በሶስና ደምሴ
በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተዘጋጀ ውይይት ላይ ሦስት ምሁራን የተሳተፉበትን ውይይት በፅሞና ተከታትዬ ነበር፡፡ ውይይቱ ቀልቤን የሳበው ከርዕሱ በተዛመደ እኔንም ሲያሳስቡኝ የኖሩ ጉዳዮች ስላሉትና ይህንኑ ለአንባቢያን ለማካፈል ነው፡፡ ሙያዬ ከግብርናና ሥርዓተ ፆታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አማካሪ በመሆን ከአንድ አፍሪካዊ ጋር፣ “South South Cooperation” በሚል ርዕስ ጥናት ለማካሄድ ወደ ታይላንድ ሄደን ነበር፡፡ የጥናቱ ዓላማ በልማት ዕድገታቸው ፈጣን ከሆኑ አገሮች አፍሪካ ምን ልትማር ትችላለች በሚል የልምድ ልውውጥ ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
በታይላንድ ቆይታችን ያገኘነው ዕውቀትና ግንዛቤ ከውይይቱ ጋር የተዛመደ በመሆኑ እዚህ ላይ ላነሳው ወድጃለሁ፡፡ ታይላንዶችም እንደ እኛው ቀደም ሲል በሳይንስ ትምህርት ተማሪዎቻቸውን በብዛት እንዲሠለጥኑ አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹ ሥልጠናቸውን ከአጠናቀቁ በኋላ የሥራ ዕድል ለማግኘት ተቸገሩ፡፡ ሁኔታውን በማጥናት ለችግሩ በሚከተለው ሁኔታ መፍትሔ ሰጡ፡፡ ኢንዱስትሪዎችና በአጠቃላይ የግል ኢኮኖሚ ተቋማት ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ አደረጉ፡፡ በዚያ መሠረት የትምህርት ተቋማቱ በተጠቀሱት አካላት ፍላጎት መሠረት ካሪኩለማቸውን በማስተካከል ለወጣቶች ትምህርት እንዲሰጡ ተደረገ፡፡
በተጨማሪም ክፍተቱን ለመሸፈን ተማሪዎቹ በዕረፍታቸው ጊዜ በግል ተቋማትና በኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ ትምህርታቸውና ዝንባሌያቸው ተደልድለው የነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ ተቀየሰ፡፡ በዚህም ሥራቸውና ትምህርታቸው ምን ያህል ዝምድና እንዳለውና ሊሻሻል የሚችልበትን ሁኔታ አጢነው ዘገባ እንዲያቀርቡ ሲደረግ፣ የግል ሴክተሩም በተማሪዎቹ የሥራ ሒደት ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ግኝትና አስተያየታቸውን ለመጡበት የትምህርት ተቋም እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ የትምህርት ተቋሙም መሻሻል ያለበትን በማጤን ካሪኩለሙን በማሻሻል ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎችም የግል ተቋማት ጋር ጥብቅ ቁርኝት በማድረግ፣ አልፎ አልፎም ከግል ተቋማት ባለሙያዎች እየመጡ ትምህርት እንዲሰጡ አደረገ፡፡
ይህ ሒደት ወጣቶቹ ሲመረቁ ያለ ምንም ችግር ውጤታማ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የሰው ኃይል ቀደም ሲል ሲደረግ እንደ ነበረው ከጃፓን ከማስመጣት ይልቅ በአገራቸው በሚገባ ለማሠልጠን መቻላቸውን ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ገልጸውልናል፡፡ ተማሪዎቹም በፍላጎታቸውና በምርጫቸው ስለሚማሩ ለሥራው ፍሬያማ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገለጹልን፡፡
ሌላው አንዴ ከሥራዬ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ያጋጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ በሙያ ትምህርት ከኢቲቪኢቲ (Technical and Vocational Education and Training – 10 +) ተማሪዎች በመስተንግዶና በሌሎችም ሙያዎች እንደ ፍላጎታቸው ሠልጥነው በየሆቴሉ ይመደባሉ፡፡ ያነጋገርናቸው የሆቴል ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች በሠራተኞቹ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም ለተመደቡት ሠራተኞች ተጨማሪ ሥልጠና መስጠት የግድ ነበረባቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች የሠለጠኑት አሁን ሆቴሎች በሚያስፈልጋቸው ደረጃ አይደለም፡፡ ለዚህም የሰጡን ምክንያትና ከእኛም ምልከታ እንደተረዳነው ሆቴሎቹ ትልልቅና ዘመናዊ ስለሆኑ አስተማሪዎቹ ለውጡን ለማየት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም፡፡ አስተማሪዎቹ የሚያስተምሩት በቆየ ካሪኩለም ሲሆን፣ በለውጡ መሠረት ማስተማሪያቸውን ለማስተካከልና የለውጡንም ሒደት ግንዛቤ ለማግኘት ሆቴሎቹ ውስጥ ገብተው ሁኔታውን ማየት ይገባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ሆቴሎቹ ውስጥ ገብተው ለመስተናገድና ለውጡን ለማየት አቅማቸው አይፈቅድም፡፡
እኛም በወቅቱ እንደ መፍትሔ የሰጠናቸው ሆቴሎቹ አስተማሪዎቹን በመጋበዝ የሥራ ሒደቱንና ለውጡን እየተመለከቱ በዚያው መልኩ የሚሰጡትን ትምህርት እንዲያሻሽሉ በማድረግ፣ ሆቴሎቹም ማሠልጠኛ ተቋሙም ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላል የሚል ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ እንደ አሁኑ የኢንተርኔት መረብ ባልተስፋፋበትና መረጃ በቀላሉ በማይገኝበት ጊዜ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ለባለሆቴሎቹ በሆቴሎች ላይ የተለወጠውን ተጨባጭ ሁኔታና የሚፈልጉትን የአገልግሎት ዓይነት አስተማሪዎቹ እያዩ የሚሰጡትን ትምህርት እንዲያሻሽሉ ማድረጉ ሁለቱንም ወገን የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ይህ የሚያሳየን ዳር ሆኖ ስለችግሩ ከማውራት ይልቅ የመፍትሔው አካል ሆኖ መገኘት እንደሚሻል ነው፡፡
በሌላ ጊዜ ለአንድ ፕሮጀክት ግምገማ ወደ ገጠር ከሌሎች ቡድን ጋር ሄጄ በነበረበት ጊዜ፣ አንድ ቀበሌ ውስጥ ገብተን የገበሬውን ሕይወት ለማሻሻል የተሠሩ ሥራዎችን ለመመልከት ችለን ነበር፡፡ በዚህም የግብርናው ባለሙያ (ኤክስቴንሽን ኤጀንት) በቀበሌው በግብርና የታቀደውን ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ለገበሬው እንዳስተዋወቁና ኅብረተሰቡ እየተጠቀመበት መሆኑን ገለጸልን፡፡
