የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ‹‹ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናትና የልማት ፍኖተ ካርታ›› በሚል ርዕስ ያስጠናው ጥናት ለወራት ከክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞች፣ ዳኞች፣ የተጫዋቾች ማኅበር፣ እንዲሁም የተለያዩ የባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቧል፡፡ ጥናቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ለዘመናት ወደኋላ የቀረቡትን ዋና ዋና ጉዳዮች ጥልቅ በሆነ ትንታኔ የነበሩበትን ችግሮችና የወደፊት መፍትሔዎች ፍንትው አድርጎ ማሳየት የቻለ ነበር፡፡ በአሜሪካ ታውሰን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፌስ ኮርነር አማካሪ ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) አማካይነት ተጠንቶ የቀረበውና 246 ገጾችን የያዘውን ጥናታዊ መጽሐፍ ለአክሲዮን ማኅበሩ አስረክበዋል፡፡ ከጥናታዊ ጽሑፉ አጠቃላይ ይዞታና የቀጣይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንኳር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- መሠረታዊ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ጋሻው፡- የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ ጥቅል ዓላማው ክለቦች በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲመሩ ማድረግ ነው። ፊፋ እግር ኳስን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል ሲሆን፣ ሥልጣኑን በአኅጉር ደረጃ ለማስፈጸም ለኮንፌዴሬሽኖች ያስተላልፋል። ክለቦች በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲመሩ ለማስቻል ፊፋ የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመርያን አዘጋጅቶ ክለቦች በሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሊያሟሉ የሚገባቸውን ዝቅተኛ መሥፈርቶችን አስቀምጧል። የፈቃድ አሰጣጥ መመርያው እንደሚያመለክተው የክለቦች አቅም ከአገር አገር የተለያየ በመሆኑ፣ በመምርያው አፈጻጸም ላይ የሚኖረው ጫና መጠን ከአኅጉር ወደ አኅጉር ሊለያይ ይችላል። በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚወሰኑ ጉዳዮች ኮንፌዴሬሽኑ ሥልጣኑን ለብሔራዊ እግር ኳስ ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ይሰጣል።
ሪፖርተር፡- ክለቦች በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲመሩ ለማስቻል፣ ክለቦች በሊግ ውድድር ውስጥ ለመሳተፍ ሊያሟሉ የሚያስፈልጓቸው ዝቅተኛ መሥፈርቶች ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ጋሻው፡– በኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበሩ መመርያዎች በካፍ (የአፍሪካ እግ ኳስ ኮንፌዴሬሽን) መመርያዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ አምስት ደረጃዎች አሉት፡፡ የስፖርቱ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የሰው ኃይል፣ ሕጋዊና ፋይናንሺያል ጉዳዮች በቅድሚያ ይጠቀሳሉ። የክለብ ውድድሮችን ታማኝነት ማስጠበቅ፣ የፕሮፌሽናሊዝም ደረጃን ማሳደግ፣ ስፖርታዊ እሴቶችን ማሳደግና ውሳኔዎችን በፍትሐዊነት መርሆች ላይ መመሥረት የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መሠረታዊ ዓላማዎች ናቸው። ደኅንነቱ የተጠበቀ የጨዋታ መድረኮችን ማመቻቸት፣ የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትን ማሳደግና በክለቦች ባለቤትነት ላይ ግልጽነትን መፍጠርም ከመሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ሪፖርተር፡- ጥናቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ፈቃድ አሰጣጥና የሕግ ማዕቀፉ ላይም ትኩረት አድርጓል። በኢትዮጵያ ስላለው የፈቃድ አሰጣጥ የሕግ ማዕቀፍ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ጋሻው፡- መመርያው ከፊፋና ከካፍ የወጣ ቢሆንም፣ መሠረታዊ መሥፈርቶቹ በስፖርት ኮሚሽን በ2005 ዓ.ም. ይፋ ሆነው ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የስፖርት ማኅበራትን ማቋቋሚያ ደረጃ ለመወሰን መመርያ ቁጥር 1/2003 ያፀደቀ ሲሆን፣ የመመርያው አንቀጽ 14 ክለብ ለማቋቋም ዘጠኝ ነጥቦችን ያዘለ መመርያ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በፕሪሚየር ሊጉ ሥር ያሉ ክለቦች የፊፋና የካፍ ክለብ የፈቃድ አሰጣጥ መመርያን ብቻ ሳይሆን፣ የ2005 ዓ.ም. የስፖርት ማኅበር አደረጃጀት መመርያን እንዲያከብሩ ማስገደድ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የሊጉ ኃላፊነት እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር መመርያዎችና የፕሪሚየር ሊግ የዕድገት ዕቅዶች ስኬት የሚወሰነው ከዓለም አቀፍ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ ድረስ መመርያዎቹ በትክክል መተግበር ሲችሉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በጥናቱ 90 ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ተገልጿል። የክለብ ፈቃድ መመርያዎችን በተመለከተ የባለድርሻ አካላት ዕይታ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ጋሻው፡- ካፍ መመርያውን ከፊፋ ተቀብሎ በአኅጉሪቱ መሠረት አዘጋጅቶ ለአባል አገሮች አቅርቧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ለዚህ መመርያ ተገዥ እንደሆነ በመመርያው ተገልጿል። ነገር ግን በጥናቱ ከተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ እንደሚያመለክተው፣ አመራሩ መመርያውን ለማስፈጸም ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው ያሳየ ሲሆን፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች ፌዴሬሽኑ በአፈጻጸሙ ላይ ጥብቅ ዕርምጃ አለመውሰዱ ለችግሩ መንስዔ ዋነኛ ምክንያት እንደነበር አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለቁርጠኝነት መጥፋት ጥናቱ ያገኘው ምን ነበር?
