የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግሥት የፈረንሣይ ወታደሮች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአገሪቱ ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የቡርኪናፋሶ ፕሬስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ ቡርኪና ፋሶና ፈረንሣይ እ.ኤ.አ. በ2018 በገቡት ስምምነት መሠረት በቡርኪና ፋሶ የሚገኙ የፈረንሣይ ወታደሮች ሙሉ ለሙሉ ወጥተው የሚያበቁበት ጊዜ አንድ ወር ቀርቶታል፡፡
የፈረንሣይ ወታደሮች በቡርኪናፋሶ እንዲቆዩ ከዚህ ቀደም በነበረው መንግሥት የተደረሰውን ስምምነት የኮነነው ወታደራዊ መንግሥት፣ ስምምነቱን ማቋረጡን አስታውቋል፡፡
ቡርኪና ፋሶ ራሷን መከላከል እንደምትችል የመንግሥት ቃል አቀባይ ኢማኑኤል ኦድራኦጎ ተናግረው፣ ሁለቱ አገሮች በአገሪቱ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት በገቡት ስምምነት መሠረት የገቡ የፈረንሣይ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ መወሰናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከአልቃይዳና አይኤስአይኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች በርካታ የቡርኪናፋሶ መሬቶችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
የፈረንሣይ መንግሥት እነዚህን ቡድኖች ለመዋጋት ከቡርኪና ፋሶ ጋር ስምምነት ገብቶ ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ቢያስታውቅም፣ መንግሥቱ ከፈረንሣይ ጋር የገባውን ስምምነት ቢያግድም የቁሳቁስ ዕርዳታ እንደሚፈልግ ግን አልሸሸገም፡፡
ፈረንሣይ 2,000 የልዩ ኃይል ወታደሮችን በቡርኪና ፋሶ ያሰፈረች ሲሆን፣ የሚመሩትም በቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግሥት ነው፡፡ ሆኖም ከጥቂት ወራት ወዲህ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት መሻከሩና ውጥረቱ እያየለ መምጣቱ የአገሮቹን ግንኙነት አላልቶታል፡፡
‹‹የፈረንሣይ ወታደሮች በቡርኪና ፋሶ እንዲሆኑ የተደረሰውን ስምምነት አቋርጠናል፤›› ያሉት ኦድራኦጎ፣ ወታደራዊ ድጋፍ ላይ የነበረው ስምምነት መቋረጥ በአገሮቹ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አብቅቷል ማለት እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
አገሪቱን የሚመራው ወታደራዊ መንግሥትና ሁሉም ዜጋ ድንበር የማስከበር ሥራው ቀዳሚ ተዋንያን መሆን ይፈልጋሉም ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በፈረንሣይና በማሊ መካከል የነበረው ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ፣ በማሊ የነበሩ የፈረንሣይ ወታደሮች ማሊን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ቡርኪና ፋሶንና ማሊ በወታደራዊ መንግሥት የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የሁለቱም አገሮች መሪዎች ወደሥልጣን የወጡት በኃይል ነበር፡፡ አመጣጣቸውም በየአገሮቹ ያለውን የደኅንነት ሥጋት እንቀርፋለን ብለው ነው፡፡
ዓምና በመስከረም የቡርኪና ፋሶ አስተዳደር በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ከወደቀ በኋላ ፈረንሣይን የሚቃወሙ በርካታ ሠልፎች ተደርገዋል፡፡ በተቃውሞውም በቡርኪና ፋሶ የፈረንሣይ አምባሳደርና የፈረንሣይ ወታደሮች ከአገሪቱ ይውጡ የሚለው ቀዳሚ አጀንዳ ነበር፡፡ በተቃውሞው በቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ የሚገኘው የፈረንሣይ የባህል ማዕከል ጥቃት ተፈጽሞባት እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ቡርኪና ፋሶም ሆነች ማሊ ከፈረንሣይ ጋር ያላቸውን ወታደራዊ ግንኙነት ቢያቋርጡም፣ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ነው፡፡ ቡርኪና ፋሶ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር እንደምትፈልግ ሩሲያን መምረጥዋም አዋጭ እንደሆነ ማስታወቋም አይዘነጋም፡፡
ፈረንሣይ በማሊም ሆነ በቡርኪና ፋሶ ላይ የነበራት ተፅዕኖ እየመነመነ ቢመጣም፣ ለዚህ ተወቃሽ የምታደርገው ሩሲያን ነው፡፡ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንደሚሉትም፣ ሩሲያ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ላይ የራሷን ፍላጎት ለማስፈጸም ተፅዕኖ እያሳረፈች ትገኛለች፡፡
የፈረንሣይ ወታደሮች ከማሊ ሲለቁ፣ የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት በአገሪቱ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት ከሩሲያ ጋር ለመሥራት መወሰኑን ፈረንሣይም ሆነች ምዕራባውያን አገሮች አይፈልጉም፡፡ ሆኖም ከአገሪቱ በኩል የተሰጠ ምላሽ ባይኖርም ማሊ ብቻ ሳትሆን ቡርኪና ፋሶም ከሩሲያ ጋር ለመሥራት ወስናለች፡፡
ፈረንሣይና አሜሪካ በእነዚህ የአፍሪካ አገሮች ወታደራዊ ካምፖች ያላቸው ሲሆን፣ ጀርመን ደግሞ የሎጂስቲክስ ካምፕ አላት፡፡