Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም ዕጦት ግን ጊዜ የማይሰጥና አንገብጋቢ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ሰላም ሲደፈርስና መረጋጋት ሲጠፋ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ይቸግራቸዋል፡፡ የምግብም ሆነ የሌሎች ምርቶች እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል፡፡ ሰላም አስፍኖ ወደ ልማት መሰማራት የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይ መሆን ቢገባውም፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ ያዳገተ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት የምግብና የሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ በየቀኑ አልቀመስ እያለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የምግብ ዋጋ ንረት የብዙዎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ ገበያ ውስጥ በቂ የምግብ ምርቶች አቅርቦት ካለመኖሩም በላይ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱም በሕገወጦችና በተባባሪዎቻቸው ተቀፍድዶ በመያዙ ብዙኃኑ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል፡፡ የምግብ ዋጋ ንረት በፍጥነት ካልተረጋጋ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በምግብ ዋጋ ንረት ዚምባቡዌን በመከተል ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ከዓለም ደግሞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ናችሁ ሲባል ደንገጥ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ሲለመንላቸውም፣ ችግሩ አስፈሪ መሆኑን መረዳት የግድ ይላል፡፡

የምግብ ዋጋ ንረት ከፍተኛ ትኩረት ካልተሰጠውና ፈጣን ዕርምጃ ካልተወሰደ፣ አገራዊ ሥጋት ሆኖ እንደሚቀጥል ያስታወቀው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት እንዳስታወቀው፣ ከሃምሳ በላይ በሚሆኑ ትርፍ አምራችና የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱም የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም፣ የማምረቻ ወጪዎች መናር፣ የመንግሥት ወጪዎችና የገንዘብ ፍሰትና ከትክክለኛው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር አለመጣጣም፣ እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱ ኋላቀር መሆን ወይም አለመዘመን የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡ በአጭር ጊዜ በምግብ ዋጋ ንረት በጣም ተጎጂ የሆኑ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ከውጭ ገበያዎች መሠረታዊ የምግብ ምርቶችን በማስገባት አቅርቦትን ማሳደግ፣ ኢኮኖሚው ውስጥ የተሠራጨውን ገንዘብ ከትክለኛው ዕድገት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በረዥም ጊዜ ደግሞ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ምርታማነት መጨመር፣ የመካከለኛና ከፍተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ማስፋፋት የሚሉት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በዚህ ደረጃ የምግብ ችግር ብሔራዊ ሥጋት ሲሆን ያስደነግጣል፡፡

ለምግብ ዋጋ ንረት በምክንያትነት ከተጠቀሱት በተጨማሪ በርካታ ጉዳዮች ስለሚኖሩ ሰፋ ያለ ጥናት ማድረጉ አስፈላጊ ሲሆን፣ አሁን ካለው አጣዳፊ ሁኔታ አኳያ መንግሥት የችግሩን ፅናት ተገንዝቦ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳንስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሳይቀሩ በከባዱ እየተፈተኑ ናቸው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ሥፍራዎች የዘረጋቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ለአገር ልማትና ዕድገት ያላቸው ፋይዳ አሌ ባይባልም፣ ነገር ግን ያን ያህል አንገብጋቢነት የሌላቸው ፕሮጀክቶች ደግሞ የአገር ሀብት እየፈሰሰባቸው ሕዝብ መራብ የለበትም፡፡ አሁን ካለው የመሠረታዊ ምግቦች ዋጋ ንረት አኳያ ማናቸውም ፕሮጀክቶች ከሕዝብ ህልውና ሊቀድሙም አይገባም፡፡ የምግብ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋቸው አልቀመስ ብሎ ብዙኃኑ ሕዝብ ሲቸገር፣ በጣም አንገብጋቢ ካልሆኑ ፕሮጀክቶች በስተቀር ቅድሚያ ለምግብ መሰጠት አለበት፡፡ ሕዝብ የሚበላው አጥቶ ሰላም ሊኖር ስለማይችል መንግሥት ለምግብ አቅርቦትና ሥርጭት ትልቅ ትኩረት ይስጥ፡፡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያቀረበው ምክረ ሐሳብም በአንክሮ ተደምጦ ፈጣን ውሳኔ ላይ ይደረስ፡፡

