በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያን ጨምሮ ሌሎች መመርያዎችን እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ለማስጀመር የሚያስችሉ በርካታ መመርያዎችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ ያስታወቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ በዝግጅት ላይ ካሉት መመርያዎች መካከል የኢንቨስትመንት ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ መመርያ፣ እንዲሁም ደላሎች (Brokers)፣ ነጋዴዎች፣ ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎችና የኢንቨስትመንት አማካሪዎች የሥራ ፈቃድ መስጠትን የሚመለከቱት ተጠቃሾች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ በፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው “Invest Origins 2023” የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በኢትዮጵያ ዕውን ሊሆን ዝግጅት እየተረደገበት በሚገኘው የካፒታል ገበያ ምንነት ዙሪያ፣ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችና የዘርፉ ተዋንያን ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ለዜጎች በባንኮች ተቀማጭ ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ዋጋው እየቀነሰ የሚመጣን ሀብት ውጤታማ ወደ ሆኑ ዘርፎች ገብቶ ለባለቤቱ ጥቅም የማስገኘት አማራጭን እንደሚሰጥ የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ለመንግሥትና ለተቋማት ደግሞ ሀብት እንዲገላበጥና እንዲንቀሳቀስ በዚህም የተሻለ ውጤት እንዲገኝ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በደላሎች፣ በነጋዴዎችና በኢንቨስትመንት አማካሪዎች የሚደረጉ የሥራ እንቅስቃሴዎች ያልተያያዙና በተበታተነ መንገድ የሚከወኑ መሆናቸውን የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር)፣ በዚህም ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸው ደላሎችና የሕግ ሰውነት የሌላቸው ነጋዴዎች ከፍተኛ የባንክ አክሲዮኖችን ቴሌግራምና ዋትስአፕን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ትስስር አማራጮች እንደሚያገበያዩ (እንደሚያሻሽጡ) ተናግረው፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ይህንን መስመር ለማስያዝ ተገቢውን የሥራ ፈቃድ የሚሰጥበት አሠራር እንደሚፈጠር አስታውቀዋል፡፡
‹‹ተገቢውን ፈቃድ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤›› ያሉት ብሩክ (ዶ/ር) የንግድ ድርጅቶች፣ ደላሎች፣ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ባንኮች እንዲቋቋሙ የሚረዱ ድጋፎችን መስጠትን ጨምሮ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አዋጅ ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የአዋጁ መውጣት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ከተጠቀሱት ውስጥ ካፒታል በመሰብሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዲስ ፈጠራዎች በመደገፍና የኢንቨስትመንት ሥጋቶችን የመጋራት አሠራርን በማስፋፋት፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ የሚል ይገኝበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ለሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሚያገለግሉ ስድስት የቦርድ አባላትን መሾማቸውና የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል፡፡
በካፒታል ገበያ ላይ ትኩረት አድርገው በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ እንደሚገለጸው፣ የካፒታል ገበያ በቀጥታ ሳይሆን የተለያዩ ጥናቶችና የሕግ ማዕቀፎች ታይተው የሚገባበት ነው፡፡
አንድ ባለሀብት በካፒታል ገበያ አንድን ድርጅት ወይም የድርጅት ድርሻን ከመግዛቱ በፊት የፋይናንስ አቅም የሚያሳይ መረጃ ስለሚያስፈልገው፣ መረጃውን የሚመረምሩለት የተጠናከሩ የሒሳብ አዋቂ ድርጅቶች ያስፈልጉታል፡፡
የካፒታል ገበያ በሰነድ ግብይት ላይ የተመረኮዘ እንደ መሆኑ መጠን፣ ያለ ሕግ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ዕገዛ የቱንም ያህል ዕርምጃ መሄድ እንደማይቻል ይገለጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶች የተሳሳተ መረጃ ይዘው ወደ ካፒታል ገበያ እንዳይገቡ የጥናትና ማማከር ድርጅቶች ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወቱ፣ የካፒታል ገበያ መቋቋም ተቋማትን የማስፋፋትም ሆነ የማነቃቃት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው “Invest Origins 2023” የኢንቨስትመንት ፎረም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታዎችን በተመለከተ፣ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ውይይት አድርገዋል፡፡