ከጥናቱ ቡድን ጋር ይህን የእርሻ ባለሙያ ሪፖርት ከአዳመጥን በኋላ፣ ከባለሙያው በመነጠል ተጠቃሚዎቹን ለመጠየቅ ሄድን፡፡ እንደ አጋጣሚ የገባንበት ቤት የዚሁ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነገሩን፡፡ እኛም ፕሮጀክቱ እንዴት እንደ ጠቀማቸው ስንጠይቃቸው፣ የኤክስቴንሽን ኤጀንቱ አለመኖሩን ከአረጋገጡ በኋላና የሚነግሩንን ለእሱ እንዳንናገር በማስጠንቀቅ የሚከተለውን አስረዱን፡፡ ‹እንደምታዩት የአካባቢው ቤቶች ጣራቸው ዝቅተኛና በሳር የተከደነ ነው፡፡ በዚህ ላይ የቤቱ ስፋት ትንሽ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ባሳዩን ቋሚ የሆነ የማይነሳ የማገዶ ቆጣቢ ምጣድ ሠርተን ስንጠቀምና ጋግረን ስንጨርስ ምጣዱ ቶሎ ስለማይበርድ፣ እንዳይሰነጣጠቅ ብዙ ማሰሻ በላዩ ላይ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህም ወጪው ቀላል አይደለም፡፡ በምጣድ የማይሠሩ እንደ አሻሮና ሌላም ለመሥራት ምጣዱን ከቦታው አታንቀሳቅሱ በማለት በቋሚነት የተተከለ በመሆኑ ይቸግረናል፡፡ የእርሻ ባለሙያዎቹ ሳይኖሩና ሳያዩን ምጣዱን አንስተን ቦታውን ለሌላም አገልግሎት እንጠቀምበታለን፡፡ የእርሻ ባለሙያዎቹ ይህንን ሲመለከቱ ይቆጡናል› በማለት ነገሩን፡፡
የጥናት ቡድኑም ይህ ለእናንተ ይጠቅማል ተብሎ ማገዶ እንዲቆጥብላችሁ የተሠራ ነው፡፡ የማይጠቅማችሁ ከሆነ ለምን ለእርሻ ባለሙያዎቹ ችግራችሁን አትነግሩም አልናቸው፡፡ ተጠቃሚዎቹም ‹ባለሙያዎቹ ያሰቡትን እንጂ እኛ የምንላቸውን አይቀበሉንም› አሉ፡፡ በማስከተልም የእርሻ ባለሙያውን ስለሁኔታው ስንጠይቀው አንዳንድ ሰዎች ልምድ ለመለወጥ ያለ መፈለግ እንጂ፣ እኛ ከላይ ታቅዶ የተሰጠንን ሁሉ ተግባራዊ አድርገናል በማለት ኃላፊነቱን እንደተወጣ ነገረን፡፡ የጥናቱ ቡድኑም ሰዎቹ ያለባቸውን ችግር ለምን ለምርምር ቢሮ ነግራችሁ እንደ አገሩ ሁኔታና ቦታ ጉዳዩን እንዲያዩት አይደረግም ስንል፣ እኛ (የእርሻ ባለሙያዎች) ከምርምር ቢሮ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለንም፡፡ ከግብርና በተሰጠን ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ አድርገን ይህንኑ ለግብርና ሪፖርት ማድረግ አለብን በማለት ተናገረ፡፡
ከዚህ በላይ በአጭሩ የቀረበው ሁኔታ የእርሻ ባለሙያዎችና በምርምር አካሉ መካከል ቅንጅት ባለመኖሩ፣ ለኅብረተሰቡ ይጠቅማል ተብሎ የሚተዋወቀው አዲስ ሐሳብ በተቀናጀ መንገድ ስለማይተገበር ውጤታማ ለመሆን ያለመቻሉ ነው፡፡ የእርሻ ባለሙያው ደመወዝ የሚከፍለውና ሥራውን የሚቆጣጠረው የግብርናው ክፍል በመሆኑ፣ ታቅዶ የተሰጠውን በመፈጸም የሥራ አፈጻጸሙን ማሳመር እንጂ ሥራው ውጤታማ ነው አይደለም ካልሆነ በምን ሊስተካከል ይችላል የሚለው በዋናነት የሚያሳስባቸው አይሆንም፡፡ የእርሻ ባለሙያውና የምርምር ቢሮዎች ግንኙነት የላላ በመሆኑ ሁሉም በየፊናቸው ያቀዱትን ሥራ መሥራታቸውን እንጂ ለውጤታማነቱ ብዙም ትኩረት አያደርጉም፡፡
ጉዳዩን ከአነሳሁት አይቀር በዚሁ ላይ ሌላው ገጠመኜን ባነሳው ደስ ይለኛል፡፡ በአንድ የመስክ ጥናት ላይ አብራኝ ትሠራ ከነበረች የፊሊፒንስ ተወላጅ ጋር አብረን ገጠር ሄድን፡፡ በሲዳ (SIDA) ፕሮግራም ተደግፎ ይካሄድ የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ዋናው ሥራችን በግብርናው ሥራ ላይ የሴቶች የሥራ ጫና ለይቶ በማወቅ መፍትሔ ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ በግብርና ሥራ ላይ የነበረች አንዲትን ወጣት ሴት ገበሬ አነጋገርን፡፡ ከአቀረብንላት ጥያቄ የመጀመርያው ከሥራዋ ሁሉ ከባዱ የትኛው እንደሆነ እንድትገልጽልን ነበር፡፡ ወጣቷም ‹ከሁሉም የሚከብደው የጤፍ አረም ነው፡፡ በክረምት ወቅት አሁን እንደምታዩኝ ሕፃን ልጄን አዝዬ፣ ሁለተኛዋንም እቤት ትቼ መምጣት ስለማልችል አጠገቤ አድርጌና አጎንብሼ ሳርም መዋሉ በጣም ይከብዳል፡፡› የሚል ምላሽ ሰጠችን፡፡
የጥናቱ ባልደረቦችም ይህንና ሌሎችንም ሁኔታዎች ካዳመጥን በኋላ በውይይት ላይ በእነሱ አገር ሳያጎነብሱ ቆመው ሊያርሙ የሚችሉበት፣ ለጤፍም ሊሆን የሚችል በቀላሉ የተሠራ የማረሚያ መሣሪያ እንዳለ፣ በተለይም በመስመር ቢዘራ ለአስተራረሙ መቀላጠፍ ይረዳል ብላ ነገረችኝ፡፡ በዚህም ዜና በጣም በመደሰት ከግብርና ባለሙያው ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያየን፡፡ ባለሙያውም በናሙና መልክ የተባለው አንድ መሣሪያ ቢመጣልን ጥናት ከአደረግንና ጠቃሚ መሆኑን ከፈተሽን በኋላ፣ በሥራ ላይ እንዲውል ልናደርገው እንችላለን በማለት ሐሳቡን አካፈለን፡፡
የፊሊፒንስ የሥራ ባልደረባዬም አገሯ እንደ ተመለሰች ቃሏን ጠብቃ ይህንኑ ለጤፍ ማረሚያ ሊሆን የሚችል መሣሪያ ይዛ መጥታ ለዚያ ለእርሻ ባለሙያ አስረከበች፡፡ በአስረከበችበት ወቅት አብሪያት ባልኖርም በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጥናት ቦታው ሄጄ የእርሻ ባለሙያው ቢሮው በተገኘሁበት ጊዜ፣ ያ ከፊሊፒንስ በስጦታ መልክ የመጣው የጤፍ ማረሚያ ሊሆን የሚችል የእርሻ መሣሪያ እዚያው ቢሮ ውስጥ አንድ ጥግ ተቀምጦ አየሁት፡፡ እኔም ይህንኑ ባለሙያ ምን እንደሆነ ስጠይቀው፣ ‹በእውነቱ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ከእኔ በፊት የዚሁ ቢሮ ኃላፊ ግለሰብ በነበረበት ጊዜ የመጣ ነው› የሚል መልስ ሰጠኝ፡፡
ይህ ክስተት እንግዲህ ብዙ ነገር ይናገራል፡፡ በመንግሥት ቢሮዎች የኃላፊዎች መለዋወጥ ለሥራው ቀጣይነት ያለው እንቅፋት፣ ሠራተኞች በሚለዋወጡበት ጊዜ ከሥራው ቀጣይነት ጋር በተገናኘ የሚያካሂዱት ርክክብ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ፣ የቅርብ አለቆች በዋናው የሥራ ሒደት ላይ ያላቸው ተቆጣጣሪነት አናሳ መሆን፣ ከሁሉም በላይ ተቋማዊ ትውስት (ኢንስቲቱዩሽናል ሜሞሪ) አለመኖር ምን ያህል የሥራውን ቀጣይነት እንደሚጎዳው የሚያሳይ ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት እያሰብኩት ከሁሉም በላይ የሚደንቀኝ ከገጠር ወጥተው