Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአዲስ አበባ የማን ነች? እኛስ ማን ነን?

አዲስ አበባ የማን ነች? እኛስ ማን ነን?

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

አዲስ አበባ የማን ነች? የሚል ጥያቄ የሚያጭሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም አንስቼ ከማውሳት ጥቂት ነገሮችን ብዬ ልለፍ።

አዲስ አበባ ከተቆረቆረችበት ዘመን አንስቶ የነዋሪዎቿ ንብረት፣ ውስጧ ለተወለዱት የእናት ጓዳ ስትሆን፣ የኢትዮጵያ መናገሻ ወይም ዋና የመተዳደሪያ፣ ሕግ የሚወጣባት፣ የሚፀድቅባት፣ የመላው ኢትዮጵያዊ መገናኛና መተዋወቂያ ዕምብርትና ከ1955 ዓ.ም. ጀምራ ደግሞ የአፍሪካ ዋና ከተማ ናት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚያም አልፋ ተርፋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽንን ያስተናገደችና የምታስተናግድ ታላቅ የኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የአፍሪካውያን አለኝታና መመኪያ ናት፡፡ አዲስ አበባ ክብሯን ጠብቃ መላው አፍሪካውያንና የጥቁር ሕዝቦችን ለማስከበር ዋነኛ ማዕከል ስትሆን፣ ዛሬ ሊበጣጥሷት የሚሽቀዳደሙ አልሚዎች ሳይሆኑ አጥፊዎች ላይ ታች የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የዓለምን ሁኔታ ቢገነዘቡ መልካም ነው ለማለት ተነሳሳሁ።

በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያለው አስተዳደር ማድረግ የሚገባው ከተማዋን በተገቢው መንገድ በማሳመር ፕላኑን ጠብቆ የሚሄድ ልማት ማከናወን፣ ከተማዋ የዓለም ሕዝብ መሰባሰቢያ እንደ መሆኗ ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለመስተካከል መጣር፣ ትምህርት ቤቶችን በሚገባ አስተካክሎ ወጣቱ በትምህርት እንዲጎለብት ማድረግ ይገባዋል፡፡

በየትኛውም አገር በማይታይ ሁኔታ አንዲት ወጣት ኢትዮጵያዊት እናት ሕፃን አዝላ በየጎዳናው ለልመና ተሰማርታ ስትታይ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ፣ ለመሰል በመከራ አዘቅት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎችና ለሕፃናቱ መጠጊያ በመሥራት ተገቢውን ትምህርት እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የመጀመሪያው የሹማምንቱ ኃላፊነት መሆን ያለበትም ይህንን መሰል ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ የችግሩ መጠን ገብቶትና ተሰምቶት ሠርቶና የሚያሠራ የሕዝብ አሽከር እንጂ፣ የሕዝብ ጌታ ወይም እመቤት ነኝ ባይ ሹማምንት ለአዲስ አበባ አያስፈልጉም። አገር በቁጭት፣ በምኞትና በትዕቢት አይመራም፡፡ ለጊዜው በቦታው ያሉ ሊገነዘቡ ባይችሉም የዓለምን ሁኔታ፣ ያለፈውንና ያለውን ታሪክ አገላብጦ ማየት ይጠቅማልና ይመልከቱ።

ስለአዲስ አበባ ማወቅ እንዲችሉ ብዙም ሳይሆን በጥቂቱ ሁለት ምሳሌዎችን ለግንዛቤ ያህል ላንሳ፡፡ አንደኛ ምክትል ከንቲባ የነበሩትን የተከበሩ አቶ ሙሉጌታ ሥነ ጊዮርጊስን፣ ሁለተኛ ክቡር ከንቲባ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወትን በምሳሌነት ላቅርብላችሁ። በነገራችን ላይ የተከበሩ የሚለውንና ክቡር የሚለውን ልዩነት የማያውቁ ባለሥልጣናት በዘመኑ ስለተፈጠሩ በመጨረሻ ላይ ለመግለጽ ወስኛለሁ፡፡

አቶ ሙሉጌታ ሥነ ጊዮርጊስ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ምን ጎድሏል? አካባቢው ውኃ አጥቶ ይሆን? የተቸገረስ ይኖር ይሆን? ተገቢውስ መገናኛ አለ? ከሌለስ ምን ማድረግ አለብን የሚሉና የመሳሰሉትን በራሳቸው አጣርተው መፍትሔ ሳይውል ሳያድር እንዲገኝ ያደርጉ ነበር።

ክቡር ከንቲባ ቢትወደድ ዘውዴ ከዘመናቸው የቀደሙ ደሃ፣ ጌታ፣ ልጅ ወይም አዋቂ ሳይሉ በሰብዓዊነት የተሞሉና ለአገራቸው የሚያስቡ ነበሩ፡፡ ዛሬ የምንኮራበትን ግዙፍ ማዘጋጃ ቤት እንዲሠራ ሐሳብ የጠነሰሱና ውጤቱንም በቁማቸው ለማየት የበቁ ታላቅ ከንቲባ ነበሩ። እንኳንስ ከተማዋ ልትሸረሸርና የተከፋፈለች ልትሆን ቀርቶ፣ የአገር ኩራትና መመኪያ ያደረጉ ሰው ነበሩ።

ዛሬ ታዲያ ምን ነክቶን ነው ከተማዋን በተለያዩ ምክንያቶች የምናብጠው? ልብ እንግዛ እንጂ፡፡ የጠላቶቻችንም መሳለቂያ እንዳንሆነም መጠንቀቅ አለብን። የውጮቹን አለባበስና ቋንቋቸውን በመገልበጥ ብቻ እነሱን ለመምሰል አንጣር፡፡ ነገር ግን ከሥራ ልምዳቸው ለመቅሰምና የሚበጀንን ለመውሰድ እንትጋ።

በእርግጥ ሰዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ እንዳመጣጣቸው ቢሄዱ መልካም ይሆናል፡፡ ገና ለገና ተሹሜያለሁና ብሎ በማናለብኝነት ለሚያልፍ ሥልጣን የማያልፍ ታሪክን የሚያጎድፍ ሁኔታ ፈጥሮ ማለፍ እጅግ የከፋ ይሆናልና መጠንቀቅ ያሻል።

እንዲያው ለመሆኑ የከተማው ባለሥልጣናት አዲስ አበባን ያውቁ ይሆን? አንድ ምሳሌ ልስጥ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ የትራፊክ ፍሰት ወይም የአነዳድ ሥልት በግራ በኩል ነበር፡፡ ታዲያ ይህ የቅኝ ገዥዎች የአነዳድ ሥልት ስለሆነ ሌሎች አፍሪካውያን ሳይወዱ በግድ የለመዱት በመሆኑ ከቋንቋው ጭምር ሲቀጥሉበት ኩሩዋ፣ በነፃነቷ፣ በሥልጣኔዋና የአፍሪካ የነፃነት ዋቢዋ ኢትዮጵያ ግን ያንን ፈለግ መከተል የለባትም የሚሉ አርቆ አሳቢ መሪዎቻችን በቆራጥነት ተነሳስተው በግራ ሳይሆን አነዳዳችን በቀኝ መሆን አለበት ሲሉ ወሰኑ። ይህንን ሥራ ላይ ሲያውሉ ጠንካራው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግራ ይነዳ የነበረውን የአነዳድ ዘይቤ ለውጦ፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቀኝ አነዳድን ተለማመደ።

ዛሬ ግን መቅደም፣ ማስመሰልና ብልጣ ብልጥ ሆኖ መገኘት ታላቅ ዕውቀት የመሰለው ያገሬ ወጣት ግራውንና ቀኙን የማያውቅ በሚመስል ሁኔታ ሲራወጥ ይታያል። ይህንን መስመር ማስያዝ ያቃተው የከተማው አስተዳደር ሌላውን ያዋክባል። ለምን? ልምዱም ዕውቀቱም የሌላቸው የይድረስ ይድረስ ሹማምንቶች በመሆናቸው፣ አዋቂንም ለማማከር የማይሹና ከጊዜ ብዛት ለመማር ሳይሆን ለመዘባነን የተኮፈሱ ይመስላሉ።

ወገኖቻችንም ሕግን በመከተል ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያን በመስጠት፣ የቁም ምልክት ባለበት ቦታ ላይ ሰው አለ የለም ሳይሆን ሕግን ብቻ በመከተል አክብረውና ተከባብረው ያከናውኑ ነበር። ያ ሁሉ ቀርቶ ዛሬ በኢትዮጵያ አነዳዱ በግራ ይሁን በቀኝ ያልታወቀበት ዘመን ሆነ፡፡ አጥፊ እንደልቡ ሲፈነጭ ሕግ አክባሪ የሚከሰስበትና የሚቀጣበት ሁኔታ ተፈጠረ።

ታዲያ ይህንን እንኳ ማስተማርና ማስተካከል ያልቻለ የከተማ አስተዳደር ከተማዋን አለማሁ ብሎ ወደ ዝብርቅርቅነት ሲቀይራት፣ ረጋ ብላችሁ ተመልከቱ የሚል መጥፋቱ እየገረመኝ ነው። ትንሽ ተመክሮዬን ላካፍልና ቢሻችሁ ይህ ጉዳይ እውነት ወይስ አስመሳይ ብላችሁ ለመረዳት እንድትችሉ ሐሳቤን ላካፍላችሁ።

ዛሬ ዓለምን የምትመራው አሜሪካ የመጀመሪያ መሪዋ ጆርጅ ዋሽንግተን ከኒዮርክ ከተመረጠና ቃለ መሃላውን ከፈጸመ በኋላ፣ የአሜሪካ ዋና ከተማ የሆነችው ፔንሲልቪኒያ ነበረች፡፡ ነገር ግን ለደቡቡ፣ ለሰሜኑ፣ ለምዕራቡና ለምሥራቁ አመቺ ቦታ ተፈልጎ የአሜሪካን ዋና ከተማ የት ቢሆን ያመቻል ትብሎ ተመክሮና ታስቦበት ሲወሰን፣ ከፔንሲልቪኒያ ይልቅ ለሁሉ የሚያመች አካባቢ መምረጥ ተጀመረ፡፡

ከሜሪላንድና ከቨርጂኒያ ቁራጭ ቁራጭ መሬት ተወስዶ የአሜሪካ ዋና ከተማ እንዲሆን ተወሰነ። ይህም ውሳኔ ፀድቆ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ፕሬዚዳንቶች ዋሽንግተን ነጩ ቤት ሳይገቡ አለፉ። ይሁን እንጂ ከሁለት ጠቅላይ ግዛቶች የተውጣጣችው ዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ዋና ከተማ ስትደረግ፣ ከሁሉም ነፃ የሆነችና የመምረጥም ሆነ የመምረጥ መብት የሌላት በመሆን ለሁሉም እኩል ከተማ ሆና እስከ ዛሬ ድረስ ታገለግላለች፡፡

ወገንተኝነት የሌላት ከተማ (ኒውትራል ሲቲ) ተብላ ራሷን ብቻ ስታስተዳድር ኖራ ባለፉት 15 እና 16 ዓመታት ይመስለኛል ለታዛቢነት እንኳ በአሜሪካ ኮንግረስ (የሕግ ምክር ቤት ውስጥ) መቀመጫ ይሰጣት ተብሎ በቀረበ አቤቱታ መሠረት፣ ያለ ምንም ድምፅ አንድ ታዛቢ ተፈቅዶላታል። በዚህ የተነሳ “Taxation without representation” በሚል እሮሮ የሚያሰሙ ነበሩ። ይህም ማለት የቨርጂኒያም ሆነ የሜሪላንድ ኅብረተሰብ የዛሬ 300 ዓመታት የእኛ ነበረ ስለሆነ፣ ዛሬ ይሰጠን ወይም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ገብተን እናምስ አይሉም፡፡ ይሁንና በዋሽንግተን ዲሲ ማንኛውም ነዋሪ ያለ አድልኦ ይስተናገዳል፡፡

ታዲያ የዛሬዎቹ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ትናንት ያልነበረን ችግር ከመፍጠር በመቆጠብ አሁን የሚስተዋለውን ችግር ፈትተው ወደ ልማትና ዕድገት መጓዝ ሲገባቸው፣ ሰውን ለመከፋፈልና አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ለመክተት ምነው ተሯሯጡ? ወሬና ልማት፣ መበጥበጥና ሰላም አንድ አይደሉምና እንጠንቀቅ፡፡ አገርን በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ለማራመድ መራኮት ሲገባ፣ ለጭቅጭቅና ለአሉባልታ ዘመቻ መሯሯጥ ዕውቀት ወይስ ድንቁርና? ወሬ አቀባባዮችም ለምታገኙት ሶልዲ ብላችሁ አገርን አትበጥብጡ፡፡ አደብ ግዙ፡፡

የፖለቲካ መሪዎችም ሰከን ብላችሁ እስኪ ማንነታችሁን፣ ከየት እንደተነሳችሁና ከየትኛው ኢትዮጵያዊ እንደምትለዩ ራሳችሁን መርምሩ፡፡ ማን ከማን ያንሳል? ይበልጣልስ? ሁላችንም አንድ መሆናችንን ተገንዝባችሁ ለጋራ አገርና ጥቅም ብትሰማሩ ሊያፋጁንና ሊያለያዩን አቆብቁበው ለሚጠብቁን መሣሪያ አትሆኑም፡፡ ከጠነከራችሁ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አፍረው እንዲርቁን የማድረግ ኃይል ይኖራችኋልና ለበጎ ተግባር ተነሳሱ።

እዚህ ላይ መገንዘብ የሚያስፈልገው ፖለቲካ ብቻ አይደለም የሥልጣን፣ የታላቅነትና የሀብት ማግኛ መንገድ፡፡ ጠንክሮ የሠራ የትም ሊደርስ ይችላልና ለጥቅም ብላችሁ አገራችሁን አትበድሉ። ሁሉም ፀጋ የሞላትን አገር ይዛችሁ እንደሌላት ደሃ አትሁኑ፡፡ ከወገናችሁ ጋር ለመተባበር እንጂ ለመለያየትና ለመፋጀት ጊዜያችሁን አታባክኑ።

ከላይ ቃል እንደገባሁት “የተከበሩ” እና “ክቡር” የሚለውን ልዩነት ላልተረዱ ወገኖቼ ገልጬ ልለፍ በማለት ይህንን ማለት ፈለግኩ፡፡ “ክቡር” የሚባሉት ከሚኒስትር ደኤታነት በላይ የሚገኙ ሹማምንት ናቸው፡፡ ዳይሬክተር፣ ዋና ጸሐፊና ምክትል ሚኒስትር ድረስ “የተከበሩ” ይባላሉ። በውትድርና መስክ ከብርጋዲዬር ጄኔራል በላይ ለሆኑት “ክብር” ሲሆን፣ “የተከበሩ” ደግሞ ከሻለቃነት እስከ ሙሉ ኮሎኔልነት የመለያ የማዕረግ ደረጃ መሆኑ ነው። ይኼውም በእንግሊዝኛ “ኤክሴሌንሲ” እና “ሆነረብል” (Excellency – ክቡር  Honorable – የተከበሩ) ማለት ነው። በዘልማድ ብቻ አንኳትን ለማለትና ከላይ ቃል በገባሁት መሠረት መልክ ለማስያዝ ብዬ ነው።

በሉ እንግዲህ ለአገራችን ሰላሙንና አንድነቱን፣ እንዲሁም ለእኛ ደግሞ ጤናውንና ፍቅሩን ያድለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...