የምግብ ዋጋ ንረት ብሔራዊ ሥጋት መቀደቀኑ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ሲቀርብ፣ በኃላፊነት ስሜት ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ የመንግሥት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ አቅርቦትና ፍላጎት መሀል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ በመሆኑ፣ መንግሥት በአገር ውስጥ ከተመረቱ የምግብ ምርቶች በተጨማሪ ከውጭ ገዝቶም ቢሆን ጉድለቱን መሸፈን ይጠበቅበታል፡፡ የስንዴ ምርት ከማሳ ተነስቶ ለሸማቾችም ሆነ ለዱቄት ፋብሪካዎች በአግባቡ መቅረብ ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገው ጥድፊያ መገታት አለበት፡፡ ምክንያቱም አሁን ምግብ ትልቁ የሥጋት አጀንዳ ስለሆነ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኖት ሕይወቱ ሲኦል እየሆነበት ባለበት በዚህ አስከፊ ጊዜ፣ ከመንግሥት በላይ ማንም አጣዳፊ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚችል ኃይል የለም፡፡ በቀን አንዴ ምግብ ለማግኘት ሚሊዮኖች በሚጨነቁባት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ አለመቻል፣ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤ ይኑር፡፡ በአገር ደረጃ ከዚህ በላይ አጣዳፊ ጉዳይ እንደሌለ ይታመን፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ መቼም ቢሆን ውድ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ 40 ብር ይሸጥ ነበር የሚባልበት ጊዜም ቢሆን፣ አቤት ደጉ ዘመን እየተባለ ከበሮ የሚያስደልቅ ታሪክ የለውም፡፡ በወቅቱ የ40 ብር ደመወዝተኛ ወይም የወር ገቢ የሚያመነጭ ሥራ ያላቸው በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ የተቀረው ሕዝብ ግን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ነበር የሚገፋው፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ በቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን የሚያመርተው አርሶ አደርም ቢሆን፣ በዓመት ውስጥ የረባ ምግብ የሚያገኘው ግፋ ቢል ለሁለት ወራት ብቻ ነበር፡፡ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ሁሌም ጭንቅና መከራ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በየአሥር ዓመቱ ሳይዛነፍ ከተፍ የሚለው ድርቅና ረሃብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ደጋግሞ ስሟን አስጠርቷታል፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት መገርሰስ ምክንያት ከሆኑት አንደኛው የ1965 ዓ.ም. ረሃብ ነበር፡፡ በ1977 ዓ.ም. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አርግፏል የሚባለው ዘግናኝ ረሃብ ጦሱ አይረሳም፡፡ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አጀንዳ ከመሆን ዘሎ የማያውቀው የምግብ ችግር፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ባለማግኘቱ አሁንም ትልቅ ሥጋት ደቅኗል፡፡

ከዕለት ጉርስ በተጨማሪም አልባሳት፣ መጫሚያዎች፣ የቤት ኪራይ፣ የትምህርት ቤት፣ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋቸው አልቀመስ እያለ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ዕቅድ መፍትሔ ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ግን በጥልቀትና በስፋት መጠናት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች ከፍተኛ መጠን ያለው ለም መሬት፣ ክረምት ከበጋ የሚፈስ ትልቅ የውኃ ፀጋ፣ በአፍሪካ አንደኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ ማዕድናት፣ በርካታ የቱሪስት መስህቦችና ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ የሰው ኃይል ያላት አገር ምግብ ብሔራዊ ሥጋት ደቀነባት ሲባል መደንገጥ ይገባል፡፡ ለዘመናት እነዚህን የተፈጥሮ በረከቶች መጠቀም አቅቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ለምን የረሃብ ተምሳሌት ሆነች የሚለው፣ ከምንም ነገር በላይ የአገራዊ ምክክሩ መነጋገሪያ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ በፊት ግን ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኝ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...