የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች ኢንቨስትምንትን ጨምሮ ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቀደ፡፡
ሪፖርተር የተመለከተውና በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው አዲስ መመሪያ ‹‹ለልማት ፕሮጀክቶች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ለመወሰን የወጣ መመሪያ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም የደረቅ፣ የፍሳሽ ወይም ማቀዝቀዣ የተገጠመለት የጭነት መኪናን ወይም ለተለየ አገልግሎት ተብለው የሚዘጋጁ አውቶብስን፣ ሚኒባስን፣ ሚዲባስን፣ ሽፍን የዕቃ ማጓጓዣ ተሽከርካሪንና የሞተር ብስክሌቶችን ይጨምራል፡፡
መመሪያው የማበረታቻው ተጠቃሚ የኢንቨስትመንት መስኮች ብሎ ከለያቸው ውስጥ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭነት፣ ባለ ኮከብ ሆቴሎች (የሪዞርት ሆቴሎችን ጨምሮ)፣ በባቡር መሠረተ ልማት፣ ሞቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ሎጆች የተሰማሩ ባላሀብቶች ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ልማት፣ በአስጎብኝ ሥራና በኤክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማሠራጫ፣ በትምህርትና ሥልጠና፣ የጤና አገልግሎት የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሽርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚፈቀድ ሲሆን፣ የአርክቴክቸርና ኢንጂነሪንግ ሥራዎች የቴክኒክ ምርመራና ትንተና አገልግሎትና ንግድ የሥራ መስኮች አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የሚያቋቋሙ ወይም ነባር ደርጅታቸውን የሚያስፋፉ ባለሀብቶችም የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
የማምረቻ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች በሚባሉት የምግብ፣ የመጠጥ፣ የጨርቃ ጨርቅና የስፌት ውጤቶች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የእንጨት ውጤቶች፣ የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች፣ የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶችን ጨምሮ በመመሪያው በሰንጠረዥ አንድ በተዘረዘሩት ኢንዱስትሪዎች የሚሠራ ማንኛውም ባለሀብት ተሽርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የሚፈቀደው መሬት ስለማግኘቱ (የፋብሪካ ሕንፃ ወይም የመሥሪያ ቦታ ተከራይቶም ከሆነ ሕጋዊ የኪራይ ውል) ማስረጃ ሲያቀርብ እንደሆነ በመመሪያው ተገልጿል፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ የመሠረታዊ መድኃኒት ምርት፣ የፕላስቲክ ውጤቶች፣ ብረት ያልሆኑ የማዕድን ውጤቶች፣ የመሠረታዊ ብረታ ብረት (የማዕድን ማውጣትን ሳይጨምር)፣ ለስትራክቸር የሚያገለግሉ የብረታ ብረት ውጤቶች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች የትራንስፖርት መሣሪያዎች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርክ ማልማትና የማከራየት ሥራዎች ተብለው በተዘረዘሩት የኢንቨስትመንት የሥራ መስኮች የማበረታቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት፣ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ (የመሬት ዝግጅት፣ መሠረተ ልማት፣ መጋዘን፣ መንገድና የመሳሰሉት ሥራዎች) እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ከኢንቨስትመንት መሥሪያ ቤት ማስረጃ ሲቀርብ መሆኑን መመሪያው ያሳያል፡፡
ማንኛውም ባለሀብት ተሽከርካሪዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ለማስገባት የሚፈቀድለት የኢንቨስትመንት ትግበራውን አጠናቅቆ የሙከራ ምርት ማምረት ስለመጀመሩ አግባብ ካለው አካል የተሰጠውን ማስረጃ የጉምሩክ ቀረጥ ነፃ መብቱን ለሚፈቅደው አካል ሲያቀርብ ብቻ ይሆናል ተብሏል፡፡
በግብርና ልማት ኢንቨስትመንት የሚሰማራ ማንኛውም ባለሀብት ከቀረጥ ነፃ የሚያስገባው ተሽከርካሪ ዓይነትና ብዛት የሚወሰነው በሚያለማው የመሬት ስፋት፣ በሚኖረው የእንስሳት ብዛት፣ የቀፎ ብዛት እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ባዋለው የመሬት ስፋት መሠረት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
የኮከብ ደረጃ ባለው ሆቴል፣ ሞቴል፣ ሬስቶራንት ወይም የሎጅ አገልግሎት የተሰማራና የኢንቨስትመንት ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ባለሀብት የቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያወጣውን የደረጃ መሥፈርት ማሟላቱ ሲረጋገጥና ማስረጃ ሲያቀርብ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ ሆኖ ማስገባት ይችላል፡፡
መመሪያው በልዩ ድንጋጌው ተሽከርካሪ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የሚፈቀድለት ተጠቃሚ ከአገር ውስጥ የተሽርካሪ መገጣጠሚያ (ማምረቻ) ፋብሪካ ተሽከርካሪ ሲገዛ ተሽከርካሪውን ለማምረት ከውጭ ተገዝተው በገቡና ከአገር ውስጥ በተገዙ የተሽርካሪው ግብዓቶች ላይ የተከፈለው ቀረጥ ተሰልቶ ተመላሽ እንደሚሆን ያትታል፡፡
በገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተፈርሞ ተፈጻሚ እንዲሆን የተመራው መመሪያ እንደሚያሳየው ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የተፈቀደለት ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከተደረገበት ዓላማ ውጭ ሲጠቀምበት ከተገኘ በተሽከርካሪው ላይ ሊከፈል የሚገባውን ታክስ ከመክፈሉ ባሻገር አስፈላጊው የጉምሩክ ሕግ ዕርምጃ ተፈጻሚ ይሆንበታል ተብሏል፡፡