በአበበ ፍቅር
በተለያዩ ምክንያቶች ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤት ያላስመዘገቡና የተሻለ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች መካከል 100 ሺሕ የሚሆኑት ተማሪዎች በደከሙባቸው ትምህርቶች ልዩ ክትትል ተደርጎ እንዲማሩ ከተደረገ በኋላ እንዲፈተኑ በማድረግ ሁለተኛ ዙር ዕድል እንደሚሰጣቸው ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይኼንን ያስተወቀው በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የፈተና ውጤታቸውን በተመለከተ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ማብራሪያ ነው፡፡
በዚህም ፈተናውን ከወሰዱ 896,520 ተማሪዎች መካከል 29,909 ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚገቡ ይሆናል ሲሉ የትምህርት ሚኒስተሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በማጠናከሪያ ፕሮግራም እንደ ዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበለ አቅም፣ የተማሪዎችን ውጤት መሠረት አድርጎ በሚፈጸም የምልመላ መስፈርት፣ ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው በልዩ ሁኔታ በደከሙባቸው የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ድጋፍ ተደርጎላቸው ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በፈተናው ወቅትም ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው ለሴቶችና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ላሉ ተማሪዎች የመግቢያ ነጥብ ላይ ዕገዛ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡
የፈተና አሰጣጡ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ የሁሉም አካላት ርብርብ የታየበት እንደነበርና በስኬት እንደተጠናቀቀ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡
በፈተናው ወቅት ምንም ዓይነት ሥርቆት ሳይደረግበት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ አሁን ላይ ይፋ የተደረገው ውጤትም በፈተና ወቅት ደንብ በመጣስ የተባበሩ ተማሪዎችን አያካትትም ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ለፈተናው 985,384 ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የተፈተኑና ውጤታቸው የተያዘላቸው ተማሪዎች ቁጥር 896,520 መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በፈተናው ተመዝግበው ያልተገኙ 7,798 ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 20,170ዎቹ ደግሞ በፈተናው ተገኝተው በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉና ፈተናውን በፈቃዳቸው ትተው የሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የተገኘው አማካይ ውጤት 29.5 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ ‹‹የፈተናውን ውጤት ስንሰማ በጣም ደንግጠናል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ውጤቱም ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫና ተሸፍኖ የነበረውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ተጠያቂው ከመንግሥት ጀምሮ ራሳቸው ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆችን አድርገዋል፡፡ ችግሩ እንደ አገር ሁላችንንም የሚያሳፍ ቢሆንም ለቀጣይ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ተቀብለን የመጣብንን ችግር መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