Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹በይቅርታና በዕርቅ ጥበብ ሁሉንም ወደ ነበረው እንመልስ›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ...

‹‹በይቅርታና በዕርቅ ጥበብ ሁሉንም ወደ ነበረው እንመልስ›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

ቀን:

‹‹ካሁን በፊት የሆነው ሁሉ ሆኖአል፤ አሁን ግን የኅዙናንን ዓይን የምናብስበት፣ ተስፋ የቆረጠችውን ልብ የምናለመልምበት፣ የተሰበረውንና የፈረሰውን የምንጠግንበት፣ የተጣመመውን የምናቃናበት፣ ያዘነውንና የተጐሳቆለውን የምናጽናናበት፣ ሰላማችንንና አንድነታችንን እንደገና በፍትሕና በእኩልነት የምንገነባበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡››

 ይህን ኃይለ ቃል ያስተጋቡት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ሲከበር ተገኝተው ቡራኬ የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡

በሃያ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ሌሎች ታዳሚያን በተገኙበት በተከበረው የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ቅዱስ ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን አስከፊ ገጽታ በሚከተለው መልኩ ነው የገለጹት፡-

‹‹እኛ እስካሁን የሄድንበት መንገድ ከእግዚአብሔር ቃል በእጅጉ የራቀ ሆኖ ተገኝቶአል፤ እግዚአብሔር በአእምሮአችን ውስጥ የተዘጋጀና የተስተካከለ መንገድ እንዳይኖረው በማድረግም በእጅጉ በድለናል፤ አእምሮአችንን ለሱ መመላለሻ ይሆን ዘንድ በማዘጋጀትና በማስተካከል ፈንታ፣ ጠመዝማዛና ጠማማ፣ ሸካራና ጐርበጥባጣ በማድረግም፣ የእልክ፣ የክፋት የራስ ወዳድነት መመላለሻ አድርገነዋል፡፡››

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ለአስከፊው ገጽታ መፍትሔውንም ያሳዩት ‹‹አሁን ሁሉም ይብቃንና በእውነት ንሥሐ እንግባ፤ በይቅርታና በዕርቅ ጥበብ ሁሉንም ወደ ነበረው እንመልስ ‹ዕርቅ ደም ያደርቅ› የሚለውን ሃይማኖታዊ አባባላችንን ያለማመንታት ተግባር ላይ እናውል፤ ይህ ሲሆን አእምሮአችን የእግዚአብሔር መመላለሻና መንበረ መንግሥት ይሆናል፤ ይህንን ዓይነት ግብረ መልስ ባለመስጠታችን ሕዝባችን ተጐድቶአል፤›› በማለት ነው፡፡ ለዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በቅንነት፣ በአርቆ አስተዋይነትና በወንድማዊ ፍቅር የእግዚአብሔርን ቃል በፍጹም ታዛዥነት ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ ከአደራ ጭምር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓሉ ክብሩ ተጠብቆ በሰላምና በፍቅር እንዲከበር ላደረጉ ሕዝበ ክርስቲያን ካህናትና ወጣቶች በተለይም የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባና ሁሉም የፀጥታ አካላት ላደረጉት የላቀ ትብብርና አስተዋጽኦ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ምስጋናን አቅርበዋል፡፡

አብሮነትን በማጠናከር አንድነትን ለማስቀጠል የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት መላበስ እንደሚያስፈልግም በክብረ በዓሉ ላይ የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያንን ደስታና ሰላም ለማጽናት፣ አብሮነትን ለማጠንከር፣ ፍቅርና አንድነትን ለማጽናት የጥምቀት በዓል አከባበር አንዱ እሴት መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ክብረ በዓሉ ከአዲስ አበባ ባሻገር ዓምናና ሃቻምና ሰላም ርቋቸው የነበሩት አክሱም፣ መቐለ፣ ማይጨው፣ ውቕሮና ዓዲግራትን ጨምሮ፤ በደብረ ብርሃን፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ምንጃር ሸንኮራ (ኢራንቡቲ)፣ ጋምቤላና በተለያዩ ከተሞች የየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተከብሮ ውሏል፡፡

‹‹ኤጲፋንያ››  የጥምቀት  ክብረ በዓል ሲገለጽ

መምህራኑ እንደሚያብራሩት፣ ኤጲፋኒያ በግሪክ ቋንቋ መገለጥ (ዘመነ አስተርእዮ) ማለት ሲሆን፣ ይህም እግዚእ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጾበታል።

ልደት (ገና) በተከበረ በ12ኛው ቀን፣ በዓለ ጥምቀቱን በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ያሉ የኦርቶዶክስና ካቶሊክ ክርስቲያኖች ያከብሩታል፡፡ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥር 11 ቀን (በጁሊያን ቀመር ጃንዋሪ 6 ብለው) ሲያከብሩ፣ ግሪጎሪያን ካላንደርን የሚከተሉት ‹‹ጃንዋሪ 6›› ብለው ያከበሩት ከ13 ቀናት በፊት ነው፡፡ 

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት ያስታውሳል፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግሥቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› – ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ -ን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡

ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ (ለዘንድሮ እስከ ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም.) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ‹‹አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምስጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዓምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ›› እየታሰበ ምስጋና ይቀርብበታል።

