ለመንገድ ግንባታና ጥገና የሚያገለግለው አስፋልት ገበያ ውስጥ በጨረታም ሆነ በቀጥታ ግዥ ማግኘት ባለመቻሉ ችግሩ እንዲፈታ በፓርላማ ዕገዛ ካልተደረገለት፣ በመጪው አንድ ዓመት ውስጥ የመንገዶች ግንባታ ጥገና ሊቆም እንደሚችል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የፓርላማው የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ገምግሟል፡፡
በአገር ውስጥ ገበያ የጠፋውንና ለመንገድ ግንባታና ጥገና አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጸውን አስፋልት ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደገጠመው በማስታወቅ፣ ይህንን ከፍተኛ ችግር ፓርላማው ተረድቶ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት እንዲያደርግበትና መፍትሔ እንዲሰጥበት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ ወንደሙ ሴታ (ኢንጂነር) ጠይቀዋል፡፡
‹‹የአስፋልት ግዥ ለአራት ጊዜያት ጨረታ ቢወጣም ገበያ ውስጥ ማግኘት ባለመቻሉና ጨረታውን ያሸነፉ አቅራቢዎችም ምርቱን ገዝተው ማቅረብ ስላቃታቸው፣ ውሎችን ለመሰረዝ ተገደናል፤›› ያሉት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ አየለ ናቸው፡፡
ከአገር ውስጥ በሚገኝ ምርት የሚሸፈነው የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት አሁን ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ዘርፉ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን አገራዊ በጀትና ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ የሚጠቀም ቢሆንም የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በ2015 ዓ.ም. 49 የመንገድ ፕሮጀክቶች በፀጥታ ምክንያት እንደቆሙ የተናገሩት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ የቆሙትን ፕሮጀክቶች መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት አብዛኞቹ የሥራ ተቋራጮች ከጅምሩ በፀጥታ ምክንያት ሲቆሙ ንብረቶቻቸው ስለተዘረፉባቸው፣ የተወሰዱ ንብረቶች እንዲመለሱና ካሳ እንዲከፈላቸው እየጠየቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ የመንገድ ከባድ ጥገና ሥራዎች አፈጻጸም፣ በግንባታ ግብዓት እጥረት፣ በፀጥታ ችግር፣ በዋጋ ንረትና በሌሎች ምክንያቶች የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ ስለመሆኑ በምክር ቤቱ ተገምግሟል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ በውጭ አገሮች ድጋፍ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ክፍያ መዘግየት ምክንያት እየተስተጓጎሉ ያሉ ፕሮጅክቶችን ቁጥር ለመጥራት በጣም አስፈሪ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሥራ በገባው የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ፣ በከተሞች የሚታየውን የከተማ ነዋሪዎች የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ልዩነት ለማጥበብ፣ መንግሥት የተለያዩ የቤት አማራጮችን በመጠቀም የታሰበውን አቅርቦት ለማሳካት ወደ 4.5 ሚሊዮን ቤቶች እንደሚገነቡ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ መተግበር ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረውን መሪ ዕቅድ ለማሳካት በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት፣ በመንግሥት በኩል የተከናወነው የቤት ልማት ከዕቅድ በታች መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ለአብነት ሊገነቡ ከታቀዱ 19 ሺሕ ቤቶች ውስጥ 6,900 ቤቶች ብቻ የተገነቡ መሆኑንና በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 የቤት ፕሮግራሞች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ምንም መገንባት አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በመንግሥት አስተባባሪነት ለሚከናወን የቤት ልማት የአምስት ቢሊዮን ብር የቦንድ ብድር ለማቅረብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማቅረብ የተቻለው በግንባታ ላይ ላሉት ብቻ መሆኑንና ለአዳዲስ ቤቶች ገንዘብ ማቅረብ አለመቻሉ ተጠቁሟል፡፡
ለዚህ ከዕቅድ በታች አፈጻጸም ማነስ ዋነኛ ምክንያት የቦንድ ብድርና የፋይናንስ አቅርቦት አለመገኘት እንደሆነ ወ/ሮ ጫልቱ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በመንግሥትና የግል አጋርነት የሽርክና ፕሮግራም የቤቶችን ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የግልና የመንግሥት አጋርነት አዋጅ ተፈጻሚነት፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ብቻ በመሆኑ ምንም ዓይነት ግንባታ አለመካሄዱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ፓርላማው አዋጁ በድጋሚ እንዲታይና በሌሎች አካባቢዎች ተፈጻሚ የሚሆንበት መንገድ እዲፈጠር ዕገዛ ያድርግልን፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት በ10/90፣ በ20/80፣ በ40/60 በመንግሥት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከ22 ሺሕ በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ምንም ዓይነት ግንባታ ማካሄድ እንዳልቻለ አስታውቆ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ እስካሁን ከ700 ሺሕ በላይ ዜጎች ተመዝግበው ቤት እየተጠባበቁ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ እየገነባቸው ያሉትን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሕንፃ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሕንፃ፣ የውጭ ጉዳይ ዋና መሥሪያ ቤት የቢሮ ሕንፃ፣ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ሕንፃ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ሁለት ሕንፃዎች አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት፣ የአማካሪና የሥራ ተቋራጭ አቅም ውስንነት፣ በቂ በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ አለመለቀቅ፣ የሕንፃ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች የዋጋ ንረትና በገበያ ውስጥ አለመገኘትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል፡፡