በኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ታሪክ ረዥም ዘመናትን ማስቆጠሩ የሚነገርለት መከላከያ ሠራዊት፣ በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተናዎች በጠንካራ ፅናት በማለፍ የኢትዮጵያን ህልውና አስጠብቆ ለዛሬ ማሸጋገር የቻለ ኃይል መሆኑ ጎልቶ ይነገርለታል፡፡
‹ኢትዮጵያ የአርበኞች አገር ናት› የሚለው የብዙ ታሪክ ጸሐፍት ድምዳሜ፣ ለዘመናት ኢትዮጵያውያን በተግባር ተፈትሸውበት የተረጋገጠ ብዙዎችን ያግባባ ሀቅ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ ማኅበረሰብ የወጣው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትም ቢሆን ከባድ መስዕዋትነት በጠየቁ ግዳጆች ውስጥ አልፎ ዛሬ ለሚገኝበት ጠንካራ ማንነትና ብቃት እንደበቃ ይነገራል፡፡
ወጥ የሆነና መደበኛ ቀለብ እየተሰፈረለት ወይም ደመወዝ እየተከፈለው ለግዳጅ የሚሰማራ ሠራዊት በኢትዮጵያ የተቋቋመው ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በ1901 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) የጦር ሚኒስትር በማድረግ የሠራዊት ግንባታውን ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ይህ ተቋማዊ ሠራዊት ዘመናዊና ዘርፈ ብዙ አደረጃጀት እንደተፈጠረለት ይነገራል፡፡ ምድር ኃይል፣ አየር ኃይልና ባህር ኃይል የሚሉ አደረጃጀቶች የመጡት በዚህ ዘመን ነበር፡፡
በሌላም በኩል የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት፣ የሐረር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አካዴሚ፣ የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይል፣ የምድር ጦር ማመላለሻ ትምህርት ቤት፣ የቀላል ተሽከርካሪ የጥገና ትምህርት ቤት፣ የምድር ጦር አስተዳደር ድርጅት፣ የሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ተግባረ ዕድ፣ የመገናኛና የመሐንዲስ ትምህርት ቤቶችንና የመሳሰሉ ሠራዊቱን የበለጠ የሚያጠናክሩ ተቋማት መስፋፋት የጀመሩት ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥትም ቢሆን ይህ ጠንካራ ሠራዊት የመገንባት ሒደት ተጠናክሮ መካሄዱ ይነገራል፡፡ በ1972 ዓ.ም. አዲስ የጦር ኃይሎች የዕዝ ተዋረድና ወታደራዊ ዶክትሪን ደርግ ማውጣቱ፣ ይህን የዕዝ ሥርዓትና ዶክትሪን ደግሞ እስከ መጨረሻው ሲተገብር እንደዘለቀ ይነገራል፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲተካ የኢሕአዴግ ሠራዊት መከላከያ በአዋጅ እስኪቋቋም ድረስ የሽግግር ጊዜ ሠራዊት ሆኖ አገልግሏል፡፡
በ1987 ዓ.ም. ሥራ ላይ በዋለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 87 መሠረት መከላከያ ሠራዊት አሁን ያለውን ተቋማዊ ማንነት ይዞ ተመሠረተ፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦን ያካተተና በሲቪል ሚኒስትር የሚመራ ሆኖ ተዋቀረ፡፡
ሠራዊቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ግዳጆች የሚወጣ መሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ ተመልክቷል፡፡ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መንገድ እንደሚዋቀርም ተደንግጓል፡፡ ታማኝነቱ ለሕገ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ነው ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በጉልህ ያስቀመጠው፡፡
ሕገ መንግሥታዊው የሠራዊት ግንባታ መርህ ይህን ቢልም፣ ኢሕአዴግ አገሪቱን ባስተዳደረባቸው 27 ዓመታት የዘለቀው ተጨባጭ የመከላከያ አደረጃጀት እነዚህን መርሆዎች በሚያሟላ መንገድ አለመሆኑ በስፋት ይወሳ ነበር፡፡
በአዋጅ ቁጥር 27/1988 መሠረት የተቋቋመው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካም ሆነ ከቡድን ወገንተኝነት ባልተላቀቀ መንገድ ሲመራ እንደነበር፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ከፍተኛ የሠራዊቱና የመንግሥት ባለሥልጣናት በአደባባይ ሲናገሩ ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡
በተለይ በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት ኃይሎች ከባድ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ፣ ከመከላከያ ተቋም አገነባብ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠንካራ አስተያየት የሰጡበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ከመስመር መኮንኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮችና የጦር ጄኔራሎች ድረስ የአገር መከላከያ ሠራዊት በሕወሓት ሰዎች ተሞልቶ እንደነበር፣ ዓብይ (ዶ/ር) ፓርላማው ፊት ቀርበው በሰፊው መተቸታቸው የቅርብ ታሪክ ነው፡፡
የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ለተከበረው ሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በዓል በታተመው ‹‹ሠራዊታችን›› ለተባለው ልዩ የመጽሔት ዕትም፣ የወቅቱ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡
‹‹ከሕዝብ አብራክ የወጣው መከላከያችን ባለፉት 27 ዓመታት የሰላም፣ የደኅንነት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የትግራይ ሕዝብና መንግሥት መከላከያ አለኝታችን መሆኑን ጥርጥር የለንም፤›› በማለት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በመጽሔቱ ላይ መልዕክታቸውን አስፍረው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ሙገሳ የሰጡትን ተቋም እሳቸው የሚመሩት ሕወሓት እንዴት ሊወጋ እንደበቃ ከመገመት በቀር የተብራራ መልስ አልተገኘም፡፡
የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በመከላከያ ተቋም ሪፎርም ላይ ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወኑ ይናገራል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንባታ አዲስ ስትራቴጂካዊ ሰነድ ማዘጋጀቱንም መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ በታኅሳስ 2011 ዓ.ም. የአዋጅ ማሻሻያ በማድረግ መከላከያ የባህር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ ኃይል፣ የስፔስና የሳይበር ኃይሎችነ ባካተተ አደረጃጀት እንዲዋቀር መንግሥት የሪፎርም ሥራ ማከናወኑን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ አዲሱ መከላከያ የሚመራበት ስትራቴጂካዊ ሰነድም ይህን የተከተለ እንዲሆን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡
በየካቲት 2012 ዓ.ም. የታተመው አዲሱ ስትራቴጂካዊ ሰነድም፣ ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ወይም ‹‹ቀዩ መጽሐፍ› ተብሎ የሚታወቀውን የኢሕአዴግ ዘመን አወዛጋቢ የመከላከያ ሰነድ የሚተካ እንደሆነ ነው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ይፋ ያደረጉት፡፡ ‹‹ቀዩ መጽሐፍ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያሉት ነው፡፡ ጠንካሮቹን ይዘን ደካማዎቹን እያረምን ካልቀጠልን የምንፈልገውን ዓይነት በሙያ የተካነ ሠራዊት መገንባት አንችልም፤›› በማለት ነበር ዓብይ (ዶ/ር) ሰነዱን ይፋ ሲያደርጉ የተናገሩት፡፡
በቅርብ ዓመታት እጅግ ሰፊ የሪፎርም ሥራ ማካሄድ የቻለ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ስለመገንባቱ የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጡበት ተቋም ስለሆነ በሚመስል ሁኔታ፣ መከላከያ ሠራዊት በልዩ ሁኔታ የሚጠራና ዝናው ከፍ ብሎ የሚነገር ተቋም ባለፉት ዓመታት ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡
የሰሜን ዕዝ መጠቃትን የተከተለው ጦርነት መከላከያ ራሱን የበለጠ እንዲገነባና እንዲያጠናክር ተጨማሪ ምክንያት ሆኖታል ይባላል፡፡ ባለፉት ሁለት የጦርነት ዓመታት የአገር መከላከያ ሠራዊት ትልቅ ትኩረት እንዲያገኝ ዋና ምክንያትም ሆኗል፡፡ ዓመት ጠብቆ የካቲት ሰባት ሲመጣ የመከላከያ ቀንን ከማክበር ባለፈ፣ በየአጋጣሚው የመከላከያን ተቋማዊ ክብርና ዝና ከፍ የሚያደርጉ ሁነቶች በእነዚህ ዓመታት ተደጋግመው ታይተዋል፡፡ ለተቋሙና ለሠራዊት አባላት የሚሰጠው ድጋፍና አጋርነት ሲጨምርም ታይቷል፡፡ ለሠራዊት አባላት ነፃ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ ‹‹ለመከላከያ ክብር እቆማለሁ›› የሚሉ እንቅስቃሴዎች የዚህ ነፀብራቅ ናቸው ይባላል፡፡
ከሰሞኑ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት የተደረገው ታላቅ ወታደራዊ ትርዒት መከላከያ እየገነባ ያለውን አቅም ያሳየ ነው እየተባለ ነው፡፡ በአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን በጦር አቅም የገነባውን ተክለ ቁመና ሠራዊቱ በዚህ አጋጣሚ ለወዳጅም ለጠላትም አሳይቷል የሚል አስተያየት እየተሰጠም ነው፡፡
በአየር ኃይልና በሜካናይዝድ ጦር የታጀበው ይህ የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ትርዒት እጅግ የዘመኑ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ለዕይታ የበቁበት ነበር፡፡ ከቻይና መገዛታቸው የተነገረው በተሽከርካሪ ላይ የተገጠሙት ተተኳሽ ሮኬቶችና ሚሳይሎች ከፍተኛ ትኩረት ስበው ነበር፡፡ የውጊያ ልምድ ሁሌም አጥቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከሰሞኑ እንደታየው በዘመናዊ ትጥቆች ራሱን ማደርጀቱ ብዙዎች በሠራዊቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ከፍ ያደረገ ነበር፡፡
በዚህ ወታደራዊ ትርዒት ላይ የታደሙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን ስለመከላከያ ግንባታ አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር ለኢትዮጵያ ጋሻና መከታ የሆነ መከላከያ የመገንባት አስፈላጊነትን በትኩረት አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጠንካራ አገር አድርጎ ለመገንባት መንግሥት በዋናነት የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመገንባት ጎን ለጎን፣ የፀጥታ ተቋማትን ማጠናከር እንደ ዋና የትኩረት አቅጣጫ እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት ተቋማትን ማጠናከር ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል፡፡
መከላከያን በማጠናከርና በማዘመን ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ የሰው መስዕዋትነትን የቀነሰ ውጤታማ የውጊያ ታክቲክ መገንባት እንደሚጠቅማት ነው የጠቆሙት፡፡ ለዚህ ሲባልም፣ መከላከያው የአየር ኃይልንና የከባድ መሣሪያ ኃይልን ያቀናጀ ዘመናዊ ውጊያን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን እየተገነባ ያለውን አቅም መከላከያው ከዚህ ቀደም ገንብቶ እንደማያውቅ የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹መከላከያ የሰላምና የልማት ምንጭ እንዲሆን›› ሰፊ ሥራ ስለመሠራቱ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መከበር ባላት ቁርጠኝነት በብዙ የዓለም አገሮች የሰላም አስከባሪ ስትልክ ኖራለች፡፡ ለአብነትም ከ1943 ዓ.ም. የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጊያ ጀምሮ በ12 አገሮች ጦርነቶችና ግጭቶች ሠራዊቷን በሰላም ማስከበር እንዲሳተፉ በማድረግ፣ በጦር ሜዳ የተፈተነ ጀግና ሠራዊት እንደገነባች ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስክበር ተሳትፎ በአኃዝ (ምንጭ ሠራዊታችን ልዩ ዕትም መጽሔት የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.)
ተ.ቁ |
የተሰማራበት አገር |
የተሰማራበት ዓ.ም. |
የተሳተፈው የሰው ኃይል ብዛት |
ማብራሪያ |
1 |
ኮሪያ |
ከ1943 እስከ 1945 |
6,037 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
2 |
ኮንጎ |
ከ1952 እስከ 1955 |
10,425 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
3 |
ሩዋንዳ |
ከ1986 እስከ 1987 |
1,694 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
4 |
ብሩንዲ |
ከ1996 እስከ 2001 |
2,766 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
5 |
ላይቤሪያ |
ከ1996 እስከ 2009 |
12,538 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
6 |
ኮትዲቯር |
ከ1999 እስከ 2009 |
23 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
7 |
ቻድ |
ከ2001 እስከ 2002 |
15 |
የተጠናቀቀ ተልዕኮ |
8 |
ዳርፉር |
ከ2000 ጀምሮ |
21,928 |
ያልተጠናቀቀ ተልዕኮ |
9 |
አብዬ |
ከ2003 ጀምሮ |
28,244 |
ያልተጠናቀቀ ተልዕኮ |
10 |
ሶማሊያ |
ከ2006 ጀምሮ |
20,968 |
ያልተጠናቀቀ ተልዕኮ |
11 |
ደቡብ ሱዳን |
ከ2006 ጀምሮ |
6,006 |
ያልተጠናቀቀ ተልዕኮ |
12 |
ማሊ |
ከ2007 ጀምሮ |
3 |
ያልተጠናቀቀ ተልዕኮ |
ድምር |
110,647 |
ከሰሞኑ በአዋሽ አርባ ደማቅ ወታደራዊ ትርዒት ያሳየው መከላከያ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው የሰሜኑ ጦርነት በሚገባ ተፈትኖ ራሱን ያሳየ ሠራዊት ስለመሆኑ በርካቶች በኩራት እየተናገሩ ይገኛል፡፡ ይህ ጠንከራ የጦር አቅም የመገንባት እንቅስቃሴ ደግሞ ከግጭትና አለመረጋጋት ተላቆ ለማያውቀው የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የሰላም ቱሩፋት እንደሚኖው ይገመታል፡፡
ይህ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች የተፈተነና በተለያዩ አገሮች የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ልምድ የገነባ ያለ ተቋም፣ አሁን በጠንካራ ተቋማዊ ግንባታዎች ተደግፎ ራሱን ማሳደጉ ለቀጣናዊ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው እየተባለ ነው፡፡