Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ የምታደርገው ድጋፍ ግልጽነት እንደሚጎድለው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአፍሪካ አገሮች የቻይናን ብድር ሥልጣናቸው ለማቆየት እየተጠቀሙበት ነው ተባለ

ቻይና ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የምታደርገው ድጋፍ ግልጽነት እንደሚጎድለው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ትናንት ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል ባዘጋጀው ሴሚናር ላይ ከኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ቻይናና ኖርዌይ የተወጣጡ የጥናት ባለሙያዎች ግኝታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ቻይና በአፍሪካ ላይ ፈሰስ ያደረገችው ዕርዳታና ብድር ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የቻይና ድጋፍ ለአፍሪካ አገሮች እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ ጥናታቸውን ያቀረቡት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ኢሊንግ ትጆላንድ እንደተናገሩት ቻይና ከፍተኛ ወለድ ያላቸው ብድሮች፣ ቀጥተኛ የዕርዳታ ድጋፍና ከወለድ ነፃ ብድር ማቅረቧ ለአፍሪካ ትልቅ ዕድል ቢሆንም የአፍሪካ አገሮች የብድር ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

ቻይና ለአፍሪካ አገሮች የምታደርገው የፋይናንስ ድጋፍ ግልጽ አለመሆኑ ለሙስናና ለብክነት ገንዘቡን ተጋላጭ እንዳደረገው በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ተበዳሪ የአፍሪካ አገሮች የብድር ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

በሴሚናሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኖርዌይ ኢንተርናሽናል አፌርስ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ሐንስ ጃርገን እንደተናገሩት ምንም እንኳን የቻይና ፋይናንስ ድጋፍ መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ ትልቅ ሚና ቢጫወትም ግልጽ ባለመሆኑ እንደ ሞዛምቢክ ባሉ አገሮች ከብድር ጫና ባለፈ ለሙስናና ለድህነት መስፋፋት አንድ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሴሚናሩ ላይ የተሳተፉ ዩ ያንግ የተባሉ በቻይና ሻንጋይ ፉዳን ዩኒቨርስቲ ምሁር በበኩላቸው ቻይና አፍሪካን የምትመለከተው እንደ አንድ ወሳኝ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አጋር እንደሆነና ያለ ምንም አድሎ በአኅጉሪቷ ፈሰስ ያደረገችው የፋይናንስ ድጋፍ ንግድ ከማነቃቃት ባለፈ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭና የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም ያሉ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ሲሉ ምሁሩ ሞግተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. 2021 በአፍሪካና በቻይና መካከል የተደረገው የንግድ ልውውጥ በታሪክ ትልቁ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በሁለቱ መካከል ያለው ንግድ ሲተመን ከሩብ ትሪሊዮን ዶላር በላይ በመሆን ተመዝግቧል፡፡ የአፍሪካ አገሮች በድምሩ 100 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጉ ምርቶችን ወደ ቻይና ልከዋል፡፡ ቻይና በበኩላ ወደ አፍሪካ የላከቸው ከ150 ቢሊየን ዶላር በላይ ሲሆን ይህም አኅጉሪቷ ለታላቋ የእስያ አገር ወሳኝ ገበያ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑን በሴሚናሩ ላይ ተገልጿል፡፡

በሴሚናሩ ላይ ጥናታቸውን ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ ያፈሰሱት ኢንቨስትመንት የአምራች ዘርፉ እንዲያድግና ሥራ ዕድል እንዲፈጠር በር ቢከፍትም ድህነትን ከመቀነስ አኳያ ያመጣው ለውጥ እምብዛም ነው ብለዋል፡፡ አፍሪካ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች የግብርና ምርቶች መሆኑን ያስታወሱት ዓለማየሁ (ዶ/ር) ቻይና ደግሞ ወደ አፍሪካ የምትልካቸው ምርቶች ጥራታቸው የጎደለ ርካሽ ምርቶች በመሆናቸው በአኅጉሪቷ ላሉ አምራቾች የዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የአፍሪካ መንግሥታት ከቻይና ጋር ያላቸው ግንኙነት በመርሕ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ያሉት የኢኮኖሚክስ ምሁሩ የመደራደር አቅማቸውን በማሳደግ ግልጽ የሆነ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በቻይና ድጋፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም ጠቃሚነታቸው በሚገባ ሊጤን እንደሚገባም ዓለማየሁ (ዶ/ር) አውስተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች