Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የማኅብረሰብን ጤና ለመጠበቅ ተብሎ ምክር ቤቱ ያፀደቀውን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ የሚጥስ በመሆኑ፣ ማሻሻያ ሳይደረግበት እንዳይፀድቅ ተጠየቀ።

ቅሬታ አዘል ጥያቄውን በግልጽ ወጥቶ ያቀረበው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን ቢሆንም፣ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በማኅበረሰብ ጤና ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ረቂቁ የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ አሁን ያለውን ይዘት እንደያዘ እንዳይፀድቅ እየተንቀሳቀሱ ነው።

ለተቋማቱ ቅሬታ ምክንያት የሆነው ከአራት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112 ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚሽር ሆኖ በመገኘቱ ነው።

‹‹የማኅበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ ሲባል በፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1112 ላይ የትምባሆ ምርት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት የተደነገገ ከመሆኑ ባሻገር፣ እንደ ሺሻና ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ክልከላ ተጥሏል፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሔራን ገርባ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ለካንሰርና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጠው ትምባሆ አጫሾች ቁጥርን ለመቀነስና ምርትና ሥርጭትን ለመቆጣጠር፣ በመንግሥት የተረቀቀውን ጥብቅ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ በማፅደቁ ከዓለም የጤና ድርጅት ሽልማትና ዕውቅና ለምክር ቤቱ መሰጠቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን እንዴት ማለፍ እንደቻለ ለማወቅ የቸገራቸው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መቅረቡን ገልጸዋል።

ይህ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ኤሌክትሮኒክስ ሲጋራ፣ ሺሻና የሺሻ መጠቀሚያ ፒፓዎች ላይ የኤክሳይስ ታክስ የሚጣል መሆኑ ተዘርዝሮ መቅረቡን የገለጹት ወ/ሮ ሔራን፣ እነዚህ የትምባሆ ምርት ዓይነቶች ወደ አገር እንዳይገቡ በአዋጅ ቁጥር 1112 ላይ መደንገጉን ገልጸዋል።

‹‹ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት የኤክሳይስ ታክስ ክፍያ ምጣኔ ማሻሻያ የተደረገባቸው ምርቶች ዝርዝር ከረቂቅ ሰነዱ ጋር ተያይዞ አለመቅረቡን ሰምቻለሁ፡፡ አሁንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሰነድ ላይ የምርቶች ዝርዝር አለመያያዙን ተረድቻለሁ፤›› የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ‹‹ይህ ለምን ሊሆን ቻለ ብሎ ፓርላማው መጠየቅ አለበት፤›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ የትምባሆ ምርት ሥርጭትን በመቀነስ የማኅበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮንቬንሽን በመፈረም ጥብቅ አዋጅ በማፅደቅ ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ባለበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርንም ሆነ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣንን ሳያወያይ የሕግ ጥሰት የሚያስከትል ማሻሻያ አዋጅ ለፓርላማ ማቅረቡ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ለፓርላማ የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ በትምባሆና ስኳር ላይ ተደራራቢ የኤክሳይስ ታክስ የተጣለ በመሆኑ፣ በአምራቾቹ ተወዳዳሪነታቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን ያስከተለ በመሆኑ ማሻሻያ መደረጉን ይገልጻል።

ወ/ሮ ሔራን፣ ‹‹የማኅበረሰብ ጤና ነው፣ የአምራቾቹ ተወዳዳሪነት ነው የሚቀድመው፤›› ሲሉ አመክንዮውን ተቃውመዋል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ በረቂቁ የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ላይ የተጨመረ አዲስ የምርት ዓይነት የለም። ማሻሻያው የታክስ ምጣኔን የተመለከተ ብቻ ነው፤›› ብለዋል።

አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት፣ ‹‹እንደ አዲስ የተጨመረ የምርት ዓይነት የለም፡፡ ቢኖር እንኳን የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ አዋጁ ያኛውን አዋጅ ድንጋጌ ሊሽር አይችልም፤›› ብለዋል።

የሕዝም ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ በዝርዝር እንዲታይ ለበጀትና ለፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ የጤናና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴንም በአጋርነት ሊመድብ እንደሚገባ በተጨማሪ ቅሬታነት ቀርቧል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች