ ሥልጣን የመጡ መንግሥታትና መሪዎች በቃል አልገኝ ብለው ያሻቸውን ፖሊሲና ሕግ ሕዝቡ ላይ ሲጭኑበትና በተለያየ መንገድ በደል ሲፈጽሙበት ስለኖሩ፣ ለመተማመን በር ከዘጉ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። ቀደም ባሉት ሥርዓቶች ገዥዎቹ ውግንናቸው ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ማደላደል ላይ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው ሲሠሩ መቆየታቸው፣ የሚሠሯቸው ተግባራት የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት የማይመጥኑ መሆናቸው፣ እንዲሁም አገርን በማሳደግ ወደ ዴሞክራሲ ከማምራት ይልቅ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጩ ተግባራትን በመፈጸም አገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲመሩት በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች አላስፈላጊ ሁኔታዎች ተደማምረው ሕዝብና መንግሥት የማይግባቡ አካላት እንዲሆኑ አድርገዋል። በዚያው ልክ መንግሥትና የሕዝብ አገልጋይነትም እንዲፋቱ አድርጓል።
እነዚህ ሁኔታዎች ሄደው ሄደው ሕዝብ ያለማመኑ ስሜት ወደ ቅሬታ፣ ቅሬታው ደግሞ ወደ ብሶትና ብሶቱ በጊዜ ሒደት ወደ ተቃውሞ እንዲያመራ ምክንያት ሆኖ አሁን እየታየ ያለው የለውጥ ሒደት ላይ ደርሰናል። በ2010 ዓ.ም. አጋማሽ የተደረገውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አመራር በኅብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና በሕዝቡ ዘንድ ያለውን መጥፎ ስሜት ለመቀየር የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም እስረኞችን በመፍታት፣ የቀድሞ የመንግሥት አስተዳደር በአገዛዝ ዘመኑ ለፈጸማቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሕዝብን ይቅርታ በመጠየቅ፣ በውጭ ሆነው ሥርዓቱን በትጥቅና በሰላማዊ መንገድ ሲቃወሙና ሲታገሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የነፃነት ታጋዮች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ አገራቸው እንዲገቡ፣ የተከሰሱባቸው ወንጀሎችም እንዲሰረዙ በማድረግ ከሕዝብ ጎን መቆሙን አረጋግጧል። በዚህ ሳቢያም ይህ መንግሥት የእኔ መንግሥት ነው የሚል አስተሳሰብ ለመጀመርያ ጊዜ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ሊፈጠር ችሏል።
ይሁንና ከተወሰኑ ወራት በኋላ መንግሥት በብዙኃን ዘንድ በተወሰነ ደረጃ እምነት እያጣ እንዲሄድ ያደረጉ ምክንያቶች እዚህም እዚያም ተፈጥረዋል። በእስካሁኑ ሒደት በአንድ በኩል ሪፎርሙ ወደ ታችኛው የመንግሥት እርከንና ልዩ ልዩ ተቋማት አልወረደም፣ የሕግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም የሚሉ ሐሳቦች ሲንፀባረቁ ይስተዋላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከማኅበራዊ እሴቶቻችንና ዘመናትን ካስቆጠረው ባህላችን ጋር የማይሄዱ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ ታይተዋል። አልፎ አልፎ በየቦታው ሲከሰቱ የነበሩትን ግጭቶች፣ የሰላም መደፍረስ፣ የሕዝብ መፈናቀሎች፣ ጽንፍ የወጣ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ፣ ወዘተ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም አልፎ አልፎ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የፍትሐዊነት መርህና አካሄድን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ አንድምታዎች የሚነሱ እንደ መሆኑ መጠን፣ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ለፖለቲካ ቅሬታ መፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል።
ስለዚህ መንግሥት ጥርጣሬን በማስወገድ መተማመንን ለመፍጠር ድክመቶቹን ማረም፣ በተለይ ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቀነትን ማስፈን፣ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ ዜጎችን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህን ደግሞ በየደረጃው ካሉ ባለሥልጣናቱ ሊጀምር እንደሚገባ የብዙዎች እምነት ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው dagimmersha@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