Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ልዩ ኃይልና በፌዴራል ፖሊስ ላይ በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት 36 የፀጥታ አስከባሪዎች...

በአማራ ልዩ ኃይልና በፌዴራል ፖሊስ ላይ በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት 36 የፀጥታ አስከባሪዎች መገደላቸው ተሰማ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ጀውኃ ቀበሌ በነበረ የልዩ ኃይል ካምፕ ላይ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት፣ 28 የክልሉ ልዩ ኃይልና ስድስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

በጥቃቱ የጀውኃ ቀበሌ አስተዳዳሪና ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁኃን እንደተገደሉ፣ እንዲሁም ከ30 በላይ የልዩ ኃይል አባላት መቁሰላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው በአሸባሪነት በተፈረጀው ሸኔ ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቡ ውስጥ ተሰግስገው የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡና የግል ፍላጎታቸውን ለማራመድ ያሰቡ አካላት በጋራ በመሆን ነው ሲሉም አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከጥቃቱ በኋላ ጥር 14 ቀን በአካባቢው አንፃራዊ መረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ  ከትናንት በስቲያ ጥር 15 ቀን የጥፋት ቡድኑ ሰንበቴ ከተማ ላይ በከፈተው ተኩስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ንፁኃንና የልዩ ኃይል አባላት ተገድለዋል፤›› ሲሉ አቶ መሐመድ አክለዋል፡፡

ጥቃቱን የፈጸሙት የተደራጁ ኃይሎች ናቸው ያሉት ደግሞ፣ የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ቢያሳዝን ናቸው፡፡

አጣዬ ከተማን ጨምሮ ኤፍራታና ግድም ወረዎች ከዚህ በፊትም በጥፋት ኃይሎቹ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት ያስታወሱት አቶ ችሮታው፣ ‹‹አሁንም እነዚህ አጥፊዎች ከተሞችንና የገጠር ቀበሌውን ለመውረርና ለማቃጠል የመጡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ችሮታው ከዚህ በፊት በጅሌና ጥሙጋ አካባቢዎች በነበረው የወገን ኃይል ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ተቀላቅለው እንደነበር  አውስተው፣ ‹‹መንግሥት ልዩ ኦፕሬሽን አድርጎ ያጥራልን ብለን በተደጋጋሚ የተናገርን ቢሆንም፣ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመሰጠቱ በዚሁ ኃይል ውስጥ ተሰግስገው የነበሩ ሸኔዎችና ተከታዮቻቸው ጥቃት አድርሰውብናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹መንግሥት እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ከኅብረተሰቡ ለይቶ እንዲያወጣልን በተለያዩ ሚዲያዎች ጭምር ተናግረናል፤›› ሲሉ አስተዳዳሪው አክለው ገልጸዋል፡፡

በጅሌ ጥሙጋና መሰል አካባቢዎች በሚገኙ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀላቅለው ያሉ የሸኔ አባላት ኅብረተሰቡን ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡

‹‹አሁንም ቢሆን የእኛ ጥያቄ›› ያሉት አቶ ችሮታው፣ ‹‹መንግሥት በኦሮሞ ኅብረተሰብ ውስጥ የተሰገሰጉ የጥፋት ኃይሎችን መለየት ይኖርበታል፤›› ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኤፍራታና ግድም ወረዳ ኩሪብሪ በተባለ ቀበሌ ብቻ ሰኞ ጥር 15 ቀን ከ35 በላይ መኖሪያ ቤቶች በእሳት እንደጋዩ በቦታው ‹‹ተገኝቼ ዓይቻለሁ›› ያሉት አቶ ምንአሉህ ከበደ፣ የኩሪብሪ ቀበሌ የሰው ኃይል አስተባባሪ ናቸው፡፡

በቃጠሎውም ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን አክለው ገልጸዋል፡፡ ከሞርታር እስከ ድሽቃ የታጠቀው ሸኔ ቡድን በንፁኃን ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነ አስተባባሪው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኤፍራታና ግድም ወረዳን ይዞ ወደ አጣዬ፣ እንዲሁም ከባልጭ ወደ ሸዋሮቢት ያለውን የአስፋልት መንገድ በመዝጋት ወደ ሰንበቴና አካባቢው ምንም ዓይነት የመንግሥት ኃይል እንዳያልፍ አድርገው እንደዋሉና ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በቁጥጥራቸው ሥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በግጭቱ ቀጣና ውስጥ ያለው ኅብረተሰብ በሸኔና በፈጠራቸው ጀሌዎች ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ የተፈጸመበት በመሆኑ፣ አሁን ከፊሉ ኅብረተሰብ ወደ አጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች በመሸሽ ላይ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በተለይም ከፌዴራል መንግሥትና ከሕወሓት የሰላም ስምምነት በኋላ ተጠናክሮ የነበረው ወጣቱን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ፣ አሁን የጥቃት ተጋላጭ እንድንሆን አድርጎናል፤›› ሲሉ አቶ ምንአሉህ ተናግረዋል፡፡

በጀውኃ የልዩ ኃይል ካምፕ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ከደረሰው የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት በተጨማሪ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ የዞኑ ሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...