የአከባበሩ ታሪካዊ ዳራ

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በዓሉን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲገባ፣ ለመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ በላከው ሰነድ ስለክብረ በዓሉ ታሪካዊ ዳራ እንዲህ ጽፏል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጉዞና በአደባባይ ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መሠረት አለው፡፡ ‹‹ጥምቀት ማለት በውኃ ውስጥ መጠመቅ፣ መጥለቅ፣ መንፃት ማለት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል የሚከበረው በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ጥር 11 ሲሆን፣ አከባበሩ የሚጀምረው ከተራ በመባል ከሚታወቀው የዋዜማ ዕለት (ጥር 10) ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹ከተራ›› መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ በጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳርና ውኃ በአለበት አካባቢ ድንኳን ይተክላል ወይም ዳስ ይጥላል፡፡ በየአጥቢያው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታተ ሕጉ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የታቦት ማደሪያ፣ ውኃ የሚከተርበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ሥፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት›› እየተባለ ይጠራል፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ታሪካዊ መሠረቱን ሳይለቅ አሁን እንዳለው መከበር የጀመረው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው ብሔራዊ ሃይማኖት ሲያደርጉ የጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ሲከበር የኖረ ‹‹የበዓለ መጸለት/የዳስ በዓል›› የሚባል ስለነበር ጥምቀት በእሱ ምትክ የጉዞና የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበርም አድርገዋል፡፡

እነዚህ ቅዱሳን ነገሥት ለሃይማኖቱ ማደግ ብቻ ሳይሆን ለበዓሉም መስፋፋት ተግተው ሠርተዋል፡፡ በዓሉ በየዘመኑ እያደገ መጥቶ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ያሬድ በዘመኑ ይፈጸም የነበረውን የበዓሉን አከባበር ሥርዓት በማየት ለበዓሉ አከባበር የሚስማማ የዜማ ሥርዓት አዘጋጅቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለበዓሉ ያዘጋጀው የዜማ ድርሰትም ከበዓሉ ዋዜማ (ከተራ) ጀምሮ የሚፈጸም በመሆኑ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀትንና ሥርዓትን ሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ላሊበላም በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ ዓለም ፈልፍሎ ባነፃቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ውስጥ በዓሉን ሁሉም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት የሚያከብሩበትን ቦታ በዮርዳኖስ ወንዝ ስም ምሳሌነት አካቶ ሠርቶታል፡፡ እስካሁንም ድረስ በላሊበላ ከተማ የሚገኘው ይህ ቦታ ‹‹ዮርዳኖስ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ከዚያ በኋላ የተነሱ ነገሥታት እንደ አፄ ይኩኖ አምላክ (13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) አፄ ዘርዓ ያዕቆብና አፄ ናኦድ (በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ካህናቱና ሕዝቡ ታቦታቱን አጅበው በአንድነት የሚያከብሩትን ይህንን ጥንታዊና መንፈሳዊ በዓል በየዘመናቸው ደምቆ እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይወሳል፡፡

በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በጎንደር የነገሡት አፄ ፋሲል ለመዋኛ ገንዳ ብለው ያሠሩት በሒደት የጥምቀት በዓል ማክበሪያ የተደረገ ሲሆን፣ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ከነገሡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጀምሮ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓሉ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ በሚከበረው በዚህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ መንፈሳዊ መዝሙሮች፣ የተለያየ ስልት ያላቸው ያሬዳዊ ዜማዎች ይደመጣሉ፡፡ በበዓሉ ላይ የየአካባቢው አገረሰባዊ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች በስፋት ይከናወናሉ፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ በዓሉም እነዚህን የትውን ጥበባትና የሥነ ቃል ሀብቶች ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለዩኔስኮ በላከው ሰነድ፡፡ 

ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ካሉት ባህላዊ ገጽታዎች አንዱ በገጠርና በአንዳንድ ከተሞች የእሩር ጨዋታ መካሄዱ ነው፡፡ በዞኑ አስተዳደር ድረ ገጽ ላይ እንደተጻፈው፣ ‹‹ሰይ ሰይ›› የሚባል የጨዋታ ዓይነት ወጣቶች ሲዝናኑበት ይታያሉ፡፡ ጨዋታው በጠብ ወቅት ራስን እንዴት መከላከል እንደሚቻል በሁለት ቡድን መካከል የሚካሄድ ጨዋታ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፈረስ ጉግስ (ግልቢያ) ሥርዓትና ትዕግሥት በተሞላበት መንፈስ በሁለት ወገን (ቡድን) በመከፈል ይካሄዳል፡፡ ጨዋታው የብዙ ሕዝብን ቀልብ የሚስብ ሲሆን ሰውነት ሊጎዱ በማይችሉ ቀጫጭን በትሮችን በመያዝና ፈረስ ላይ ወጥቶ በመጋለብ እያነጣጠሩ በመወርወር ተቃራኒ ቡድንን በመምታት ረዘም ላለ ጊዜ ይካሄዳል፡፡

የጥምቀት በዓል ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበር በመሆኑ፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ በየክፍላተ ሀገሩ ከተማዎችበሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምዕመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በአገራዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው። ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

በብሔራዊ ደረጃ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመዘገበው የጥምቀት ክብረ በዓል፣ በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) የተመዘገበው በታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...