Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ሲሆኑ፣ መቀራረብ የሚችሉት ለአገር ልማትና ዕድገት ለመተባበር ነው፡፡ አንደኛው ሃይማኖት በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ መግባት የማይችል ከመሆኑም በላይ፣ አሉታዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም ሕግ አይፈቅድለትም፡፡ ሃይማኖቶች በውስጣቸው ችግር ሲያጋጥማቸው በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱት ከማድረግ ውጪ፣ አንዱን ወገን ደግፎ ሌላውን ማጣጣል ወይም ማሳጣት ለማንም የተፈቀደ አይደለም፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሹማምንት፣ ፖለቲከኞች፣ የማይመለከታቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የፖለቲካ ጣጣቸውን ተሸክመው ሃይማኖቶችን መጠጋት አይኖርባቸውም፡፡ በሌሎች እምነቶች ውስጥ ያሉ መሪዎችም ሆኑ ምዕመናን ከአሉታዊ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ሲባል፣ ከምንም ነገር በላይ በሕግና በሥርዓት አብሮ የመኖርን ፋይዳ ለማሳየት ነው፡፡ የፖለቲካው መንደር ውስጥ የሚውረገረጉ ግለሰቦች ሃይማኖትና ፖለቲካን እየቀላቀሉ የሚፈጥሩት ትርምስ፣ አንዴ ከተቀጣጠለ ሊቆም የማይችል ሰደድ እሳት እንደሚፈጥር መገንዘብ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የተረጋጋ ምኅዳር እንዲፈጠር የሚሹ ቁጥራቸው ቢልቅም፣ በጥቂት ይሉኝታ ቢሶች ምክንያት ግን የሚፈለገውን ሰላም ለማስፈን እየተቻለ አይደለም፡፡ አንድ ችግር ተከስቶ በስንት መከራ ከዚያ አረንቋ ውስጥ ሲወጣ፣ ወዲያው ያኛውን የሚያስንቅ ሌላ ውጥንቅጥቅ ይፈጠራል፡፡ ፖለቲከኞች አለመግባባታቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት አቅቷቸው ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከዳረጉ በኋላ በውጭ ኃይሎች አሸማጋይነት አንፃራዊ ሰላም ፈጥረው አረፍ ሲሉ፣ በእምነትና በተለያዩ መስኮች ውስጥ ያደፈጡ ድንገት ይነሱና አገር ማተራመስ ይጀምራሉ፡፡ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ አማራጮችና ዘዴዎች ባሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ጥቂቶች የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ድርጊት ሲፈጽሙ ዝም የሚባልበት ምክንያት ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ በሰላም አትኑሪ ተብሎ የተፈረደባት ይመስል፣ ጥቂቶች በንፁኃን ሕይወትና በአገር ህልውና ላይ እንዲቀልዱ መፍቀድ አይገባም፡፡ ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈን እያቃተ በእሳት ለመጫወት መሞከር መዘዙ የከፋ ነው፡፡

በዚህ ዘመን በርካታ አወዛጋቢና አስተዛዛቢ ድርጊቶች ተምረዋል፣ ነቅተዋል፣ ማኅበረሰቡን ቀድመዋል፣ ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ዕውቀት ሸክፈዋል፣ ወዘተ በሚባሉ ግለሰቦችና ስብስቦች ሲፈጸሙ ማስተዋል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ በሽታ ለአገር ዋልታና ማገር ይሆናሉ የሚባሉ አዛውንት ልሂቃንንና የእምነት መሪዎችን ሲያዳርስ ግን ለምን ካልተባለ ማቆሚያው ይቸግራል፡፡ በተለይ በሃይማኖቶች አካባቢ የተሰማሩም ሆኑ እስከ አመራር ደረጃ የደረሱ ግለሰቦች ለአገር ሰላም፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለመጪው ትውልድ ጭምር የሚያስብ ልቦና አጥተው ሰላም አደፍራሽ ሲሆኑ በግራም ሆነ በቀኝ ተቆጪና ገሳጭ ያስፈልጋል፡፡ የማይነኩ ነገሮችን እየነካኩ የአገር ህልውናን የሚፈታተኑ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ በአያገባኝም ስሜት ፊትን ማዞርም ሆነ ለችግሩ ጀርባ መስጠት አያዋጣም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ ችግሩ ከእምነት ጉድኝትና ከዕሳቤ ዓውድ ውጪ አገር የሚያጠፋ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ ሴረኞች የሚፈልጉት በዚህም በዚያ ብለው ዓላማቸውን ማሳካት ስለሆነ፣ የሚጭሩት እሳት ግን ለትውልድ እንደሚተላለፍ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ለአገር ህልውና መቀጠል የራሳቸው አስተዋፅኦ ያላቸው የእምነት ተቋማት ሲነኩ፣ ችግሩን ከራስ አርቆ የሌሎች አድርጎ መመልከት ይዞት የሚመጣው ጦስ ለሁሉም ይተርፋል፡፡ የአንድ እምነት ተቋም ህልውና፣ ክብርና ሥርዓት ተጥሶ አላስፈላጊ ድርጊት ሲፈጸም ከአገር ዘላቂ ሰላም አኳያ ድርጊቱ እንዲቆም ሁሉም ሊተባበር ይገባል፡፡ መንግሥት ደግሞ በእምነት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ሳይገባ በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሕገወጥ ድርጊቱ እንዲገታ ማድረግ አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ታላቅና ምጡቅ ማንነት እንዲገነቡ ካደረጉ ዓበይት ማዕከላት መካከል ሃይማኖቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሰዎች ውጥንቅጥ የበዛበት ዓለማዊ ሕይወታቸው ውስጥ ተዘፍቀው ቀርተው እንስሳዊ ባህሪ እንዳይጫናቸው፣ ቤተ እምነቶች የተጫወቱትን ሚና ያህል በዚህ አገር ውስጥ አለ ለማለት ይቸግራል፡፡ በኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን እንደሚሆን ከሚገመተው ሕዝብ ውስጥ አብዛኛው በሁለቱ ትልልቅ ቤተ እምነቶች የተጠለለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አደገኛ ችግር ውስጥ በገባችበት ጊዜ ሁሉ ዜጎች ራሳቸውን ከአጥፊ ድርጊቶች አርቀው አገራቸውን እንዲታደጉ ማድረግ አስችለዋል፡፡ ለዚህም ነው ሃይማኖቶችን በፖለቲካ ግርዶሽ መነካካት የማይቆም እሳት ያስነሳል የሚባለው፡፡

ዘወትር እንደምንለው ማንም ከአገር በላይ አይደለም፡፡ የራሱንና የቡድኑን ጥቅም ብቻ እያሰላ የአገር ሰላም የሚያደፈርስ በሕግ መጠየቅ አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ለአገር ህልውና ደንታ የሌላቸው በቆሰቆሱት ግጭት በርካቶች ተገድለዋል፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፣ በተፈጸመባቸው ግፍ አካላቸው ብቻ ሳይሆን አዕምሮአቸው ጭምር ተጎድቷል፡፡ የአጠቃላይ ሕዝቡን ሕይወት ሊቀይር የሚችል ከፍተኛ ሀብት ወድሟል፡፡ በአንድ ወቅት በጥቂቶች ዕብሪትና ጥጋብ ምክንያት ከተሞች ሳይቀሩ በእሳት ጋይተው ቤተ እምነቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና የግልና የመንግሥት ንብረቶችና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ውድመቶች የደረሱት ጥቂት ጥጋበኞች ባስነሱት ሁከት እንደነበረ አይረሳም፡፡ በመቀጠል ለሁለት ዓመታት ያህል በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰው ዕልቂትና ውድመት መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ምክንያቱ ምንድነው ሲባል ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ጥቂቶች እንዳሻቸው በመፈንጨታቸው ነው፡፡ ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ሰላም ሲፀልይ፣ ሲማስንና የሚፈለግበትን ሁሉ ያለ ስስት ሲያደርግ ጥቂቶች ግን ከልካይ እያጡ አገር እናጥፋ እያሉ ነው፡፡

እምነት የማንነትን ያህል በሚከበርባት ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ሌላውን አክብሮ ዘመናትን መሻገር መቻሉ አስደናቂ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አኩሪና አስደማሚ የጋራ ማኅበራዊ እሴት ሊገነባ የቻለው እንደ ዋዛ አይደለም፡፡ ከዚህ አኩሪ የጋራ እሴት በስተጀርባ ፈሪኃ ፈጣሪ፣ አርቆ አሳቢነት፣ ጨዋነት፣ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ ይሉኝታና የአገር ፍቅር ስሜት አሉ፡፡ እስላም ክርስቲያኑ ተጋብተውና ተዋልደው አብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ በውስጧ የያዘቻቸው አስገራሚ መስተጋብሮች አሉ፡፡ እነዚህ መስተጋብሮች ሕግ አክባሪነትን፣ አገር ወዳድነትን፣ ከእኔ በፊት ለወንድሜ ለእህቴ ማለትን፣ አዛውንት አክባሪነትን፣ በሽምግልና ሥርዓት መዳኘትንና የመሳሰሉትን አስተሳስረው የያዙ ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ ግዙፍ ማኅበራዊ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ጥጋበኞች አገር ሲያምሱ፣ እንደ ጥንቱ እንደ ጠዋቱ በአንድነት ቆሞ አይቻልም ማለት የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተግባር መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ከአገር በላይ እንሁን እያሉ የሚያምሷትን ማስቆም ይገባል፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልምና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...