የሚማሩ ተማሪዎች በአካባቢያቸው ያለውን የሥራ ክብደት፣ በአባቶቻቸውና በእናቶቻቸው ላይ ያለውን የሥራ ጫና እያዩ፣ እነሱም የሥራው ጫና ተካፋይ ሆነው እያደጉ ከዚያ ሲወጡ ያንን ሁኔታ ለማሻሻል ምርምርም ሆነ ሌላ ጥረት በማድረግ ሁኔታውን ለመለወጥ ሲተጉ አለመታየታቸው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እስካሁን ድረስ በገጠሩ ኑሮ ላይ ብዙ የተለወጠ ነገር አይታይም፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንዱ ከገጠር የሚወጡ ተማሪዎች ሁኔታውን በቁጭት ለመለወጥ በቂ ጥረት አለማድረጋቸውም ጭምር ይመስለኛል፡፡
ከገጠር የሥራ ጫናዎቹ መካከል በየገጠሩ ሴቶች እንሥራ በመሸከም ከሩቅ ሥፍራ በወጣ ገባ መንገድ ወገባቸው እየተቀጠቀጠ ውኃ ይቀዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው አርጅተውና ጎብጠው ይታያሉ፡፡ እስካሁን የተደረገው ለውጥ ከሸክላ እንስራ ወደ ፕላስቲክ እንስራ መቀየር ብቻ ነው እንጂ፣ ለጀርባቸው በሚያመች ሁኔታ የተሠራ በጀርባ እንደሚታሰር ቦርሳ (ባክ ባግ) ዓይነት በቀላሉ የሚታዘል አልሆነም፡፡ የእርሻውም ሁኔታ ለዘመናት በሚሠራበት በሞፈርና በቀንበር ነው፡፡ በአንድ የሥራ አጋጣሚ ጥሩ ምርት አግኝተው ኑርዋቸው የተሻሻለ ሁኔታ ላይ ያሉ ገበሬዎችን ስናነጋግር፣ በሚቀጥለው እርሻችሁ ላይ ምን ኢንቨስት ታደርጋላችሁ ሲባሉ ማድረግ የሚፈልጉት ከግብርና ውጪ ከተማ ሄደው ቡና ቤት መክፈት፣ ወይም መኪና ገዝቶ መነገድ እንጂ ግብርናውን በማዘመንና በዚህም የበለጠ ውጤት ለማምጣት ማቀዳቸውን አይገልጹም፡፡ ይህ የሚያሳየው ግብርናው ኋላቀር በመሆኑና ብዙ ድካም ስለሚጠይቅ አሻሽሎ ውጤታማ ከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ሌላ ሥራ መሄዱን ይመርጣሉ፡፡
የአገራችን ምጣኔ ሀብት በእርሻ ላይ የተመሠረተ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ግብርና ለአገሪቱ አጠቃላይ ምርት፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆንና ለሥራ ፈጠራ ያለውን አስተዋጽኦ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ክፍለ ኢኮኖሚ በተቻለ መጠን ማዘመንና ለዕድገት የሚኖረውን ድርሻ መጨመር በአገራችን ላይ የሚኖረው ሚና በቀላል የሚገመት አይሆንም፡፡ ወጣቱም ሁኔታውን ለመለወጥ መመራመርና በየአቅጣጫው በተሰማራበት ሙያ ሁሉ ለውጥ ለማምጣትና ሥራ ፈጣሪ በመሆን በአገሩ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ኢኮኖሚያቸውን በአብዛኛውም ሆነ በከፊል በእርሻ ላይ ከመሠረቱ አገሮች ትምህርት በመውሰድና ከአገራችን ሁኔታ ጋር በማዛመድ ብዙ ኋላቀር አሠራሮቻችንን ማሻሻልና ከችግራችን መውጣት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዋ የሥርዓተ ፆታ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው sosenadem@yahoo.ca ማግኘት ይቻላል፡፡