Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሁለት ዓመታት በፊት የተሻሻለው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ እንደገና ተሻሽሎ ፓርላማ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየካቲት 2012 ዓ.ም. በማምረቻ፣ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ እንዲሁም ዕቃዎች ወደ አገር ሲገቡ የሚሰበስበውን የጉምሩክ ጣቢያ ታክስ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትና በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶችን ለመቀነስ በሚል ተሻሽሎ ወደ ሥራ የገባው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ፣ እንደገና ተሻሽሎ ለፓላርማው ቀረበ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ከዚህ በፊት ተሻሽሎ ወደ ሥራ የገባው አዋጅ ያስገኘውን ጠቀሜታ፣ እንዲሁም ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ዝርዝር ጥናት  ተደርጓል ይላል፡፡ በዚህም መሠረት አንዳንድ የታክስ ማስከፈያ ምጣኔዎች በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ ጫና ማሳደራቸውንና የተጋነነ የማስከፈያ ምጣኔ ሆኖ በመገኘታቸው ማስተካከያ ማድረግ ማስፈለጉ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ባሉ ሕጎች በተሽከርካሪ ላይ የተጣለው ቀረጥና ታክስ በድምር ሲታይ እንደ ተሽከርካሪው ዓይነት ከ66 በመቶ እስከ 374 በመቶ እንደሚደርስ፣ ነገር ግን በኬንያ ከፍተኛው ምጣኔ 96 በመቶ፣ በሩዋንዳ 71 በመቶ፣ እንዲሁም በጋና 41 በመቶ በመሆኑ በኢትዮጵያ የተጣለው ታክስ ምጣኔ ግን በጣም የተጋነነ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በስራላይ ባለው አዋጅ እስከ 1,300 ሲሲ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተጥሎ የነበረው 30 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ለቀረጥ አከፋፈል እንዲያመች በሚል በዓለም ላይ ያለው የተሽከርካሪ አመዳደብ አራት ስለሆነ፣ በኢትዮጵያ ያለውንም አመዳደብ አራት በማድረግ ከ1,500 ሲሲ በታች፣ 1,501 እስክ 2,500 ሲሲ፣ ከ2,501 እስከ 3,000 ሲሲ፣ እንዲሁም ከ3,000 ሲሲ በላይ በሚል መመደባቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ሆነው ከ1,500 ሲሲ በታች 10 በመቶ፣ ከ1,501 ሲሲ እስከ 2,500 ሲሲ 20 በመቶ፣ ከ2,501 እስከ 3,000 ሲሲ 30 በመቶ፣ እንዲሁም ከ3,000 ሲሲ በላይ የሆኑት 60 በመቶ የኤክሳይ ታክስ እንዲከፈልባቸው በረቂቁ ቀርቧል፡፡

በማሻሻያ ረቂቁ ላይ የተጣለው ቀረጥና ታክስ ድምር እንደ ተሽከርካሪው ዓይነት የሚቀንስ መሆኑን፣ ከ3,000 ሲሲ በላይ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚከፈለው ቀረጥና ታክስ ድምር 121 በመቶ እንዲሆን በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

ከውጭ አገር ባለቀለት ምርት ደረጃ የሚመጡ የአልኮል ምርቶች በመጨረሻ ምርት ብቻ ታክስ የሚከፈልባቸው በመሆኑና የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪ ሊሆኑ ባለመቻላቸው፣ በንፁህ አልኮል ላይ የተጣለው 60 በመቶ ኤክሳይስ ታከስ ወደ አሥር በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

በተመሳሳይ የኤክሳይስ ታክስ የተጣለባቸውን ስኳር የታከለባቸው ምርቶች የሚያመርቱ እንደ ከረሜላ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በስኳር ላይ ከሚከፍሉት የኤክሳይስ ታክስ በተጨማሪ፣ በምርቱ ላይ የሚከፍሉት የኤክሳይስ ታክስ 20 በመቶ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ አሥር በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ባደረገችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት ከተፈቀደው በስተቀር በኢንቨስትመንት ማበረታቻም ሆነ በሌላ ተመሳሳይ ልዩ ፈቃድ የኤክሳይስ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎች ወደ አገር የሚያስገቡ ሰዎች ወይም ድርጅቶች፣ በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ስለሆነ የኤክሳይስ ታክስ እንዲከፍሉ ረቂቁ ደንግጓል፡፡

በዚህም መሠረት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኢንቨስተሮችና የአካል ጉዳተኞ የሚያስመጧቸው ዕቃዎች ከኤክሳይስ ታክስ ነፃ መደረጋቸው በረቂቁ ተቀምጧል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች ላይ የአምስተ በመቶ ኤክሳይስ ታክስ የሚጥል ሲሆን፣ በሌላ በኩል የኤክሳይስ ታክስ ተጥሎባቸው ከነበሩ ምርቶች በተለይም በቪዲዮ ካሜራና በቴሌቪዥን ላይ የተጣለው አሥር በመቶ ታክስ ሙሉ በሙሉ እንዲቀር መደረጉ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች