በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት ወደ ትግራይ ክልል የተጀመረውን የአየር ትራንስፖርት በየብስም ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከአገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ማኅበራት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ወደ ትግራይ የተለያዩ ከተሞች የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎትን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ መመርያ ተላልፎላቸዋል፡፡
በዚሁ የሚኒስቴሩ መመርያ መሠረት ማኅበራቱ ለአባሎቻቸው አገልግሎቱን መልሶ ለማስቀጠል ዝግጁ እንዲሆኑ ያሳወቁ ሲሆን፣ አሁን እየጠበቁ ያሉትም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከፍቅር አንደኛ ደረጃ አገር አቋራጭ የግል አውቶብስ ባለንብረቶች ማኅበር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ መቀሌን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች ዳግም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎቱ የሚጀመር ስለመሆኑ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ የማኅበሩ አባላት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ነው፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱን መልሶ ለመጀመር የሚጠብቁት የመንግሥትን የመጨረሻ ትዕዛዝ ብቻ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በጦርነቱ ምክንያት ወደ ክልሉ የሚደረጉ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች እንቅስቃሴ ከመቋረጡ በፊት ይህ መስመር በርካታ መንገደኞችን ያስተናግድ እንደነበርም ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ አሁን ድጋሚ አገልግሎቱን ለመጀመር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የትንስፖርት ዘርፉንም በማንቀሳቀስ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሏል፡፡ ግዳጅ ላይ የነበሩ አውቶብሶች አሁን ላይ ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው የሚመለሱ በመሆኑ፣ ወደ ሰሜን ለሚደረጉ ጉዞዎች በቂ ትራንስፖርት ለማቅረብ እንደሚቻል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከመቀሌ ሌላ ከአዲስ አበባ ሽሬ፣ ማይጨውና የመሳሰሉ ከተሞች አውቶቡሶች የደርሶ መልስ አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ ሲሆን፣ አሁንም ማኅበራቱ ወደ እነዚህ ከተሞች አገልግሎት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መልሶ መጀመር በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ያልቻሉ መንገደኞች አማራጭ ኖሯቸው እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው ሲሆን፣ በርካታ ተገልጋዮችም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመርን አጥብቀው እየጠየቁ እንደሆነ ከእነዚሁ ማኅበራት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ በተለይም በአየር ትራንስፖርት መጓዝ ያልቻሉ ተገልጋዮች የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመርን በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነ ማኅበራቱ ይገልጻሉ።
ከዓለም ሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ያገኘነውም መረጃ የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ወደ ትግራይና ወደ ተለያዩ ከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመጀመር ዝግጁ እንዲሆኑ ማዘዙንና በተባለው መሠረትም ማኅበሩ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ነው፡፡
ነገር ግን አገልግሎቱን ከመጀመራቸው በፊት የትራንስፖርት ማኅበራቱ ሊሟሉ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ዳግም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለመጀመር ሊሟላ ይገባል ካሏቸው መካከል ስለፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝነት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው የሚጠይቀው በቀዳሚነት ይገኝበታል፡፡ በመስመሩ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ካልሆነ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚከብድ በመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም ሌላ መንገድ ላይ መስተጓጎል እንዳይገጥም በጉዞው መስመር ላይ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች አገልግሎት መስጠት አለመሰጠታቸውንም ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እንዲያረጋግጥላቸው ይፈልጋሉ፡፡
በተለይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶቹ በሚደርሱባቸው የክልሉ ከተሞች ውስጥ ያለው ዝግጅት አገልግሎቱን ለመጀመር ወሳኝ በመሆኑ የተሟላ ዝግጅት መኖሩ ካልተረጋገጠ አገልግሎቱን ለመጀመር እንደሚቸገሩ የተለያዩ የሕዝብ ማመላሻ ትራንስፖርት ማኅበራት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩም በቀረበው ጥያቄ መሠረት ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ሥራ የሚጀምሩበትን ጊዜ እንደሚያስታውቃቸው በመግለጹ፣ ማኅበራቱ ይህንኑ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለመጀመር ማኅበራቱ እንዲዘጋጁ ካሳወቀ በኋላ፣ ሊዘገይ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት የፀጥታው ሁኔታ እስኪያስተካክልና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።
ከመቀሌ ሌላ ማኅበራቱ ወደ ሽሬ፣ አክሱም፣ አዲግራትና ማይጨው ከተሞች አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከጦርነቱ በፊት በቀን ከሦስት እስከ አምስት የሚሆኑ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ወደ መቀሌ ይጓዙ እንደነበር፣ ወደ ሌሎቹ የትግራይ ከተሞች ደግሞ በቀን አንዳንድ አውቶቡሶች ይጓዙ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበራት ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች ከሚጀምሩት የትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር፣ ልዩ አውቶቡሶችና ሚኒባሶችም በተጨማሪነት እንዲሰማሩ ሊደረግ እንደሚችል ተጠቁሟል።
በሰሜኑ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የበርካታ መደበኛ ከተሞች የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሎ የቆየ ሲሆን፣ የአንዳንድ ከተሞች አገልግሎት መልሶ እየተጀመረ ነው፡፡ በቅርቡም ከአዲስ አበባ ዓላማጣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ካደረገ በኋላ የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ወደ መቀሌ የመጀመርያውን በረራ ያደረገው ታኅሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡
በወቅቱ በቀን አንድ በረራ በማድረግ የተጀመረው የመቀሌ የአየር ትራንስፖርት አሁን ወደ ሦስት ያደገ ሲሆን፣ ከመቀሌ ሌላ ወደ ሽሬ ከተማ ከታኅሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የበረራ አገልግሎት ጀምሯል። ከሁለቱ የክልሉ ከተሞች በተጨማሪ በአክሱም ከተማ የአየር ማረፊያ ቢኖርም በጦርነቱ ምንክንያት በአየር ማረፊያው መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሰ ጉዳት በረራዎችን ማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም። የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን ወደ አገልግሎት ለማስገባት ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ መገንባት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አክሱም ከተማ በረራ ለመጀመር እንደሚቸገር ያገኘነው መረጃ ያመልከታል።
ሆኖም ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት በአየር ትራንስፖርቱ ላይ እየፈጠረ ያለውን መጨናነቅ በተወሰነ ደረጃ ያቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