Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የንግድ ግንኙነቶችን ለመፍጠር የሚዘጋጁ የውጭ ጉዞዎች የሽርሽር ፕሮግራም መሆን የለባቸውም!

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን ወደ አገር ቤት መጥተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው፡፡ የአዳዲስ ዲፕሎማቶችም ሹመትም እየተሰጠ ሲሆን፣ የዲፕሎማቶች ሽግሽግ እየተደረገ መሆኑን እየሰማን ነው፡፡ አዲሶቹ ተሿሚዎች ሆኑ ነባሮቹ ዲፕሎማቶች ወደ አገር ቤት ተጠርተው የአገሪቱን የውጭ ግንኙነትን በሚያጠናክሩበት ረገድ ምክክሮች እያካሄዱ ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የተለያዩ የኢንቨስትመንትና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲጎበኙ ማድረግም የፕሮግራሙ አካል ነበር፡፡ ከንግድ ኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው እንዲመክሩ መድረክ ተዘጋጅቶ ተወያይተዋል፡፡ ዲፕሎማቶች እንደ ዋነኛ ተግባራቸው ተደርጎ የሚወሰደው የኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን ማጠናከር በመሆኑ ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር ያካሄዱት የምክክር መድረክ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ ነገር ግን የአስፈላጊነቱን ያህል በቂ ውይይት ተደርጓል ብሎ ለመግለጽ ግን አይቻልም፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ዲፕሎማቶቻችን የኃላፊነት ልክ ኢትዮጵያን በአግባቡ መሸጥና ማስተዋወቅ ነውና የወጪ ንግድን ከማሳደግ አኳያም ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

በእርግጥም የዲፕሎማቶቻችን ዋነኛ ሥራ መሆን ያለበት ኢትዮጵያን በደንብ ማስተዋወቅና መሸጥ ነው፡፡ ዲፕሎማቶቻችን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣትና አለመወጣታቸው ሊመዘን የሚገባውም በዚሁ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ባስገኙት ውጤት መሆን ይገባዋል፡፡ 

አብላጫውን የሥራ ጊዜያቸውን መስጠት ያለባቸውም ለኢትዮጵያ ገበያ ማፈላለግ ዋነኛ ተግባራቸው መሆን አለበት፡፡ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠሩ እስከመጨረሻው ድረስ በመትጋት ለኢትዮጵያ ገበያ መፍጠር ካልቻሉ ሥራቸውን ሠርተዋል ለማለት አይቻልም፡፡ በዚህ  ረገድ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚበጁ ሥራዎች ላይ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሠርተዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሰሞኑን ከንግድ ኅብረተሰቡ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይቶች ላይ በየተመደቡበት አገር ሰፊ ገበያ ቢኖርም እየተጠቀምንበት አይደለም ብለው መግለጻቸው በራሱ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡  በኢትዮጵያ ያሉ ዕድሎችን በሚገባ አስተዋውቆ አዳዲስ ገበያዎችን ለማግኘት ኤምባሲዎቻችን  ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና ከንግዱ ማኅበረሰብ ወኪሎች ተደርገው ከሚወሰዱት የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጋር በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ሰሞኑን የተዘጋጀው ዓይነት የውይይት መድረክ ጠቃሚና ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል የተባለው፡፡

የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ዋነኛ ተልዕኮዎቻቸው በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ረገድ ውጤት ማምጣት ነው ከተባለ ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሥራት ደግሞ መናበብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ግልጽ የሆነ አሠራር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ሥራው የሁለቱንም ወገኖች ጥንካሬ የሚጠይቅም ነው፡፡ አንዳንድ ዲፕሎማቶች በግልጽ እንደተናገሩት ያሉባቸው አገሮች ኢትዮጵያን ሊጠቅሙ የሚችሉ ብዙ ዕድሎች ያሉ ቢሆንም የኢትዮጵያ ንግድ ኅብረተሰብ በአግባቡ እየተጠቀመበት ያለመሆኑን መግለጻቸው በራሱ ተናቦ የመሥራት ችግር ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱ ወገኖች በትብብር መሥራት ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የተደረጉ አንዳድ ጥረቶች አዳዲስ ገበያ ከመፍጠር ባለፈ ጥቂት ቢሆንም የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ሊሠሩ የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት ተችሏል፡፡

ስለዚህ እስካሁን አሉ የተባሉትን ዕድሎች ላለመጠቀማችን አንዱ ምክንያት የንግድ ኅብረተሰቡን አቃፊ ያደረገ የወጪ ንግድ ዕድሎችን በማመቻቸት ረገድ ደካማ የሆኑ አሠራር ስለነበር መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ 

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የንግድ ዕድሎች፣ የንግድ ትርዒቶችና የመሳሰሉ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቶችን የሚስተናገዱበት የውጭ  ጉዞዎች እንዴት ለአገር ይጠቅማሉ ለማለት የተደራጀ አሠራር ፖሊሲ ባለመኖሩ መሆኑ ይታመናል፡፡  

በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ለንግድ ልውውጦችም ሆነ በንግድ ትርዒቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት ጉዳይ አንድ ችግር ነው፡፡ በትክልል ከጉዞው ጥቅም የሚያስገኙ ተመርጠው እንዲጓዙ አይደረግም፡፡

በተለይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የንግድና ቢዝነስ ግንኙነትን ያጠናክራሉ የገበያ ትስስር ይፈጥራል፣ በጋራ ለመሥራት ያስችላሉ የተባሉ የውጭ ጉዞ ዕድሎችን በአግባቡ እየተጠቀሙት ያለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ 

ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲተች የነበረና ለአገር ጥቅም ይሰጣሉ የተባሉ የውጭ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት የጉዞ ዕድሎችን እዚያው ምክር ቤቶቹ ውስጥ ያሉ አመራሮች በመቀራመት ዕድሉ ሲሰነካከል ታይቷል፡፡ በትክክል በዚያ የቢዝነስ ጉዞ ተሳትፎ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ኩባንያ የማይወከል በመሆኑ ብዙ ዕድሎችን ተክተዋልና ይህ እንዳይደገም የሚመለከተው ሁሉ በጋራ ሊሠራበት ይገባል፡፡ 

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በኤምባሲዎቻችን በኩል የሚመጡ የንግድ ግንኙነቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የንግድ ትርዒቶችና መሰል የጉዞ ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ የነበረባቸው የንግዱ ኅብረተሰቡ አካላት ቀርተው ጉዳዩ የማይመለከታቸው አንዳንዴም የንግድ ምክር ቤቱ አባላት  መሆናቸው የሚያጠራጥር ግለሰቦች ሁሉ ይላካሉ፡፡ ያለአግባብ ከሚላኩ ከእነዚህ ግለሰቦች ውስጥም አንዳንዶች በዚያው በሄዱበት አገር የሚቀሩበት አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ መሰማቱ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ንግድ ምክር ቤቶች በዚህ ረገድ የሚታይባቸውን እስካሁንም ያልተቀረፈ ችግሮች ካላረሙ ኤምባሲዎቻችን የቱንም ያህል ቢለፉ የሚፈለገውን ውጤት ላይመጣ እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡

አሁንም ንግድ ምክር ቤቶችና ኤምባሲዎቻችን በጋራ ይሥሩ ከተባለ ኢንቨስትመንትና ንግድን ሊያጠናክሩ ይችላሉ ተብለው የሚሰጡ የንግድ ጉዞዎች ከንግድ ጉዞው ጋር በቀጥታ የሚመለከታቸው የንግዱ ኅብረተሰቡ አካላት እንዲወከሉ ማድረግ ለዚህም ራሱን የቻለ አሠራር መበጀት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በንግድ ጉዞዎች ስም ጥቂቶች የሚንሸራሸሩበት መሆኑ ሳያንስ እንደ አገር የሚጠቀሱ መልካም ዕድሎችን እንዳያሰናክል መደረግ አለበት፡፡ ዲፕሎማቶችን በኢኮኖሚ ዲሎማሲ ረገድ መመዘን ያለባቸው ለኢትዮጵያ ገበያ በመፍጠርና ኢንቨስትመንት በመሳብ ነው ባስገኙት ውጤት ነው እንደምንለው ሁሉ የንግድ ምክር ቤቶችም ከሚያገኙት የውጭ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉዞዎች ምን አስገኙ? መባል ይኖርበታል የንግድ ጉዞዎችም ለሚመለከታቸው መሰጠት አለመሰጠታቸው ገለልተኛ በሆነ አካል ሊመዘን ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት