በኢዮብ አሰለፈች ባልቻ
በዚህ አጭር ጽሑፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች በአገራዊው የምክክር ሒደት ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ የሚሳተፉበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚሠሩ አካላት (የወጣት ማኅበራትና ድርጅቶች ወይም ወጣቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩ ድርጅቶች)፣ አፅንኦት ሊሰጧቸው ይገባሉ የምለውን ሦስት ዓብይ ጉዳዮች አነሳለሁ።
እነዚህ ሦስት ዓብይ ጉዳዮች አንደኛ የኢትዮጵያን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎችን በጥልቀት መረዳት፣ ሁለተኛ ወጣቶችን ከዕድሜ ስብስብ ባሻገር ያላቸውን አንድነቶችና ልዩነቶች ማጤን፣ ሦስተኛ የአገራዊ ምክክር ሒደቱና ታሳቢ የሚደረገው ለውጥ የሚሄድበትን ውስብስብ ሒደቶች የሚመጥን ሁሌም ለመሻሻል ዝግጁ የሆኑ ሥልቶችን መንደፍ የሚሉ ናቸው። ለጽሑፉ አትኩሮት ሲባል ሰፋ ያለ መንደርደሪያና መግቢያ ከመስጠት ይልቅ፣ በቀጥታ ወደ ጉዳዮቹ እገባለሁ።
- 1. የኢትዮጵያን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎችን በጥልቀት መረዳት
ግለሰቦችም ሆኑ የተደራጁ አካላት ለውጥን ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረትና ስኬት በሰዎች ፍላጎትና አቅም ብቻ ሳይሆን፣ ዓላማቸውን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በሚጋፈጧቸው መዋቅሮችና ሥርዓቶች ተፅዕኖ ሥር ነው። መዋቅሮችና ሥርዓቶች አስቻይ ወይም ከልካይ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ ያላቸውን ሚና በተገቢው መንገድ መረዳት ተግዳሮቶችን ለመቋቋምና መልካም ዕድሎችን በበጎ ለመጠቀም ይረዳል።
መዋቅራዊ የምንላቸው ጉዳዮች ተፈጥሯዊና መልክዓ ምድራዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሐሳባዊ (ርዕዮተ ዓለማዊ) የሆኑ ማዕቀፎችን ያካትታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት አንፃር ያሉ የተለያዩ የመልክዓ ምድር አቀማመጦችና ተያይዘው ያሉ የሕዝብ አሠፋፈር፣ የመሬት ለምነት፣ የተፈጥሮ ሀብት (መኖርና አለመኖር)፣ መሀል አገር፣ የጠረፍ አካባቢዎች፣ ተራራማና ሜዳማ ሥፍራዎች፣ ወዘተ. በተፈጥሮ በይበልጥ የሚወሰኑ መዋቅራዊ ጉዳዮች ናቸው። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ጉዳዮች ደግሞ የአገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ የአንበሳ ድርሻ ያለው ግብርናና ሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ስብጥር (አምራችና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች)፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የኢኮኖሚ መደቦች መካከል ያለ የሥራ ክፍፍልና የምርት ሒደቶችን ያካትታል። የፖለቲካ መዋቅሮች የምንላቸው በአገራችን ያለውን የሥልጣንና የውሳኔ ሰጪነት የሚና ክፍፍል፣ የአገዛዝ ዓይነት (መርህዎች) የሚይዝ ሲሆን፣ ማኅበራዊ መዋቅሮች ደግሞ ማኅበራዊ መደብ፣ የዘውግ/ባህል/ቋንቋ ማንነት፣ የፆታና የዕድሜ ክፍፍሎችን ያካትታል። ሐሳባዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ የምንለው መዋቅር በኅብረተሰብ ውስጥ ገዥ የሆኑ አመለካከቶች፣ ዕሴቶችና ዕይታዎችን የሚይዝ ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል ያላቸው ቡድኖች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ነው።
