- ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል?
- እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ገጥሞህ ነው?
- ስምምነቱን ጥሰውታል ክቡር ሚኒስትር?
- ኧረ ተውው ተረጋጋ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር ይቅርታ… ደንቆኝ እኮ ነው።
- ስምምነቱን እንደጣሱ በምን ተረዳህ?
- ክቡር ሚኒስትር የፌዴራል መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠርት ተስማምተው ሳሱ እነሱ ግን ከዚህ የሚቃረን ተግባር ሰሞኑን ፈጽመዋል።
- ምን አደረጉ?
- እንደኛ አዲስ የካቢኔ አደረጃጀት ላይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
- ሁለተኛውስ?
- በስምምነቱ መሠረት የክልሉ ምክር ቤት መበተን ሲኖርበት ሌላ ነገር ተወስኖል።
- ምን ተወሰነ?
- የክልሉ ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ለክልሉ ሥራ አስፈጻሚ አሳልፎ ሰጥቷል።
- አየህ ተረጋጋ ያልኩህ ለዚህ ነበር።
- ለምን? እንዴት?
- የክልሉ ምክር ቤት አዲስ የሥራ አስፈጸሚ መዋቅር ላይ ከወሰነ በኋላ ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ለሥራ አስፈጸሚው አሳልፎ ሰጠ ማለት ትርጉሙ ሌላ ነው።
- አዲስ የሥራ አስፈጻሚ መዋቅር ላይ ሲወሰን የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ተቀበለ ማለት ነው።
- እህ… እሺ እሱ እንደዛ ይሁን ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ለምን አሳልፎ ሰጠ?
- ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ለሥራ አስፈጻሚው አሳልፎ ሰጠ ማለት ደግሞ ምን መሰለህ?
- ምን ማለት ነው?
- የክልሉ ምክር ቤት ፈረሰ ማለት ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደኅንነት ጉዳዮች አማካሪያቸው ጋር ስለ ወቅታዊ ጉዳች እየተወያዩ ነው]
- በድርጅት ደረጃ የተወሰነው ጉዳይ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ ነው?
- የትኛውን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በቅርቡ ስለ ፖለቲካ ማርኬት ፕሌስ ተወያይተን ውሳኔ ማሳለፋችንን ዘነጋኸው? ወይስ አንተም…
- እኔ ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ተጠልፈህ እንዳይሆን ብዬ ነው።
- ማን ይጠልፈኛል ብለው ነው?
- የፖለቲካ ነጋዴዎቹ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እየቀለዱ መሆን አለበት?
- ግራ ሲገባኝ እኮ ነው።
- ግራ የገባዎት ምንድነው?
- ማንን ማመን እንዳለብኝ።
- ክቡር ሚኒስትር በእኔ መሥጋት የለበዎትም። የውሳኔዎቹን የእስካሁን አፈጻጸም በተመለከተ ግን ማለት የምፈልገው ነገር አለ።
- ምንድነው ቀጥል።
- ክቡር ሚኒስትር በድርጅትም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ለይተን ያወጣነው የፖለቲካ ንግድ መንሰራፋት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የብሔራዊ ደኅንነታችን ዋና ፈተና መሆኑን አረጋግጠናል።
- እንዴት?
- እነዚህን የፖለቲካ ንግድ ተዋናዮች ከመዋቅራችን ቆርጦ የማውጣት መጠነኛ እንቅስቃሴ ብዙ ነገር እያሳየን ነው።
- ምን አስተዋላችሁ?
- ዋናው ነገር ይህ ችግር የብሔራዊ ደኅንነታችን ፈተና መሆኑን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተዋናዮቹ ላይ መውሰድ የጀመርነው ዕርምጃ አደገኛ ምልክቶችን እያሳየን ነው።
- አደገኛ ማለት?
- ክቡር ሚኒስትር አንዱ ቦታ ዕርምጃ ለመውሰድ ስንሞክር የተፈጠረው ኔትወርክ በሌላ ቦታ ግጭት እየቀሰቀሰ አገሪቱን የማፈረስ አደጋ እየደቀነ ነው።
- እስኪ ሁኔታውን በዝርዝር አስረዳኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ለምሳሌ ሰሞኑን ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሞከረውን መውሰድ እንችላለን። ይህ ጉዳይ በቀጥታ የእነዚሁ የፖለቲካ ንግድ ተዋናዮች ኔትወርክ መሆኑን ደርሰንበታል።
- እህ…
- ዕርምጃው የክልል አመራሮችንም እንደሚያካትት የገመቱ ደግሞ አቅማቸውን ለማሳየት እየሞከሩ ነው።
- እንዴት?
- ዕርምጃው ገና ወደ ክልል መዋቅሮች ሳይደርስ በአጣዬ ግጭት በመቀስቀስ ቢነኩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እያሳዩን ነው።
- ምን ሊፈጠር ይችላል?
- የእነሱ ሥሌት የብሔር ግጭት መፍጠር ነው።
- እህ….
- በአዲስ አበባ አስተዳደር በመሬት ሥርቆት የጠረጠርናቸው ደግሞ መረጃ የማውደም ተግባር ፈጽመዋል።
- ምን አደረጉ?
- ግንባታው ተጠናቆ ሊመረቅ ቀጠሮ የተያዘለት የክፍለ ከተማው የመረጃ ማዕከልን በእሳት አጋይተውታል።
- ዘግይተናል ማለት ነው?
- ምን አሉኝ?
- በዚህ ደረጃና ጥልቀት እስኪንሰራፉ አለመንቃታችን ያናዳድል።
- አሁን እሱ አይጠቅምም ክቡር ሚኒስትር።
- ምኑ?
- መናደድ።
- እና ምንድነው የሚጠቅመው?
- መፍትሔውን ማለም!