አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማኔጅመንት አባላት ጋር ትውውቅ እንደሚያደርጉና በመጪው ሳምንት ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተጠቆመ፡፡
ከአራት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩትን ይናገር ደሴ (ዶ/ር)ን በተመካት ሥራ የሚጀምሩት አቶ ማሞ ምሕረቱ ዛሬ ይካሄዱታሎ ተብሎ ከሚጠበቀው የትውውቅ ፕሮግራም ባሻገር ከማኔጅመንቱ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንዳመለከቱት ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ አዲስ የተሾሙት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ከባንኩ ሠራተኞች ጋር ለመተዋወቅ ፕሮግራም ተይዞላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ አዲሱ ገዥ ብሔራዊ ባንክ ከሚቆጣጠራቸው ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ጋር በመጪው ሳምንት አጋማሽ ላይ ትውውቅና ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ማሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው በመሰየማቸው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚነታቸው በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልነታቸውም እንደሚለቁም ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ አባላት እያገለገሉ ካሉት አሥር የቦርድ አባላት ውስጥ አቶ ማሞ አንዱ ሲሆኑ፣ ከታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
አሁን ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሆነው በመሰየማቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልነታቸውን ይዘው መቀጠል እንደማይችሉ ተገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጥቅም ወይም የሥልጣን ግጭት የሚፈጥር በመሆኑ ነው ተብሏል። ይህም በመሆኑ በእሳቸው ምትክ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ የቦርድ አባል ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባላት ሆነው እያገለገሉ ያሉት አብረሃም በላይ (ዶ/ር)፣ አቶ አዲሱ ሀባ፣ አቶ አሕመድ ቱሳ፣ አቶ ጌታቸው ነገራ፣ ማሞ ምሕረቱ (አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ)፣ አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና ወ/ሪት ያስሚን ዎሀብረቢ ሰኢድ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ማሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው መሰየማቸውን ተከትሎ ከሁለት ወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተሰጥቶ የነበረውን የካፒታል ገበያ የቦርድ ሊቀመንበርነትንም ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የካፒታል የገበያው የቦርድ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እንደሚሆን የካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ የሚደነግግ በመሆኑ አዲሱ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ይህንን ኃላፊነት ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ማሞ ከለውጡ ወዲህ በተመደቡባቸው የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉበትን ጊዜ ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከሃያ ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ የማስተር ዲግሪያቸውን በሕዝብ አስተዳደር ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ሕግ ወስደዋል፡፡
አቶ ማሞ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ ሪፎርም አማካሪና የአገሪቱ ዋና የንግድ ተደራዳሪ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ ሪፎርም አማካሪ ሆነው ማገልገል ከመጀመራቸው ቀደም ብሎም የዓለም ባንክ ግሩፕ ከፍተኛ የፕሮጀክት ማናጀር በመሆን መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገዥነት ሲመሩ የቆዩት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እስካሁን በአዲስ ኃላፊነት ቦታ ላይ አልተመደቡም፡፡
ከብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው የተነሱት ይናገር (ዶ/ር) ቀጣይ ማረፊያቸው እስካሁን ባይታወቅም በበርካታ ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነትና ሊቀመንበርነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የቀድሞ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዴኤታ በመሆን ጭምር የሠሩት ይናገር (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም በቦርድ ሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