ከላይ ያየናቸው የተለያዩ መዋቅራዊ ጉዳዮች የራሳቸው የሆነ ሥርዓቶችን በማበጀት፣ የሰዎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ተፈጥሯዊና መልክዓ ምድራዊ የሆኑ መዋቅሮች ሰዎች ስለሚከተሉት ሥልተ ምርት (ግብርና፣ አርብቶ አደርነት)፣ ስለሚያመርቷቸው የምርት ዓይነቶች፣ ከተለያዩ የምርት ግብዓቶች ወይም ሀብት ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ይቃኛሉ። ለምሳሌ የመሬት ባለቤትነት መብት ወይም የመሬት ሥሪት/ይዞታ ጉዳዮች በግብርና የሚተዳደሩ ሰዎች ባሉበት አካባቢ በጣም ወሳኝ ሥርዓት ሲሆን፣ በአርብቶ አደሮች አካባቢ ወሳኝ የሚባሉት ሥርዓታት የግጦሽ መሬትንና የውኃ አቅርቦት ያለባቸውን ቦታዎች የሚመለከት ይሆናል ማለት ነው።
የኢኮኖሚ መዋቅሮች የሚቃኙት ሥርዓት ደግሞ የንብረት ባላቤትነት ጉዳይ፣ የሠራተኛና አሠሪ ግንኙነት፣ የግብር አወሳሰን ሒደቶችን ይመለከታሉ። የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚቃኙት ሥርዓቶች አገረ መንግሥቱና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የተቋቋሙበትን ቀመር ያሳዩናል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ፌዴራላዊና ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን የሚከተል ሲሆን፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያሉት የሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አካላት ያላቸው የሥልጣን ክፍፍል፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ወይም በክልል መንግሥታትና በተዋረድ ባሉት የመንግሥት የአስተዳደር እርከን ያሉት የፖሊሲና የሕግ ማውጣት አቅምና ሥልጣን ክፍፍል የሚቃኙት በፖለቲካዊ ሥርዓቶች ነው።
የማኅበራዊ ሥርዓቶቻችን በበኩላቸው በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያሉ መብቶችን፣ ልዩ ተጠቃሚነትን ወይም መገለልን ያሳልጣሉ። ለምሳሌ ፆታን፣ ዕድሜንና ማኅበራዊ መደብን መሠረት ያደረጉ ክልከላዎችና ማበረታቻዎችን ማንሳት ይቻላል። ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚገድቡ መብቶች፣ ከተወሰነ የዕድሜ ክልል በታች ያሉ ሰዎች በፖለቲካ ሒደት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚገድቡ ሕጎች (መምረጥ፣ መመረጥ፣ የመንግሥት ኃላፊነት ሹመት፣ ወዘተ.) የመሳሰሉት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ሐሳባዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ ሥርዓቶች የሰዎችን የጋራ የሆኑ አስተሳሰቦች፣ እሴቶች፣ ወግ፣ ልማዶችና ያልተጻፉ ግን ብዙዎችን የሚቃኙ አመለካከቶችን ያካትታሉ። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የብሔርተኝነት አመለካከት፣ ለብሔር ማንነት የሚሰጠው ከፍ ያለ ሥፍራ፣ የመንግሥትንና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ያላቸውን ሚና በተለያየ ዕይታ የሚያዩ አመለካከቶች (ልማታዊ መንግሥትና የነፃ ገበያ/ኒዮሊበራል አተያዮች) ሐሳባዊ ሥርዓቶች ሲሆኑ፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች፣ የትምህርት ፖሊሲዎችና መገናኛ ብዙኃን ሐሳባዊ ወይም ርዕዮተ ዓለም ሥርዓቶች የሚኖራቸውን የጎላ ሚና ይወስናሉ።
ከላይ የተጠቀሱት መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ጉዳዮችን በስሱም ቢሆን ለመረዳት መሞከር፣ አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተጋፈጠችው ውስብስብ ችግር በጥልቀት ለማየት ያስችላል። ለምሳሌ በአገራዊው የምክክር ሒደት የኢትዮጵያ ወጣቶች ትርጉም ያለው ሚን እንዲኖራቸው የሚወጥን አካል፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ያሉባቸውን ተጨባጭ ተግዳሮቶች በአካባቢው ካሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሐሳባዊ መዋቅሮችና ሥርዓት አንፃር ሊመለከት ይገባል። በአንድ አካባቢ ያሉ እነዚህ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎች በአገራዊ፣ ከፍ ሲልም በክፍለ አኅጉራዊ ወይም ቀጣናዊ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ እንደሚችሉ መረዳትም ተገቢ ነው። በአፋር ወይም በሶማሌ ክልሎች ያሉ ወጣቶች መሀል አገር ካሉ የዕድሜ እኩያዎቻቸው ጋር የሚጋሩት አገራዊ መዋቅሮችና ሥርዓቶች ቢኖሩም፣ የአፍሪካ ቀንድን ማዕከል ያደረጉ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ደግሞ ከመሀል አገር ወጣቶች የበለጠ የአፋርና የሶማሌ ክልሎች ወጣቶችን የሕይወት አቅጣጫ ይወስናሉ።
- 2. ወጣቶችን ከዕድሜ ስብስብ ባሻገር ያላቸውን አንድነቶችና ልዩነቶች ማጤን
በ1996 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ወጣቶችን ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ያስቀምጣል። እ.ኤ.አ. በ2006 የፀደቀው የአፍሪካ የወጣቶች ቻርተር ደግሞ የአፍሪካ ወጣቶችን ከ15 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው ብሎ ይበይናል። ወጣቶችን የዕድሜ ስብስብ አድርጎ ማስቀመጥ ቁጥራቸውን ለይቶ ለማወቅና ተያይዘው የሚመጡ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማርቀቅና ለመፈጸም ጉልህ ሚና ይጫወታል። ነገር ግን ወጣትነትን ከዕድሜ ጋር ብቻ ማያያዝ ከፍተኛ የሆነ የአተያይ ውስንነትን የሚያመጣና አለፍ ሲልም ችግር የሚፈጥር አካሄድ ነው። ተፈጥሯዊ ዕድሜ ወጣትነትን ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ ቢሆንም፣ ዋነኛ ወይም ብቸኛ ምክንያት አይደለም። ወጣቶች በዕድሜያቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም፣ በብዙ ነገሮች ስለሚለያዩ ከወጣትነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ መልካም አጋጣሚዎችም ሆኑ ተግዳሮቶች የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ተመሳሳይ አይሆኑም። በሌላ አነጋገር ወጣትነት አንድ የዕድገት ደረጃ ቢሆንም፣ ተፈጥሯዊው ዕድገት ዕውን የሚሆነው በተለያዩ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዓውድና ሥርዓቶች ውስጥ ስለሆነ ተመሳሳይ የሆነ የተፈጥሮ ዕድሜ የሚኖረው ሥፍራ፣ ትርጉምና ኃላፊነት ፍፁም የተለያየ ነው። ስለዚህ ወጣቶች የሚለው ጥቅል ማንነት ከፍተኛ የሆነ ሚና ያላቸውን ልዩነቶችን እንዳይሸፍን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ተመሳሳይ የዕድሜ ስብስብ ውስጥ ከመሆን ባሻገር በወጣቶች መካከል ያሉትን አንድነቶችና ልዩነቶች በተገቢው መጠን መረዳትና ለሚዘጋጁ የፖሊሲም ሆነ የሕግ ማርቀቅ ሒደቶች ውስጥ ማስረፅ፣ አካታችነትን ለማሳካትና መገለልን ለማስቀረት ይረዳል። ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እየተስፋፉ የመጡትን ግጭቶች፣ ከመኖሪያ ሥፍራ መፈናቀል፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች፣ ጦርነት፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት መመሰቃቀል ከሥር መሠረታቸው ለማየትና የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሒደት ወጣቶችን ትርጉም ባለው መንገድ ማሳተፍ ካለበት፣ ከወጣትነታቸው ባልተናነሰ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ማንነቶች በተገቢው ሁኔታ መታየት አለባቸው። ለምሳሌ ግጭት፣ ጦርነትና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ሲፈጠር ሴት ወጣቶች የሚደርሱባቸው ፆታን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎችና ለሌሎች ሥርዓታዊ ለሆኑ ጥቃቶችና መገለሎች ያላቸው ተጋላጭነት ይጨምራል። ወጣት ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ አካላዊ ጥቃትን ለማድረስ፣ ወንጀሎችን ለመፈጸምና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ለሚያካሄዱት ኃይል የተቀላቀለ ዕርምጃ ፈጻሚዎችም ሆነ ተጎጂዎችም የመሆን ዕድላቸው በጣም የሰፋ ነው። ስለዚህ ወጣት ወንድነትና ወጣት ሴትነት በግጭትና ጦርነት ወቅት ያላቸውን ተመሳሳይም ሆነ የተለያዩ ተጋላጭነት፣ በሒደቱ ውስጥ የሚኖሩትን ሚናዎችም በአፅንኦት መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
ከሥርዓተ ፆታ በተጨማሪ የመኖሪያ ሥፍራን (ከተማ ወይም ገጠር)፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደብ (የሀብት ደረጃ)፣ የፖለቲካ፣ የርዕዮተ ዓለምና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች፣ የትምህርት ደረጃ፣ የብሔር/የባህልና የቋንቋ ማንነቶች ወጣቶችን በተለያየ ጎራ ይከፋፍላሉ። ከዚህም በተጨማሪም ለተለያዩ አስተሳሰቦችና ተግዳሮቶች ያለው ተጋላጭነትና የሚኖሩት ምላሾችም እንዲሁ በወጣቶች መካከል ከፍተኛ የልዩነት መስመሮች ናቸው። ወጣቶች ለዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች፣ ለግጭት፣ ለዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች፣ ለመገናኛ ዘዴዎችና አስተሳሰቦች ያላቸው ተጋላጭነት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል እኩል አይደለም። ስለዚህ በአገራዊው የምክክር ሒደት ውስጥ ትርጉም ባለው መንገድ ወጣቶች መሳተፍ አለባቸው ሲባል በዕድሜያቸው ወጣት መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በተለያየ የማኅበራዊ ሥፍራ ላይ ሆነው አገራችን እያለፈችበት ያለውን ችግር የተጋፈጡበትን ማንነት እኩል ያማከለ መሆን አለበት።
- ውስብስብ ሒደቶችንና ሁኔታዎችን የሚመጥኑ ሥልቶችን መቅረፅ
የለውጥ ሒደት ቀጥተኛ መስመርን አይከተለም። የለውጥ ሒደት ውስብስብ የሆኑና ሄድ መለስ የሚሉ የተጠላለፉ መስመሮችን የሚከተል ነው። የአገራዊው የምክክር ሒደት ሊያሳካው የሚፈልጋቸው የለውጥ ዓላማዎች በቅደም ተከተል የተቀመጡ ምዕራፎችን እያጠናቀቀ ከመሄድ ይልቅ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ላይ እያከሉ፣ ተግዳሮቶችን ምላሽ እየሰጡ የሚሄዱ ሥልቶችን ቢያካትት ይመረጣል። የአገራዊው የምክክር ሒደት ፖለቲካዊ ሒደት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ፖለቲካዊ እንደ መሆኑ መጠን የኃይል ፉክክር፣ የኃይል ሚዛን መዛባትና በተቃራኒ ጎራዎች መካከል የአሸናፊነት ፍላጎትን የማሳካት ሒደቶች ፈተናዎችንም ሆነ ጥሩ ዕድሎችንም ይፈጥራሉ።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦ ፖለቲካዊ ቀጣና አንፃርና ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አኳያ ምዕራባውያን አገሮች፣ ሩሲያ፣ ቻይናና የባህረ ሰላጤው አካባቢ ዓረብ አገሮች የራሳቸውን አጀንዳና ፍላጎት ለማስረፅ የሚችሉትን ከማድረግ አይቆጠቡም። የዓለም የከበርቴውን መደብና የድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶችን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃርና የኒዮሊበራል ኢኪኖሚያዊ አስተሳሰብ፣ የምዕራባውያንን የሊበራል ዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማሥፈን የሚጥሩት የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና በምዕራባውያን የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የጥናትና ምርምር ማዕከሎችና ድኅረ ግጭትን በተመለከተ የማማከርና የማስተባበር ሥራ የሚሠሩ አያሌ ተዋንያን በአገራዊ የምክክር ሒደቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚናና ተፅዕኖ እንዲኖራቸው መሞከራቸው አይቀርም። ለዚህም ነው የለውጥ ሒደቱ ውስብስብነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት በጥንቃቄ መቃኘት አለበት የምለው።
ከላይ ያነሳኋቸው መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ሁኔታዎችና ከዕድሜ ባሻገር ያሉት የወጣትነት ድርብርብ ማንነቶች የሚያስገነዝቡን ነገር ቢኖር፣ ትርጉም ያለው የወጣቶች ተሳትፎን በአገራዊ ምክክር ሒደት ውስጥ ማረጋገጥ በጥናት የተደገፈ፣ ብዙኃንን ያማካለና በረጅም ጊዜ ሒደት የሚሠራ ትልቅ ሥራ ነው። ለዚህ ሥራ የሚረዱ ሰፊ የውይይት ምኅዳሮች፣ ሐሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመር አለባቸው። ከተግባራዊ ሥራዎች ደግሞ የሚጠቅሙ ልምዶችን በመቀመር ለሌሎች ሁኔታዎች የሚመጥኑ፣ የተለያዩ ዓውዶችን ያገናዘቡ ቀኖናዊ ሳይሆን፣ እንደ አመቺው ሁኔታ የሚተገበሩ ሐሳቦችን ማጎልበት ያስፈልጋል። በመጨረሻም በአጭሩ የተቃኙት ሦስት ዓበይት ነገሮችን ሊጠቀሙባቸ የሚችሉት በወጣቶች የሚመሩ ድርጅቶችና ማኅበራት፣ የሚከተሉትን ነጥቦች ከግንዛቤ ቢከቱ ምናልባት ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ።
- አገራዊው የምክክር ሒደት በአጠቃላይ ለወጣት ማኅበራትና ድርጅቶች የግብዣ ሥፍራ ነው። የምክክር ኮሚሽኑ አመሠራረትና አካሄድ ላይ ወጣቶች የነበራቸው ሚና በጣም ውስን ነበረ። ስለሆነም የምክክር ሒደቱን የሚመራው ኮሚሽን ሲጋብዛቸው ብቻ ነው የወጣት ማኅበራትና ድርጅቶች (ሌሎች ተዋናዮችም ቢሆኑ) በምክክር ሒደቱ ውስጥ መሳተፍ የሚችሉት። ስለዚህ የወጣት ማኅበራትና ድርጅቶች ራሳቸውን በማደራጀትና በማብቃት ወደ ምክክር ሒደቱ ለመጋበዝ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆን አለባቸው።
- መደራጀት ኃይል ይሰጣል። በተገቢው መንገድ የጎለበተ ሐሳብና ዓላማ ያላቸው የወጣት ማኅበራትና ድርጅቶች ወደ አገራዊው የምክክር ሒደት የመጋበዝ ዕድል እንዲኖራቸው የውትወታ፣ የቅስቀሳና የማሳመን ሥራዎችን በመሥራት አቅማቸውን ማሳየት አለባቸው። በተጨባጭ የሚታይ አቅምና ብቃት ማሳየት የቻሉ የወጣት ድርጅቶችና ማኅበራት ወደ ምክክር ሒደት አለመጋበዛቸው የሒደቱን ቅቡልነት ሊያሳጣ ስለሚችል፣ እንዲህ ያለ ውስጣዊና ከመደራጀት የሚመነጭን ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።
- ወጣቶችን የሚመለከቱ አጀንዳዎችን ቀርፆ ማወያየት በወጣት ድርጅቶች መሪነት መጀመር አለበት። የወጣት ድርጅቶችና ማኅበራት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑንና ሌሎች በሒደቱ ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን አካላት፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ተቋቋሙ የውይይትና የሐሳብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች በመጋበዝና የውይይት አጀንዳዎችን፣ ፍሬ ነገሮችንና የሚጠብቁ ውጤቶች አስቀድሞ በመወሰን ለአጠቃላይ አገራዊው ምክክር ሒደት ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን ለማመንጨት ዝግጁ መሆን አለባቸው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ebalcha@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