Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትጣሪያው የሚያፈሰው የዳኝነት ሥርዓታችን

ጣሪያው የሚያፈሰው የዳኝነት ሥርዓታችን

ቀን:

በላቀው በላይ

ከአሁን በፊት ኅዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. (ክፍል አንድ) እና ኅዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም. (ክፍል ሁለት) “የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥና ተግዳሮቶች” የሚል ጽሑፍ ሪፖርተር ጋዜጣ ያስነበበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ ክፍል የዳኝነት ሥርዓታችን ሥርዓታዊ ችግሮችና መፍትሔዎች የሚሉትን በመጠኑ ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ የኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ጣራ የሌለው ወይም ጣራው የሚያፈስ ቤትን የሚመስል ነው፡፡ አንድ ቤት ወለሉና ግድግዳው በጥሩ ሁኔታ ተጠናቆ ለቤት ውስጥ መገልገያ የሆኑ ዕቃዎች፣ የሚበላው የሚጠጣው ሁሉ ቤት ውስጥ ገብቷል እንበል፡፡ ቤተሰቡም ቤቱ ውስጥ ገብቶ መኖር ጀምሯል እንበል፡፡ እንደ አለመታደል ቤቱ ጣራ የለውም ወይም የቤቱ ጣሪያ ያፈሳል እንበል፡፡ ይህ ቤተሰብ የመጀመርያውን ክረምት እንደምንም ሊያልፈው ይችላል፡፡ ቀጣዩን ሁለትና ሦስት ክረምት፣ መጪውን 20 እና 30 ክረምት እንደምን ያልፈዋል? ከዳኝነት ሥርዓታችን አኳያ አሁን የገጠመን ችግር ይህ ቤተሰብ የገጠመው ዓይነት ችግር ነው፡፡ ጣሪያው የሚያፈስ ወይም ጣራ የሌለው ቤት ውስጥ፣ 30 ክረምቶችን ለማሳለፍ የተገደደ ቤተሰብ የገጠመው ችግር በዳኝነት ሥርዓታችን ውስጥም ገጥሞናል ለማለት ይቻላል፡፡

በሥርዓት ደረጃ ጣሪያው የሚያፈስ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖረን ለምን እንደተፈለገ፣ ለምን እንደተደረገ በጥልቅ ጥናት የሚመለስ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ጽሑፍ ደረጃ መጨረሻ ላይ ክርክሮችን ለመቋጨት በሕዝብ የታመነ የዳኝነት አካል አለመኖር፣ እንዲሁም መርህና ተጠያቂነት የሌለበት የዳኝነት ሥርዓት መሥፈን የዳኝነት ሥርዓታችን ዋና ዋና ችግሮች አድርጉ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሀ.መጨረሻ ላይ ክርክሮችን ለመቋጨት የታመነ የዳኝነት ተቋም አለመኖር

የኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ጣሪያ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን፣ የሰበርና የይግባኝ ፍርድ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ በሚያደርገው ማጣራት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ 11 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የጉባዔው ስድስት አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ናቸው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የጉባዔ አባላት ስንመለከት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ከተሾሙት ስድስቱ መካከል ሦስቱ በግል ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ ቀሪ ሦስቱ ደግሞ ሌላ መደበኛ ሥራ ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች ናቸው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ሦስቱ ደግሞ መደበኛ ሥራቸውን በክልሎች የሚያከናውኑ ወይም ግፋ ቢል በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውስጥ ሌላ መደበኛ ሥራ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ሁሉም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት ቋሚ የጉባዔው ሠራተኞች አይደሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት የሚሰባሰቡት፣ እንደ ቡና ጠጭ ተጠራርተውና ሲመቻቸው ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሆን ተብሎም ይሁን ባለመታደል በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ የመጀመርያው ችግር የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸው ነው፡፡ ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሚሄዱ ጉዳዮች ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት በፍርድ ቤቶች የተፈጸሙ የሕገ መንግሥት ጥሰቶች ናቸው፡፡

የሕገ መንግሥት ጥሰቱ የተፈጸመው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት ወይም ሁለቱ በአንድ ላይ ተሰይመው በተሰጠ ፍርድ ነው እንበል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በፍርድ ቤት ሥልጣናቸው ትክክል ነው በሚል በሰጡት ፍርድ ሕገ መንግሥታዊ ስህተት ተፈጽሞበታል ተብሎ ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሲቀርብ፣ የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች የጉባዔው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የራሳቸውን ፍርድ የሕገ መንግሥት ጥሰት ተፈጽሞበታል በሚል ይተቹታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በሌላ በኩል በፍርድ ቤቱ የተሰጡ በርካታ ውሳኔዎች በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ታይተው የሕገ መንግሥት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ተብለው የሕግ ውጤት የላቸውም መባላቸው፣ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ አልተረጎሙም ከሚል መደምደሚያ የሚያደርስና የሚያስወቅሳቸው በመሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የጉባዔው ሰብሳቢ መሆናቸውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው፣ በቅድሚያ ጉባዔው እንዳይሰባሰብ እንቅፋት መፍጠራቸው የማይቀር የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡ ጉባዔው ከተሰበሰበም የፍርድ ቤቱ አመራሮች የጉባዔው ሰብሳቢነታቸውን ተጠቅመው ጉዳዩ በገለልተኝነት እንዳይታይ እንቅፋትና ጫና መፍጠራቸው አይቀርም፡፡

አሁን ያለው ተጨባጩ ሁኔታ የሚያረጋግጥልን ይህንን እውነታ ነው፡፡ ከለውጡ (2010 ዓ.ም.) በኋላ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ለረጅም ጊዜ ሳይሰበሰብ እንዲቆይ መደረጉ፣ አሁን በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተከፈቱ መዝገቦች ወደ ስምንት ሺሕ የተጠጉ ቢሆንም፣ በጉባዔው ታዩ ተብለው በዘፈቀደ የተዘጉ መዝገቦች ከአራት ሺሕ በታች መሆናቸው፣ የጉባዔው ዳኞች ቋሚ የጉባዔው ሠራተኞች ሳይሆኑ ልክ እንደ ቡና ጠጪ በጥሪ የሚሰባሰቡ ተመላላሽ ዳኞች እንዲሆኑ መደረጉ፣ ጉባዔው ሥራውን የሚያከናውንበት ሕንፃ ለፍትሕ አግልግሎት አሰጣጥ ያልተገባና ያልተመቸ እንዲሆን መደረጉና ሌሎችም ሁኔታዎች ጉባዔው በሕገ መንገሥቱ በታሰበው ልክ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ሥራውን በአግባቡ እንዳይሠራ የተፈለገና የተደረገ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡

በቅርቡ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከታዮ 81 መዝገቦች የሕገ መንግሥት ጥሰት የተገኘባቸው ሁለት መዝገቦች ብቻ ናቸው በሚል የተሰጠው የሚዲያ መግለጫ ዋና ግቡ፣ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን አክብረው ሠርተዋል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ የተደረገ ይመስላል፡፡ ሕዝብ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል ብሎ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ቅሬታ ሲያቀርብ፣ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች የአጣሪ ጉባዔውን ካባ ደርበውና በጉዳዩ ላይ ተሰይመው ሕገ መንግሥታዊ መብትህ እኛ በምንመራው ፍርድ ቤት በጭራሽ አልተጣሰብህም ብለው እንዲወስኑበት ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር፡፡ በአጭሩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ሆነው በሕገ መንግሥቱ መሰየማቸው፣ የዳኝነት ሥርዓታችን ቁልፍ ሥርዓታዊ ችግር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ሁለተኛው ቁልፍ ችግር የጉባዔው ሌሎች ዘጠኝ አባላት ቋሚ የጉባዔው ሠራተኞች አለመሆናቸው ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ከተሾሙት ስድስት የጉባዔው አባላት ውስጥ ሦስቱ በግል የጥብቅና ሥራ ከሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ጠበቃና የሕግ አማካሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት የሆኑ ሦስት ጠበቆች በአንድ በኩል የደንበኞቻቸውን ጉዳይ የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ሆኖ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የአገርና የሕዝብ አደራ እንዲሸከሙ ተደርገዋል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላት የሆኑት ሦስቱ ጠበቆች በፍርድ ቤት የያዟቸው ጉዳዮች ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሲደርሱ የሚፈጠረውን የጥቅም ግጭት የእኛ አገር የጉድ አገር፣ የእኛን አገር ጉድ ሆድ ይፍጀው ብለን አልፈነው የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት ከራሱ ሥራ ከሚያገኘው ገቢ የሚመራን ሰው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብና የአገር ኃላፊነት እንዲረከብ ማድረግ ለሕዝብ ጥቅም ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሌሎች የጉባዔው አባላትም ዋና ሥራቸው የጉባዔው ዳኛ ሆኖ መሥራት ሳይሆን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ወይም ኃላፊዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ሆነው የሚሠሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ተጠቃለው ሲታዩ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተቋቋመው የለም ለሚሉ አለ ለማለት፣ አለ ለሚሉት ደግሞ አይሠራም ለማለት ይመስላል፡፡ ከ1943 ዓ.ም. ጀምሮ የተደራጀውንና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኘውን የጀርመን ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት (ይህ ፍርድ ቤት ለኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድነት የተሰጣቸው ኃላፊነት የተሰጠው አካል ነው) ብንወስድ፣ የፍርድ ቤቱ 16 ዳኞች ለ12 ዓመታት ፍርድ ቤቱን በሙሉ ጌዜያቸው በቋሚነት የሚያገለግሉና ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚሆነውን ገቢያቸውንም ከመንግሥት ከሚከፈል ደመወዝ የሚያገኙ ናቸው፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የተሰጠው ሥልጣንም ሆነ አሁን በተጨባጭ ተሰናባቾቹ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉ ሌሎች የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች የሚሠሩት ሥራ የዳኝነት ሥራ አይደለም፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሁሉም የፍርድ ቤት ኃላፊዎች አሁን የሚሠሩት አንድ የፍርድ ቤት ሥራ አስኪያጅ (Court Manager) የሚሠራውን ሥራ ነው፡፡

በአዋጁ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በዋናነት የተሰጠው ሥልጣን ዳኞችን መደልደል፣ ሠራተኛ መቅጠር፣ ዕቅድና በጀት አዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ፣ ሪፖርት ማቅረብ፣ የዳኞችንና የሠራተኞችን ትምህርትና ሥልጠና ማመቻቸት፣ የመዝገብ አያያዝ ሁኔታን ማሻሻል፣ ወዘተ. የሚሉ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቶች በተግባር ሲሠሩ የነበሩት ሥራ ከዚህ የተለየ አይደለም/አልነበረም፡፡ በእርግጥ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ለፍርድ ቤተ ኃላፊዎች የተሰጠው ሥልጣን የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ሳይሆን፣ የፍርድ ቤት ሥራ አስኪጅነት ቢሆንም የአንድ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዋናና ተፈጥሯዊ ሥራ ዳኝነት በመሆኑ ከ2010 ዓ.ም. በፊት የነበሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች መዝገብ አገላብጠው፣ መጽሐፍ ገልጠው፣ በችሎት ተሰይመው ክርክር ሰምተው ፍርድ ይሰጡ የነበረ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅጽ 9 በ2003 ዓ.ም. ታትመው ከወጡ 144 የሰበር መዝገቦች ውስጥ በወቅቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት በ37 መዝገቦች ላይ፣ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ በ18 መዝገቦች ላይ ተሰይመው ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ከሥራ የተሰናበቱት የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በአንድ በኩል ከተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥራቸው ርቀውና ለሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ጊዜ መድበው፣ በሌላ በኩል የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ መሆናቸው በዳኝነት ሥርዓቱ መታመን ላይ ጥያቄ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡   

በዳኝነት መዋቅሩ (Judicial Prism) ከከፍተኛው የዳኝነት አካል ሥርና ከዝቅተኛው የዳኝነት አካል በላይ የሚገኙት፣ በሥር ፍርድ ቤቶች የተጓደሉ ፍርዶችን በማቃናት፣ በሥር ፍርድ ቤቶች የተፈጸሙ መሠረታዊ የሕግ ስህተቶችን በማረም ፍትሕ እንዲረጋገጥ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው የይግባኝና የሰበር አጣሪ ችሎቶች የቀረበላቸውን ቅሬታ ያለ በቂ ምክንያት፣ ያለ በቂ ማብራሪያ ውድቅ የሚያደርጉ በመሆኑ የይግባኝ ሰሚና የሰበር አጣሪ ችሎቶች የዳኝነት ሥርዓቱ አካሎች በመሆናቸው ላይ ሳይቀር ጥያቄ እየተነሳባቸው ይገኛል፡፡

የይግባኝና የሰበር አጣሪ ችሎቶች የዳኝነት ሥርዓቱ እንዲታመንና እንዲጎለብት የሚያደርግ ሥራ እንዲሠሩ የሚጠበቁ ቢሆንም፣ በተግባር የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ይከናወናል የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌው ጭምር በመጣስ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ መታመን እንዲታጣ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ትክክለኛ ዳኝነት የሞተውም የተቀበረውም ይግባኝ ሰሚና ሰበር አጣሪ ችሎቶች ሲደርስ ነው፡፡ ለይግባኝና ለሰበር የቀረቡ ቅሬታዎችን ያለ ምንም ማብራሪያ በደፈናው ውድቅ ማድረግ የዳኝነት አካሉ የዳኝነት ሥርዓት ሆኖ ተወስዷል፡፡ ዜጎች የጠየቁትን ዳኝነት የተከለከሉበትን የሕግና የፍሬ ነገር ምክንያት በግልጽ፣ የማወቅ ሕገ መንግታዊ መብት ያላቸው ቢሆንም፣ የይግባኝና የሰበር አጣሪ ችሎቶች ይህንን የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት በዘፈቀደ ሲጥሱ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት የተጣለበት ራሱ የዳኝነት ሥርዓቱ በዝምታ እየተመለከታቸው ይገኛል፡፡

ለ. መርህና ተጠያቂነት የሌለው የዳኝነት ሥርዓት መሥፈን

ማንኛውም ተቋም እንዲሁም፣ ማንኛውም ሰው በጣሰው ሕግና በሠራው ጥፋት በሕግ ተጠያቂ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ተቋም ነው መባሉ ፍርድ ቤቱን እንደተቋም፣ በውስጡ የሚሠራውን ዳኛም በግሉ ከየትኛውም ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ከአሁን በፊት ‹‹ከተጠያቂነት እየሸሸና እያመለጠ ያለው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት›› በሚል በሪፖርተር ጋዜጣ ታትሞ በወጣ ጽሑፍ የዳኝነት ሥርዓቱን ውስጣዊ ተጠያቂነት (In-House Or Endogenous Accountability) ያረጋግጣሉ የተባሉ የፍርድ ምርመራ (ኢንስፔክሽን) እና የሕግ ጥናትና ምርምር ክፍሎች ሥራቸውን እንዳይሠሩ ስለመደረጋቸው በሰፊው ተብራርቷል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ኃላፊነትን የተረከቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቶች በያዙት የሚዲያና ስታትስቲካዊ ጨዋታ የይግባኝና የሰበር አጣሪ ችሎቶች የዳኝነት ሥርዓቱን ውስጣዊ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የማይችሉ የይግባኝ ሰሚና ሰበር አጣሪ ችሎቶች፣ ልባቸው ያሰበውን ያህል ጥፋት እየፈጸሙ ከማናቸውም ተጠያቂነት ነፃ ስለመሆናቸው በሰፊው ተመልክቷል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱን ውጫዊ ተጠያቂነት (Exogenous Accountability) ያረጋግጣል የተባለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔም በጠራ መርህና የዳኝነት ሥርዓቱን ተጠያቂነት ሊያረጋግጥ በሚችልበት ሁኔታ ያልተዋቀረ በመሆኑ፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የፍርድ ቤቱን አመራር የተረከቡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቶች የዳኞች አስተዳደር ጉበዔ ተቋማዊ ገጽታ እንዳይኖረው በማድረጋቸው የዳኝነት አካሉ ከማናቸውም ተጠያቂነት ነፃ ሆኖ በኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ላይ እንዳሻው እያዘዘ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡

የዳኝነት አካሉን ውጫዊ ተጠያቂነት ያረጋግጣል በሚል ‹‹የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ›› በ1988 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 24/88 የተቋቋመ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 684/2002 ተሻሽሎ ተቋቁሟል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ‹‹የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ›› በሚል በአዋጅ ቁጥር 1233/2013 አንቀጽ 5 የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሚል ስያሜ በድጋሚ ተቋቁሟል፡፡ በሦስቱም አዋጆች የጉባዔው ዓላማ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሲሆን፣ የዳኞች አስተዳደርን ከማናቸውም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ተፅዕኖ ነፃ በሆነ ሁኔታ እንዲመራ ማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች ከማናቸውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ማድረግ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ተጠያቂነት ማስፈን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ግልጽ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ በሆነ አሠራር የሚሾሙበት ሥርዓት በመዘርጋት የፍርድ ቤቶችንና የዳኞችን ብቃት፣ ነፃነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት በማረጋገጥ የዳኝነት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን ያስከበረና የሕዝብ አመኔታን ያገኘ እንዲሆን ማድረግ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

የጉባዔ አባላትን ብዛት ስንመለከት በመጀመርያው ማቋቋሚያ አዋጅ ዘጠኝ፣ በሁለተኛው ማቋቋሚያ (ማሻሻያ) አዋጅ 12 የነበሩ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 1233/2013 የአባላቱ ብዛት 15 እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በስብጥር ረገድ የጉባዔው አባላት ተዋጽኦ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት የጉባዔውን ሥራ በተደራቢነት የሚሠሩ ናቸው፡፡ አዋጁ ሦስት ኮሚቴዎች ያቋቋመ ቢሆንም፣ እነዚህ ኮሚቴዎችም የጉባዔውን ሥራ የሚሠሩት በተደራቢነት ነው፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኝነት ሥርዓቱን የመምራት ሥራውን የሚያከናውነው በተመላላሽ ሠራተኞች (Part Time Workers) ነው ለማለት ይቻላል፡፡

የአዋጆችን ዕድገት (Metamorphosis) ስንመለከት ተቋሙ ከዳኛች አስተዳደር ጉባዔ (Judges Administration Council) ወደ ዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ (Judicial Administration Council) ለመሸጋገር ፍላጎት ያሳየ ቢመስልም፣ በሥልጣንና ተግባር ዝርዝሩ ጉባዔው አሁንም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከመሆን ብዙም ፈቀቅ ያለ አይደለም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ መሆንና የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ መሆን በእጅጉ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ተቋሙን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሚል የምንጠራው ከሆነ የጉባዔው ዋና ሥራ በዳኞች ምልመላ፣ ቅጥር፣ አስተዳደርና ስንብት ላይ ብቻ ማተኮር ነው፡፡

ተቋሙን የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ በሚል የምንጠራው ሲሆን፣ የተቋሙ ኃላፊነት ከዚህ በእጅጉ የሰፋና የላቀ ነው፡፡ ተቋሙ የዳኝነት አስተዳደር ተቋም ሆኖ ሲጠራና ሲደራጅ በጠቅላላው የዳኝነት ሥርዓቱን የመምራት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ከስሙ መጠሪያ ጀምሮ ለመረዳት እንደምንችለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሥልጣንና ተግባር መግለጫውም ሆነ በተጨባጭ በሚያከናውነው ሥራ ወደ ዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ ለመሸጋገር የቻለ አይደለም፡፡

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚባለው ተቋም በዳኞች አስተዳደር ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑ የዳኝነት ሥርዓቱን የሚመራ ተቋም የሌለን መሆኑን ያስረዳናል፡፡ የኢትዮጵያን የዳኝነት ሥርዓት የሚመራ የዳኝነት ተቋም ከሌለ የዳኝነት ሥርዓቱ ሲመራ የነበረው እየመጡ፣ እየተጠቀሙ ሲሄዱ በነበሩ ሰዎች መልካም ፈቃድና ፍላጎት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ አሁንም የሆነው ይህ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የመጡ አመራሮች የሠሩትንና የጣሉትን መሠረት ሳናይና ሳናውቅ ለምን ኃላፊነታቸውን እንደለቀቁ እንኳን ሳናውቅ ፍርድ ቤቱን ሲፈልጉ የሚገቡበት ሲፈልጉ የሚወጡበት ክፍት በር አድርገውት ሄደዋል፡፡ ይህ የሆነው በትክክልም የዳኝነት ሥርዓቱ የሚመራበት ሥርዓትና ባለፈው 30 ረጅም የሥራ ዘመን በተግባር የዳበረ የፍርድ ቤት አመራር ሥርዓት የሌለ በመሆኑ ነው፡፡    

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሚል በአዋጅ የተቋቋመው ተቋም በፊት የፖለቲከኞች መጫወቻ የነበረ ሲሆን፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መጫወቻ ነበር፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተቋም ሳይሆን፣ አንድ ግለሰብ ነበር፡፡ ያ ግለሰብም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ ይህ ግለሰብ ሲፈልግ ጉባዔው ሲሰበሰብ፣ ይህ ግለሰብ ሳይፈልግ ጉባዔው እንደተበተነ እንዲቀር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሲፈልግ ጉባዔውን አዲስ አበባ ላይ ይሰበስበው ነበር፣ ሲፈልግ ደግሞ ጉባዔውን በሻንጣው ውስጥ ጠቅልሎ ከቶ ወደ አዳማና ወደ ባህር ዳር ለሽርሽር ይዞት ሲሄድ ነበር፡፡ አጠቃላይ ሕግ፣ የተቋሙ ሕግ በማይገዛው ሰው ሲመራ የነበረው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ምንጊዜም ቢሆን ግለሰብ ነበር እንጂ ተቋም ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተቋም ሳይሆን፣ ግለሰብ ነበር ከተባለ አጠቃላይ የዳኝነት ሥርዓቱም የግለሰብ ፍላጎትና የግለሰቡ ነፀብራቅ ነበር ለማለት ያስችለናል፡፡

ከመርህ አኳያ የአንድ የዳኝነት ሥርዓት መሠረታዊ መርህ ነፃነትና ገለልተኝነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት በነፃና ገለልተኛ መርህ የሚመራ ሳይሆን፣ ዓይን ያወጣ የፆታና የብሔር ድልድል የሚቀላጠፍበት ቦታ ነው፡፡ የፆታና የብሔር ጉዳዮች የፖለቲካ ጉዳዮች እንደመሆናቸው መጠን በተገቢው የፖለቲካ መድረክ እንደ አግባቡ መስተናገዳቸው ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፆታ ከግምት ሳይገባ፣ ዘር ከግምት ሳይገባ፣ ብሔር ከግምት ሳይገባ፣ ቀለም ከግምት ሳይገባ፣ ቁመትና ውፍረት ከግምት ሳይገባ፣ ሀብትና የኑሮ ደረጃ ከግምት ሳይገባ ሁሉም የሰው ልጅ በሕጉና በሕግ አነጋገር መሠረት ብቻ እኩል በሚስተናገድባቸው ፍርድ ቤቶች የሚሠሩ ዳኞች በፆታና በብሔር ማንነታቸው እንዲሾሙ ማድረግ፣ በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታይ ከፍተኛ የመርህ ጥሰት ነው፡፡

ሲጠቃለል የዳኝነት ሥርዓታችን የሚመራበት መርህና መሪ ተቋም የሌለው መሆኑን እንረዳለን፡፡ የዳኝነት ሥርዓታችን መሪ ተቋም የሌለው እስከሆነ ድረስም በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ተጠያቂነት ያለውን አሠራር ለመዘርጋት የሚቻል አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ የተዘረጋው የዳኝነት ሥርዓት ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ፣ ከአምስት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ለሚያመነጭ ሕዝብ የሚመጥን አይደለም፡፡ በዚህ ደረጃ ግብር ለሚያመነጨው ሕዝብ የዳኝነት አገልግሎት ለሚሰጠውን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ቋሚ ዳኞችን አለመመደብ፣ የዳኝነቱን ሥርዓት ለሚመራው የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ ቋሚ የጉባዔ አባላትን አለመመደብ፣ ብቃት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ሰፊው ሕዝብ በተሳተፈበትና የሰፊው ሕዝብ ይሁንታ በተገኘበት ሁኔታ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን አለመመደብ፣ የዳኝነት ሥርዓቱ ሁሌም እንደ ቃልቻ እየተሸፋፈነ በሥርዓቱ ውስት ግልጽ አሠራር እንዳይዳብር ተጠያቂነት እንዳይፍን መደረጉ ሕዝቡን በግልጽ ዳኝነት ከመከልከል ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡

የዳኝነት ሥርዓቱ ሥርዓታዊ ችግሮች መፍትሔዎች

  1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ መሆናቸው የመርህና የአፈጻጸም ችግር ያለው ቢሆንም፣ ሁለቱ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች የጉባዔው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመሆኑ ይህ ችግር በአጭር ጊዜ የሚቀረፍ አይደለም፡፡ በኃላፊት መደራረብ ምክንያት ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ላይ የሚታየውን ችግር መቅረፍ የሚቻለው፣ ለዳኝነት ሥርዓቱ መሻሻል ህልምና ፍላጎት ያለውን ሰው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ በመሾም ብቻ ነው፡፡ ቀሪ የጉባዔው ዘጠኝ አባላት የጉባዔው ቋሚ ዳኞች ሆነው ሊሾሙ ይገባል፡፡ ለጉባዔ ቋሚ ዳኞች የሚከፈል ገንዘብ ቆጥበን በፍትሕ ስብራት ከምንጎዳ ጉባዔው የሚያስፈልገውን ሁሉ ወጪ አውጥተን የምንተማመንበት የዳኝነት ሥርዓት ሊኖረን ይገባል፡፡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ቋሚ ዳኞች እንዳይኖሩት የተደረገው በወጪ ምክንያት ሳይሆን፣ በፖለቲካ ፍላጎት ምክንያት ከሆነ በዳኝነት ሥርዓት ያልተደገፈ ፖለቲካ ዘለቄታ የሌለው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
  2. የዳኝነት ሥርዓቱን የሚመራ መሪ ተቋም አስፈላጊ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በልዩ ልዩ አገሮች የዳኝነት ሥርዓቱን የሚመራው ተቋም የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ (Judicial Administration or Judicial Commission) በሚል የሚጠራ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከስም ባለፈ የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ የሚባል ተቋም በአዋጅ ቢቋቋምም፣ በተግባር እንዳይደራጅና በአዋጁ የተሰጠውን ሥራ እንዳይሠራ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ የቆየና አሁንም በመደረግ ላይ ስለመሆኑ በተግባር የምናየውና በሁሉም ዘንድ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔው በተቋምነት እንዳይቆም ዋናውን ሚና የሚጫወቱት፣ የተሰናበቱትን ጨምሮ የፍርድ ቤት አመራሮች መሆናቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የመጀመርያው የመፍትሔው አካል በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓቱን የሚመራ ተቋም እንዳይኖር የፍርድ ቤት አመራሮች ለምን ፈለጉ የሚለውን በጥናትም ሆነ በምርመራ መለየት ያስፈልጋል፡፡ የምርመራው ውጤት ምንም ይሁን ምን ከቡድኖችም ሆነ ከግለሰቦች መዳፍና ፍላጎት ነፃ የሆነ የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋምና ማደራጀት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡
  3. ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ማናቸውም የዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝም ሆነ ውድቅ ሲደረግ ትዕዛዙ/ውሳኔው/ፍርዱ በበቂ ምክንያት የተብራራ እንዲሆን ማድረግ፣ በበቂ ምክንያት ሳይብራሩ በተሰጡ ትዕዛዞች/ብይኖች/ፍርዶች፣ በዘፈቀደ ምክንያት በተብራሩ ትዕዛዞች/ውሳኔዎች/ፍርዶች፣ በተሳሳተ ሕግና ፍሬ ነገር ላይ ተመሥርተው በተሰጡ ትዕዛዞች/ውሳኔዎች/ፍርዶች ላይ ተመጣጣኝና አስተማሪ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ በአገራችን ተመልካችና ጠያቂ ያጣው ‹‹የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት›› የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ድንጋጌ በግንባር ቀደምነት በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲተገበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...