በዓላትን ብዙዎች ማክበር የሚፈልጉት በቤታቸው ነው፡፡ ተገቢና ትክክለኛው ቦታውም ቤት ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ ከቤታቸው ውጭ የሚያከብሩ ካሉም ሁኔታዎች ያላመቿቸው ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዓላትን በቤት ማክበር ተጀምሮ ሆኖ ከዚያ ወደ ጎረቤት እያለ እያለ ይሰፋል፡፡
ለዚህም ነው በሥራ፣ በትምህርት፣ በንግድም ይሁን በሌሎች ሁኔታዎች በዓላትን ለማክበር ጊዜያቸውን በዓላትን ለማክበር ወደ ቤተሰቦቻቸው ዘመድ ወዳጆቻቸውና ወደሚመቻቸው ሥፍራዎች የሚያቀኑት፡፡
በዓላትን ያላቸውን ተካፍለው በመብላትና በመጠጣት ተደስተውና ትዝታ በሚፈጥሩ መንገዶች ለማክበርም ጥረት ያደርጋሉ፡፡
የዛሬ በዓል የነገ ትዝታና ትውስታም ሆኖ ለማውሳትም በዓላትን ከቅርብ ሰዎች ሆኖ ማክበር ተመራጭ ይሆናል፡፡
ሰዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ሆነው በዓላትን ባልፈለጉበትና ባልጠበቁበት ቦታዎች ለማክበር ተገደው ይሆናል፡፡ ምክንያቶቻቸው ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ በመሆናቸው ምንም ሊያደርጉ ሳይችሉ ቀርተዋል:: ‹‹መቼስ ማል ጎደኒ›› እንደሚባለው፡፡
እኔና ባልደረባዬ የዘንድሮን የልደት በዓል (ገና)ን በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ያሳለፍንበት ሁኔታ ግን፣ በምንም መንገድ መሆን ያልነበረበትና በተለይ በዓሉን በዓል እንዳይመስለን ያደረገ ሁኔታ/ክስተት ነበር፡፡
ሐረር ላይ ለነበረን ሥራ ማክሰኞን ከአዲስ አበባ መድረሻ፣ ቅዳሜን ደግሞ መመለሻ እንዲሆን አድርገን የአወሮፕላን ቲኬት ይቆረጥልናል፡፡ የምንሄድበት ሥራ ምናልባት ካቆየን ብለን እንጂ፣ ቀድመን ልንመለስ እንደምንችል ገምተናል (ቅዳሜ የልደት በዓል መሆኑን አልረሳንም)፡፡
ሥምሪታችንን ሐሙስ አጠናቀን ዓርብ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የድሬዳዋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍን ወንበር እንዳለ ስንጠይቅ፣ በዕለቱ ባሉት በረራዎች ሁሉ ክፍት ወንበሮች እንዳሉ አረጋገጡልን፡፡ የበረራ ሰዓታችንን መርጠን መብረር እንደምንችል ተነገረን፡፡
ነገር ግን እያንዳንዳችን አንድ ሺሕ ስድስት መቶ (1,600) ብር መክፈል እንዳለብን ተነገረን፡፡
ቀጣዩ ቀን በዓል መሆኑን አስታውሰን ባሉት ወንበሮች እንዲያሳፍሩን ለማግባባት ብንሞክር፣ ባዶ ወንበሮችን ሞልተን ብንሄድ በወንበራችን ሌሎች መንገደኞች የሚተኩበት ዕድል እንዳለ ለማስረዳት ብንጥርም ማን ሰምቶን፡፡
ይህንንስ በከፊል የራሳችን ጥፋት ይሆናል ብለን ተቀበልነው፡፡ ሆኖም አየር መንገዱ በአንድና ገንዘብ አምላኪ በሆነ አካሄድ ብቻ እንደሚሠራ ታዘብነውም፡፡
በነጋታው የልደት በዓል በሕዝበ ክርስቲያን መከበር ጀመረ፡፡ እኛም ከዕኩለ ቀን ጀምሮ በዓሉን ከቤተሰቦቻችን ከዘመዶቻችን ከወዳጆቻችን ጋር እናከብራለን ብለን ለአራት ሰዓት በረራ ቀድመን ኤርፖርት ደረስን፡፡ ረፋዱ ላይ የነበረው በረራው ተሰርዞ እስከ ሰባት ሰዓት ጠብቁ ተባልን፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት የደረስነው መንገደኞች ዕጣ ፋንታችን ካፊቴሪያ መክተም ሆነ፡፡
ለበዓሉ የሚጠብቁንን በቤታችን አስቀምጠን እንኳን ሰው ድመቶችና ውሾች ጠግበው በሚውሉበት ቀን የማይገባ ወጪ አውጥተን በዓሉን በትካዜ ለማሳለፍ ተገደድን::
የተባለውን ሰዓት ባልጠበቀው በረራ ተጠቅመን የምንናፍቀውንና የምናከብረውን በዓል ባልሆነ ሁኔታ ተጉላልተን ዋልንና ባለቀ ሰዓት በየቤታችን ገብተን አከበርነው፡፡ በስደትና በመከራ ውስጥ የነበርን እስኪመስለን ድረስ ተሰምቶን አሳለፍነው፡፡
ገጠመኜን የማጠናቅቀው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥያቄዎችን በማቅረብ ይሆናል::
አንደኛው ደንበኞቹ ከተመዘገቡበት በረራ አስቀድሞ ባሉት ባዶ ወንበሮች ቢጠቀሙ ጉዳቱ ምንድነው? ባሉት ባዶ ወንበሮች መጠቀም ወረፋ የሚጠብቁ መንገደኞችን ለማስተናገድ ዕድል አይሰጥም ወይ? ሁለተኛው በረራዎች ሲሰረዙ ማሳወቅ አይገባም ወይ?
መንገደኞች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጉዞአቸውን ካስመዘገቡት ጊዜ አስቀድመው ለማድረግ ቢፈልጉ ተጨማሪ ክፍያ ከመጠየቅ ባለፈ፣ ለምን ሌሎች ነገሮች ከግምት ውስጥ አይገቡም? ለምሳሌ አጣዳፊ ሕክምና፣ መንግሥታዊ ሥራ፣ በዓላት፡፡
አየር መንገዳችን ገንዘብ ወይም ትርፍ ቢያስብ ችግር የለውም፡፡ ባለና በሚቻል ነገር መንገደኞችን ማገልገል ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አይተናነስም፡፡ ባዶ ወንበሮችን እየሞሉ የጎደለውን ወንበርም በሌሎች ተሳፋሪዎች ለመሙላት ሊሠራ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡
በተረፈ አየር መንገዱ የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብትና እሴት መሆኑ እየታወቀ፣ በዓላትን ለማክበር አገልግሎቱን የፈለጉ መንገደኞቹን ማጉላላት ተገቢ አይደለም እላለሁ::
በበዓል ከመንከራተት ይሰውራችሁ::
(ብርሃኑ ተሰማ፣ ከአዲስ አበባ)