ዶ/ር ጋሻው፡- ፌዴሬሽኑ ከባድ ዕርምጃ ባለመውሰዱና ጠንካራ ጫና ያለማሳደሩ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ቅጣቱ ክለብን በውድድር ላይ ተሳትፎ እንዳያደርግ እስከ ማገድ ሊደርስ ይችላል፡፡ በካፍ የክለቦች ውድድር አገርን ወክለው ሲሳተፉ ክለቦችን ማገድ አገራዊ ጥቅምን የሚጎዳ ሲሆን፣ ክለቦች መሥፈርቱን አላሟሉም ሲባሉ የየአካባቢው ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግላቸው ቀርበው በሒደት መሥፈርቶቹን እንዲያሟሉ ይማፀናሉ። በዚህም ምክንያት ፌዴሬሽኑ ቁርጠኛ መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡ እስከ ዛሬ ሲስተዋል የነበረው በቀጣይ የቁርጠኝነት ያለመኖር ችግር በአክሲዮን ማኅበሩ፣ በፌዴሬሽኑ፣ እንዲሁም በባለድርሻ አካላት ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ሌላው በጥናቱ የተነሳው የክለብ የባለቤትነት ይዞታ በተመለከተ ነበር፡፡ በዚህ ጋር በተያያዘ ጥናቱ ምን ይላል?
ዶ/ር ጋሻው፡- የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ፣ በዋናው ጥናት ነጥረው ከወጡና የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱና ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚቀመጥ ነው። በመሆኑም በዚህ የመወያያ ርዕስ ሰነድ ሥር የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ከባለ ድርሻ አካላት ዕይታ ከአገሮች ተመክሮና ከገዥ የእግር ኳስና የንግድ ሕግ ማዕቀፍ አኳያ ተፈትሾ፣ የአማራጭ መንገድ ተሰናድቷል፡፡ ለውይይትም ቀርቧል። አክሲዮን ማኅበሩ በክለቦች ጥምረት የተመሠረተና ልማቱን እየጀመረ ያለ ተቋም በመሆኑ፣ የሊጉ ወቅታዊ ሁኔታ ክለቦቹ ለረዥም ዓመታት ያጋጠሟቸው ችግሮች ማሳያዎች ናቸው። ክለቦቹ በመንግሥት ገንዘብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የቦርድ አመራር አወቃቀራቸው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ነው፡፡ ተቋማዊ ደረጃቸው ደካማ የሆነና የብሔር መገለጫ ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የሌሎች አገሮች ሊጎች የክለብ ባለቤትነት ይዞታ ልምድ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ጋሻው፡- በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች፣ የስፖርት ክለቦች የባለቤትነት ይዞታ በታሪክ ሒደት ውስጥ እየተቀየረ መጥቷል፡፡ በአውሮፓ በሚገኙት 54 ሊጎች ውስጥ ሁለት ዓይነት የእግር ኳስ ክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ የግልና የማኅበረሰብ ወይም የሕዝብ ናቸው። እ.ኤ.አ. በ2019 እና 2020 የውድድር ዘመን በአውሮፓ 54 ሊጎች ውስጥ 712 ክለቦች በአባልነት የታቀፉ ሲሆን፣ ከ54 ሊጎች ውስጥ ስምንቱ ሊጎች ሙሉ በሙሉ በግል ይዞታነት የሚተዳድደሩ ክለቦችን ሲያሰተናግዱ፣ 12 ሊጎች ሙሉ በሙሉ በማኅበረሰብ ይዞታነት የሚተዳደሩ ክለቦች አሏቸው፡፡ የተቀሩት 34 ሊጎች በሁለቱም በማኅበረሰብና በግል ይዞታዎች የተያዙ ክለቦችን ቀላቅለው ያስተናግዳሉ (ለምሳሌ ስፔን፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ግሪክ፣ ቱሪክ) ይጠቀሳሉ፡፡ ከእንግሊዝ በስተቀር በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተያዙት ክለቦች ቁጥር በውጭ አገር ባለሀብቶች ከተያዙት ይበልጣሉ።
በአውሮፓ ከሚገኙት ሁለቱ የክለብ ባለቤትነት ይዞታ ዓይነቶች የግልና የሕዝብ (ማኅበረሰብ)፣ በተጨማሪ የአፍሪካ ተሞክሮ ሦስተኛ የባለቤትነት ይዞታ ዓይነትን አስተናግዶ ይገኛል፡፡ ይኸውም የመንግሥት የባለቤትነት ይዞታ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ያሉት ክለቦች አብዛኞቹ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እግር ኳሱ በኢትዮጵያ ማደግ እንዲችል ክለቦች ከመንግሥት እጅ ወጥተው ራሳቸውን ችለው መቋቋም ይገባቸዋል፡፡