ከአዲስ አበባ ተነስተን ካይሮ፣ ግብፅ አንድ ቀን አድረን፣ በማግስቱ ለንደን ከተማ ገባን። ከዚያም ተነስተን፣ በባቡር ወደ ምሥራቅ እንግሊዝ ሂቺን (Hitchin) ወደምትባል ከተማ ተጓዝን። ትምህርት ቤት ስንደርስ፣ ሞግዚቶቹና መምህራኑ መስተንግዶ አደረጉልን። አድረን ስንነሳ፣ ትምህርት ቤቱ የተሞላው በነጮች ነበር። ምንም እንኳ ሳንድፈርድ ትምህርት ቤት ከብዙ የውጭ አገር ልጆች ጋር የተማርኩ ቢሆንም፣ የነጮቹ ብዛት ግራ አጋባኝ። ጥሩነቱ፣ ታላቅ ወንድሜና ሁለት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስለነበሩ፣ እነሱ መከታ ሆነውኝ፣ አዲሱ ኑሮዬን መለማመድ ጀመርኩ።
ትምህርት ቤቱ በምኑም፣ በምኑም፣ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የሚለይ ስላልነበረ፣ ብዙም መናገር አልችልም፡፡ ሆኖም፣ አንድ ሁለት ትዝታዎች አሉኝ። ትምህርት ቤታችን ኖሪች (Norwich) በምትባል ከተማ አጠገብ ስለነበረችና በዚያችም ከተማ በጣም የቆየና የታወቀ የፕሮቴስታንት ካቴድራል በመኖሩ፣ በወቅቱ የነበሩት የእንግሊዝ ንጉሥና ቤተሰቦቻቸው በበዓል ቀን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ፣ ሳንድሪንግሀም (Sandringham) ከሚባለው የርስት ቦታቸው እየመጡ ያስቀድሱ ነበር። በዚያን ወቅት አካዴሚው ውስጥ የሚገኙ ዲያቆናት ተማሪዎች፣ በቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ተራ በተራ ይካፈሉ ነበር።
በዚያን ዓመት የኛ ትምህርት ቤት ተራ ስለነበር፣ ወንድሜ ይስሐቅ ክፍሌ፣ አንድ ትልቅ የቅዳሴ መስቀል ይዞ፣ ነጭና ጥቁር የዲያቆን ልብሰ ተክህኖ ለብሶ፣ ሌሎች ዲያቆናትን ከኋላው አስከትሎ፣ ንጉሣዊ ቤተሰቦቹን ከዐውደ ምሕረቱ እስከ ክብር መቀመጫቸው ድረስ ሲመራቸው በማድነቄና ምናልባትም በልጅነት አእምሮዬ፣ ‹‹እኔም አንድ ቀን እንደዚሁ ንጉሡን እና ቤተሰቦቻቸውን እመራ ይሆናል›› የሚል ፍላጎት አድሮብኝ ይመስለኛል፣ ያቺ ቀን እና ሥነ ሥርዓት አንጎሌ ውስጥ ተቀርጻ እስከ ዛሬ አስታውሳታለሁ።
በዚያኑ ዓመት፣ እ.ኤ.አ. በ1952 ንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛው አርፈው፣ አስከሬናቸው ከሳንድሪንግሀም ወደ ለንደን ሲወሰድ፣ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰልፈን ስንሸኝ ትዝ ይለኛል። ሌላው የማስታውሰው ነገር፣ ቢስክሌት ተገዝቶ እንደተሰጠኝ ለመጋለብ ቸኩዬ ስለነበር፣ ኮርቻውን በቁመቴ ልክ ሳላስተካክል ለመንዳት ስሞክር፣ አበባ ተክል ውስጥ ሄጄ ወደቅሁ። እዚያ አካባቢ የነበሩ ነጭ የእንግሊዝ ተማሪዎች ከበውኝ እየሳቁ፣ ‹‹ቢስክሌት አይተህ ታውቃለህ? የት ነበር የምትኖረው? ጫካ ውስጥ ነበር? ቤትህስ ዛፍ ላይ ነበር?›› ብለው መሳቂያ እንዳደረጉኝ አስታውሳለሁ።
አንድ ሌላ የማስታውሰው፣ ክፍል ውስጥ ስንማር፣ ከጎኔ ከተቀመጠው ተማሪ ጋር በክብሪት ስንጫወት ተያዝን። ከዚያም ተከሰስንና ወደ ርእሰ መምህሩ ቢሮ ተጠራን። በእንግሊዝ ትምህርት ቤት ልምድና ደንብ መሠረት፣ አራት ጊዜ መቀመጫችን ላይ እንድንገረፍ ተፈረደብን። ቄሱ ዶ/ር ፓት ከገረፉኝ በኋላ፣ ‹‹የገረፍኩህ በጥላቻ ሳይሆን እንደገና እንዳታጠፋ ትምህርት እንዲሆንህ ነው፤›› ብለው አስቀምጠው አባበሉኝ።
- ‹‹ሳይቀድመኝ ብቀድመው››- የዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ የሕይወት ታሪክ